የአምስት ሚኒስትሮች ሹመት በነገው ዕለት በፓርላማ ሊጸድቅ ነው

በቤርሳቤህ ገብረ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገው ዕለት በሚያካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ ከአንድ ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙትን ጨምሮ የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ ሊያያጸድቅ ነው። ፓርላማው በዚሁ ስብሰባው፤ የከተማ መሬትን የተመለከቱትን ሁለት የአዋጅ ረቂቆችን ጨምሮ አራት አዋጆችን ለሚመለከታቸው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ይመራል ተብሎ ይጠበቃል። 

መደበኛ ስብሰባዎቹን ማክሰኞ እና ሐሙስ የሚያካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት፤ ለነገ ጥቅምት 19፤ 2017 ሰባት አጀንዳዎችን ይዟል። በህዝብ ተወካዮች እና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች የመክፈቻ የጋራ ስብሰባ ላይ፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የሚቀርብ “የድጋፍ ሞሽን” ማድመጥ የሚለው ከአጀንዳዎቹ መካከል አንዱ ነው። 

አቶ ታዬ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት፤ በመስከረም ወር መጨረሻ በተካሄደው በዚሁ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ ስነ ስርዓት አንድ ሳምንት በኋላ፤ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስ አቶ ታዬን በመተካት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

ለሶስት ዓመታት ያህል የፍትህ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ጌዲዮን፤ ኃላፊነታቸውን ያስረከቡት ለወ/ሮ ሃና አርአያ ስላሴ ነው። ሃና ይህን ሹመት ከማግኘታቸው አስቀድሞ፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመት ኮሚሽንን ለዘጠኝ ወራት ያህል በኮሚሽነርነት ሲመሩ ቆይተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካኝነት ጥቅምት 8፤ 2017 በተሰጠው በዚሁ ሹመት፤ የቱሪዝም ሚኒስቴርም አዲስ አመራር አግኝቷል። በዚህም መሰረት ለሶስት ዓመት የቱሪዝም ሚኒስቴርን የመሩት ወ/ሮ ናሲሴ ጫሊ ከኃላፊነታቸው ተነስተው፤ በወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ተተክተዋል።  

ወ/ሮ ሰላማዊት ላለፉት ሶስት ዓመታት በመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት በሚኒስቴር ዴኤታነት ሰርተዋል።  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እርሳቸውን ጨምሮ ሶስት ሚኒስትሮችን ከመሾማቸው ሶስት ወራት አስቀድሞ፤ ሌሎች ሁለት አዲስ ሚኒስትሮችን ወደ ካቢኔያቸው ቀላቅለዋል።  

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ በተሰጠው በዚህ ሹመት፤ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር፣ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ደግሞ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል። የሁለቱ ሚኒስትሮች ሹመት እስካሁን ለፓርላማ ቀርቦ ያልጸደቀ ሲሆን፤ በነገው ስብሰባ ሹመታቸው እንደሚጸደቅ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከተወካዮች ምክር ቤት ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን እና ተግባር በሚዘረዝርበት ክፍል ላይ፤ የሚኒስትሮች ሹመት በተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ እንዳለበት ይደነግጋል። ሚኒስትሮች ሹመታቸው በፓርላማ ከጸደቀ በኋላ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አማካኝነት ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ ይደረጋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)