የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት ሁለተኛ ዓመት ሲታሰብ፤ ማን ምን አለ?

አቶ ሬድዋን ሁሴን የፌደራል መንግስትን እና አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ህወሓትን ወክለው፤ ግጭት የማቆም ስምምነት ተፈራርመው፣ እጅ ለእጅ ከተጨባበጡ፤ ትላንት ቅዳሜ ጥቅምት 23፤ 2017 ድፍን ሁለት ዓመት ሞላቸው። ስምምነቱ ለሁለት ዓመታት በትግራይ ክልል ያጓሩትን ጠመንጃዎች ጸጥ በማሰኘቱ፤ በአቶ ጌታቸው አገላለጽ “ስኬታማ” ነው። 

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲቀሰቀስ ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ በመሾም ውጊያው እንዲቆም ከፍተኛ ግፊት ስታደርግ የቆየችው አሜሪካ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ትላንት ምሽት ባወጣችው መግለጫ ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቃለች። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊነት ያመጣቸውን “ጠቃሚ መሻሻሎች” አሜሪካ በአዎንታ እንድምትመለከት ገልጸዋል።

ብሊንከን በዚሁ መግለጫቸው “ከምንም በላይ በትግራይ የአፈሙዝ ላንቃ ዝም ብሎ መቆየቱን” አድንቀዋል። በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች እና ሰብአዊ እርዳታ መጀመራቸው፣ የተወሰኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዎንታዊ ለውጥነት ጠቅሰዋል። 

ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በመበተን መልሶ ከማህበረሰቡ ለማዋሃድ የተያዘው ዕቅድ በዚህ ወር ተግባራዊ እንደሚሆን የጠቆሙት ብሊንከን፤ ይህ እርምጃ “ሰላምን ለማጠናከር” “ወሳኝ” እንደሆነ ገልጸዋል። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ያደረጋቸው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ እና የትግበራ ፍኖተ-ካርታ፤ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅ ለማውረድ መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውንም አስገንዘበዋል። 

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ዝግጅት ያደረገበት የሽግግር ፍትህ “ተዓማኒ እና ተጎጂዎችን ያማከለ” መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። ቦሬል ይህን ያሉት የፕሪቶሪያ ስምምነት የተፈረመበትን ሁለተኛ ዓመት በማስመልከት በትላንትናው ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት ነው። 

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳም፤  በተመሳሳይ መልኩ ዕለቱን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት አጭር ጹሁፍ ዘክረውታል። ስምምነቱ “የፖለቲካ ሙግቱን ከጦር አውድማ ዘወር በማድረግ”፤ ከፌደራል መንግስት ጋር “በትብብር ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነት ዕድሎችን” መፍጠሩን አቶ ጌታቸው በትላንቱ መልክታቸው አስፍረዋል። 

ሆኖም የስምምነቱ ስኬታማነት የሚመዘነው፤ ጦርነቱ ያስከተላቸውን አወዛጋቢ ጉዳዮች “በመፍታት አቅሙ ብቻ” እንደሆነ አቶ ጌታቸው ሳይገልጹ አላለፉም። በሕገ መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው የትግራይ ክልል ግዛቶች ጉዳይ “አሁንም መፍትሔ አልተበጀላቸውም” ያሉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት፤ ምዕራብ ትግራይ በአማራ ኃይሎች፣ ሰሜን ምዕራብ እና ምስራቃዊ ትግራይ በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ለአባባላቸው በማስረጃነት ጠቅሰዋል። 

“በዚህም ምክንያት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች፤ በተፈናቃዮች መጠለያዎች ውስጥ ሊገመቱ በማይችሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እየማቀቁ ይገኛሉ” ሲሉ ጉዳዩ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል። “የተቀናጀ ጥረት በሌለበት፤ እነዚህን ጉዳዮች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት እና ሰላምን ለማስፈን ማሰብ ቅዠት ይሆናል ቢባል ማጋነን አይሆንም” ሲሉ አቶ ጌታቸው በትላንቱ መልዕክታቸው አስፍረዋል። 

የፕሪቶሪያን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አለማድረግ፤ ለኢትዮጵያ ጸጥታ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሰላም እና ደህንነት ከፍተኛ አንደምታ እንደሚኖረው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አስገንዝበዋል። በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት “ግዴታዎችን እና ቃል ኪዳኖችን” በማክበር ረገድ “ብዙ ስራ ይቀራል” የሚል እምነታቸውን የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በትላንቱ መግለጫቸው አንጸባርቀዋል። 

ስምምነቱን በማስከበር ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት አብዛኛዎቹን ስራዎች ማከናወን እንደሚጠበቅበት ብሊንከን በመግለጫቸው ጠቁመዋል። “በግጭቱ የተፈናቀሉ ሁሉንም ሰዎች በፈቃደኝነት የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃውን እንዲያፋጥን” ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከመከላከያ ሰራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ብሊንከን በዚሁ መግለጫቸው ጥያቄ አቅርበዋል። ተጎጂዎችን ላማከለ የሽግግር ፍትህ እና ለተአማኒ እና አካታች ብሔራዊ ምክክር፤ የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት አሁንም እንዲያረጋግጥ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል። 

ብሊንከን በትላንቱ መግለጫቸው፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶችን ሁሉም ወገኖች በማቆም ልዩነቶቻቸውን በድርድር እንዲፈቱ አሳስበዋል። የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊም፤ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ የሚገኙ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንደሚገባቸው ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቦሬል “በኢትዮጵያ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግዴታዎች መሰረት ሰብአዊ መብቶች ሁልጊዜም ሊከበሩ ይገባል” ብለዋል።  በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ወገኖች እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡት ቦሬል፤ ሂደቱ በተለይ “ለሴቶች እና ለወጣቶች አካታች ሊሆን ይገባል” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)