በወላይታ ሶዶ ነዳጅ ማደያዎች የማይገኘው ቤንዚን፤ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ እንዴት እንደ ልብ ሊገኝ ቻለ?

በናሆም አየለ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ የሆነችው የወላይታ ሶዶ ከተማ፤ በሰባት በሮች እንግዶቿን ትቀበላለች። የህዝብ ትራንስፖርት እና የግል ተሽከርካሪዎችን የሚጠቀሙ ተጓዦች፤ በአረካ፣ ቦዲቲ፣ ኡምቦ እና ገሱባ ከተሞች አድርገው ወደ ወላይታ ሶዶ መግባት ይችላሉ። በጭዳ፣ ሆቢቻ፣ በዴሳ ከተሞች በኩል ያሉ መንገዶችን ለተጓዦች በአማራጭነት ያገለግላሉ።  

ከአዲስ አበባ ከተማ 332 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በወላይታ ሶዶ፤ ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ በዋናነት የሚጠቀሙት በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩትን ባለ ሶስት እግር ታክሲዎችን ሲሆን ሞተር ሳይክልም በነዋሪዎቹ ዘንድ ይዘወተራል። በከተማይቱ ከ12 ሺህ በላይ ባጃጆች እና ሞተር ብስክሌቶች  እንደሚንቀሳቀሱ ከወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የወላይታ ሶዶ ከተማ ደም ስር የሆኑት እነዚህ መጓጓዣዎች በዋነኛነት የሚጠቀሙት ቤንዚን ቢሆንም፤ በአቅርቦት ረገድ ያለው ችግር የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ለከፍተኛ ምሬት ዳርጓል። ላለፈው አንድ ሳምንት በሶዶ ቆይታ ያደረገው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ በከተማይቱ ውስጥ ባሉ የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ ከፍተኛ የቤንዚን እጥረት መኖሩን አስተውሏል። 

ካለፈው ረቡዕ ጥቅምት 20፣ 2017 ጀምሮ ደግሞ፤ የከተማይቱ ነዳጅ ማደያዎች “ቤንዚን የለም” የሚሉ ጉልህ ማስታወቂያዎችን መለጠፋቸውን ታዝቧል። የወላይታ ሶዶ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት፤ የንግድ ኢንስፔክሽን እና ሬጉሌሽን የቡድን መሪ የሆኑት አቶ ፋኑኤል ተርጫ ላለፉት አራት ቀናት በከተማዋ የነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን አለመኖሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።  

በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ያለው፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር “በመጠባበቂያነት” ያስቀመጠው ስድስት ሺህ ሊትር ቤንዚን ብቻ እንደሆነም አቶ ፋኑኤል ተናግረዋል። የከተማይቱ አስተዳደር “በማደያዎች ውስጥ ምንም ቤንዚን የለም። መጠባበቂያ ብዬ ያስቀመጥኩት ብቻ ነው ያለኝ” ቢልም፤ በሶዶ ዋና አውራ ጎዳናዎች ላይ ግን ለግብይት የቀረበ ቤንዚን በብዛት ይታያል።

የቤንዚን ንግዱ ማስታወቂያ ቀለል ያለ ነው። በተለምዶ “ሃይላንድ” ተብሎ በሚጠራው ባለ ሁለት ሊትር የፕላስቲክ ጠርሙስ፤ ድፍርስ ውሀ ጎደል ተደርጎ በአውራ ጎዳናዎች ይቀመጣል። ይህን አይነት የአሸሻጥ ዘዬ፤ በወላይታ ሌሎች ከተሞች እና ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ባሉ ቦታዎች መመልከት የለመደ አሽከርካሪ፤ በአቅራቢያው ቤንዚን ሻጮች እንዳለ ያውቃል። 

ከአራት ዓመት በላይ በወላይታ ሶዶ በባጃጅ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን የሚናገረው መልካሙ በዛብህ፤ ቤንዚን ከነዳጅ ማደያ ከቀዳ መቆየቱን ይናገራል። “ብዙ ጊዜ የለም ነው የምንባለው። ‘አለ’ ተብሎ ስንሄድም፤ ወረፋ በጣም አለ። ለሊት 10 ሰዓት ማደያ በር ላይ ተሰልፈን፤ ከቀኑ አራት ወይንም አምስት ሰአት ላይ ነው ቀድተን የምንወጣው” ይላል መልካሙ። 

ዕድለኛ ባልሆነባቸው አንዳንድ ቀናት፤ ተሰልፎ ውሎ “አለቀ ወይም ማሽን ተበላሸ” ተብሎ ነዳጅ ሳይቀዳ የሚመለስባቸው ቀናት እንዳለም የባጃጅ አሽከርካሪው ይናገራል። መልካሙ በሶዶ ከተማ ላለው የቤንዚን እጥረት ዋነኛ ተጠያቂ የሚያደርገው ነዳጅ ማደያዎችን ነው። 

የነዳጅ ማደያዎቹ ያላቸውን ቤንዚን በአግባቡ ለአሽከርካሪው ከማቅረብ ይልቅ፤ “ለህገወጥ ቸርቻሪዎች መሸጣቸው” ችግሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ አባብሶታል የሚል እምነት አለው። ላለፉት ስድስት ዓመታት በወላይታ ሶዶ በሞተር ሳይክል የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው፤ ተካልኝ በቀለም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራል። 

ወደ ከተማው የሚገባው ቤንዚን፤ በአግባቡ ለተጠቃሚው ቢቀርብ እጥረት እንደማይኖር የሞተር ሳይክል አሽከርካሪው  ይሟገታል። “ማደያዎች ማታ ማታ በጀሪካን እና በታንከር ለቸርቻሪዎች ቤንዚኑን ይሸጣሉ” የሚለው ተካልኝ፤ ቤንዚን ከእነርሱ ላይ በሊትር በ200 ብር ሂሳብ ገዝቶ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ይናገራል።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለፈው መስከረም ወር ባወጣው የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ፤ አንድ ሊትር ቤንዚን በአዲስ አበባ ከተማ የሚሸጥበት ዋጋ 91 ብር ከ14 ሳንቲም ነው። በዚህ ላይ በመመስረት የወጣው ታሪፍ፤ አንድ ሊትር ቤንዚን በወላይታ ሶዶ የሚሸጥበት ዋጋ 92 ብር ከ45 ሳንቲም እንዲሆን ያደረገ ነበር። 

ይህ እየተተገበረ እንዳልሆነ የሚገልጸው ተካልኝ፤ እንደ እርሱ ያሉ አሽከርካሪዎች ያለባቸውን ችግር በዚህ መልኩ ያስረዳል።    “ቤንዚን በውድ ስለምንገዛ፤ ለአጭር መንገድ የምንጠይቀው [ትንሹ ሂሳብ] 30 ብር ነው። ሰው ደግሞ ‘ውድ ነው’ እያለ ከእኛ እየሸሸ ነው። ስራ የለም። ወጣቶች ነን። ስራ እዚህ እያለ፤ መስራት ካልቻልን ምን እናደርጋለን? በወጣትነታችን መከላከያ እንሂድ እንዴ? መስራት አልቻልንም” ይላል በምሬት። 

በወላይታ ሶዶ ከተማ ያለው የዳሎል የነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በረከት ብርሃኑ ግን የአሽከርካሪዎቹን ውንጀላ አይቀበሉም። በከተማይቱ ያሉ ማደያዎች ቤንዚን እንዲገባላቸው ሲያዙ፤ ከከተማ ጀምሮ እስከ ክልል ያለው የንግድ እና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት መዋቅር እንደሚያውቅ እንዲሁም ቁጥጥር እንደሚያደርግበት ያስረዳሉ።   

ቤንዚኑ በነዳጅ ማደያ ከደረሰ በኋላ፤ ሽያጭ የሚከናወነው የከተማይቱ የፖሊስ አባላት ባሉበት ጭምር እንደሆነም ይገልጻሉ። “ይሄ ሁሉ ቁጥጥር ባለበት፤ ለቸርቻሪ በውድ እንሽጥ ብንልስ፤ እንዴት አድርገን ነው የምንሸጠው?” ሲሉም ይጠይቃሉ። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት ቤንዚን ቸርቻሪዎች፤ ለእነርሱ የሚሸጡላቸው ሰዎች “ቤንዚኑን የሚያመጡት ከነዳጅ ማደያዎች ነው” ባይ ናቸው። 

የቤንዚን የችርቻሮ ንግድ ምንጭ የሆኑት ነዳጅ ማደያዎች፤ በሶዶ ከተማ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ባሉ የወረዳ ከተሞች ጭምር የሚገኙ መሆናቸውንም እኚሁ ሻጮች ያብራራሉ። በወላይታ ሶዶ ከተማ ካሉ 11 የነዳጅ ማደያዎች፤ መንግስት በተመነው ዋጋ ገዝተው ለእነርሱ አትርፈው የሚሸጡ እንዳሉም ያክላሉ። 

ሶስቱም የቤንዚን ቸርቻሪዎች፤ አንድ ሊትር ቤንዚን ከ130 እስከ 150 ብር እንደሚረከቡ ገልጸዋል። ይህንኑ ለተጠቃሚዎች  የሚሸጡት ከ180 እስከ 200 ብር ባለው ዋጋ እንደሆነም ይናገራሉ። ቤንዚን “ከማደያ እያወጡ የሚሸጡልን አሉ” የሚለውን የቸርቻሪዎቹን ክስ፤ በወላይታ ሶዶ የሚገኘው የቶታል ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አህመዲን ከድር ያጣጥሉታል።  

“በሶዶ ከተማ ዙሪያ ወዳሉ የወረዳ ከተሞች ቤንዚን ተጭኖ በዚህ ስለሚያልፍ ከመሸበት እዚሁ ሊያደር ይችላል። ሰዎች ማደያ ግቢ ውስጥ የነዳጅ ቦቴ ቆሞ ሲያዩ ነዳጅ እየገባልን ይመስላቸዋል። ‘ገብቷል እኮ፤ ማታ ሊቸረችሩት ነው፤ የማይሸጡልን’ ይላሉ። እውነታው ግን እኛ በታሪፍ መሰረት ነው ለተጠቃሚው የምናሰራጨው” ሲሉ አቶ አህመዲን የነዳጅ ማደያዎችን አሰራር ያስረዳሉ።

ሁለቱ የነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጆች፤ በወላይታ ሶዶ ከተማ ያለው የቤንዚን እጥረት ዋነኛው ምክንያት፤ ከተማይቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ መሆኑዋን ተከትሎ የመጣው የቤንዚን ፍላጎት መጨመር ነው። ባለፉት ዓመታት ከነበሩት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር፤ በአሁኑ ወቅት ከፍ ያለ የቤንዚን ተጠቃሚ መኪኖች ቁጥር መኖሩንም ስራ አስኪያጆቹ ይገልጻሉ። 

በስድስት ዞኖች እና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ከሁለት ዓመት በፊት የተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ የወላይታ ሶዶ ከተማን ዋነኛ መቀመጫ አድርጎ የመረጠው በነሐሴ 2015 ዓ.ም. ነበር። ከተማዋ የክልሉ የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ መሆኑዋን ተከትሎ፤ “የቤንዚን ፍላጎት ጨምሯል” የሚለውን ገለጻ የወላይታ ከተማ አስተዳድር የንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የንግድ ኢንስፔክሽን እና ሬጉሌሽን የቡድን መሪው አቶ ፋኑኤል ይስማሙበታል።  

በዚህም ምክንያት ለከተማዋ የሚሰራጨው የቤንዚን ኮታ እንዲጨምር፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ለወላይታ ዞን ጥያቄ ማቅረቡን የቡድን መሪው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በከተማው የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የነዳጅ የችርቻሮ ንግድ ለማስቆምም፤ የከተማ አስተዳደሩ አዲስ ደንብ እያዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ደንቡ ህገወጥ ቸርቻሪዎቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እና የእስር ቅጣት የሚጥል መሆኑን አቶ ፋኑኤል አብራርተዋል። አሁን በስራ ላይ ያለው መመሪያ፤ ከቸርቻሪዎቹ ላይ ቤንዚኑ “እንዲወረስ” የሚፈቅድ ብቻ መሆኑ በከተማው ህገወጥ ንግድ እንዲስፋፋ አድርጎ መቆየቱን አመልክተዋል። የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ባደረገው የዘመቻ ስራ፤ ከስድስት ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ከህገወጥ ቸርቻሪዎች መውረሱን አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)