በቤርሳቤህ ገብረ
የስራ ዘመናቸውን ከአራት ወራት ገደማ በፊት አጠናቅቀው የተሰናበቱትን የህዝብ ዋና ዕንባ ጠባቂ የሚተኩ ዕጩዎችን የሚያቀርብ ኮሚቴ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋቋመ። በኮሚቴው ውስጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የጌዲኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌህዴድ) የፓርላማ ተመራጮች እንዲካተቱ ተደርጓል።
ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፤ በህግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈጻሚ አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ፤ የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን የማድረግ ዋና ዓላማ ያለው ነው። ተቋሙ የቀረቡለትን የአስተዳደር በደል አቤቱታዎች መሰረት በማድረግ፤ “ስልታዊ ምርመራ” የማካሄድ ኃላፊነትም በአዋጅ ተሰጥቶታል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ በተጨማሪ ስምንት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያሉትን ይህን ተቋም ላለፉት ስድስት ዓመታት በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ ናቸው። ዶ/ር እንዳለ በድጋሚ ተሹመው፤ ለተጨማሪ ስድስት ዓመታት በኃላፊነት መቀጠል የሚችሉበትን ዕድል የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ቢሰጣቸውም፤ ከዋና እንባ ጠባቂነታቸው መሰናበትን መርጠዋል።
ያገለገሉበት የስራ ዘመን “ከበቂ በላይ” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ዶ/ር እንዳለ፤ “አሁን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ እና ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ለመስራት አስቸጋሪ” ስለሆነ በኃላፊነት ላለመቀጠል መወሰናቸውን አስረድተዋል። ለስራቸው ይከፈላቸው የነበረው ደመወዝ አነስተኛ መሆን፤ በዋና እንባ ጠባቂነት ለሁለተኛ ዙር ላለመሾም ካስወሰኗቸው ምክንያቶች መካከል እንደሚገኝበትም ገልጸዋል።
ዶ/ር እንዳለ የህዝብ ዋና እንባ ጠባቂ ሆነው ከመሾማቸው አስቀድሞ፤ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሰርተዋል። በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው ግሼ ራቤል ወረዳን በመወከልም፤ ከ1997 እስከ 2002 ድረስ የፓርላማ አባል ነበሩ። እርሳቸውን በመተካት በአሁኑ ወቅት ተጠባባቂ ዋና እንባ ጠባቂ በመሆን እያገለገሉ ያሉት አቶ ደነቀ ሻንቆ ናቸው።
አቶ ደነቀ ከተወከሉበት የዋና እንባ ጠባቂነት በተጨማሪ በተቋሙ ሊኖሩ የሚገባቸውን የሶስት ምክትል እንባ ጠባቂዎችን ስራ ደርበው እየሰሩ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት የተሻሻለው የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ መስሪያ ቤቱ ካሉት ዋና እና ምክትል ዕንባ ጠባቂዎች በተጨማሪ የሴቶች፣ የህጻናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ዕንባ ጠባቂ ሊኖረው እንደሚገባ ይደነግጋል።
የማቋቋሚያ አዋጁ የልዩ ልዩ ዘርፍ ሌሎች ዕንባ ጠባቂዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ያስቀምጣል። በእነዚህ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተጓደሉ የእንባ ጠባቂ አመራሮችን ለመሾም፤ የተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ አባላት አቋቁሞ ነበር። ኮሚቴው ይህንን ስራውን ከማጠናቀቁ በፊት፤ የዋና እንባ ጠባቂው የኃላፊነት ዘመን አብቅቷል።
የተወካዮች ምክር ቤት በተሰናበቱት ዋና እንባ ጠባቂ ምትክ ዕጩ የሚያቀርብ ሌላ ኮሚቴ ከማቋቋም ይልቅ፤ ባለፈው መጋቢት ወር የተቋቋመው ኮሚቴ አዲሱን ስራ ደርቦ እንዲሰራ አድርጓል። ከዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው፤ የኮሚቴው አባላት “ካላቸው ልምድ አንጻር የዋና ዕንባ ጠባቂውንም ሹመት አብረው ቢሰሩ የተሻለ ነው” በሚል ምክንያት መሆኑን አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 26፤ 2017 በተካሄደ የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
በዚህ መሰረት በዋና ዕንባ ጠባቂ ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ውስጥ ሰባት የፓርላማ አባላት እንዲካተቱ ተደርጓል። ከኮሚቴ አባላቱ መካከል፤ የኢዜማው አቶ ባርጠማ ፍቃዱ እና የጌህዴዱ አቶ ብርሃኑ ጎበና ይገኙበታል። የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የፓርላማ ተወካዮች የሆኑት አቶ እውነቱ አለነ፣ አቶ ኢሳ ቦሩ፣ ወ/ሮ ዘሀራ ቢፍቱ፣ አቶ ከድር አደም እና አቶ አኔሳ ሚልኮም፤ የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው አባላት ሆነዋል።
ይህ ኮሚቴ በህዝብ ድምጽ መሰረት ተተኪ እጩ የመመልመል ሂደት የመምራት ኃላፊነት የተጣለበት ነው። በዋና እንባ ጠባቂነት በዕጩነት ለመቅረብ መሟላት ከሚገባቸው መስፈርቶች መካከል፤ ከፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ መሆን፣ በታታሪነት፣ በታማኝነት እና በስነ-ምግባር መልካም ስም ማትረፍ እንዲሁም ከደንብ መተላለፍ ውጪ በሌላ የወንጀል ጥፋት ተከሶ ፍርደኛ አለመሆን የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)