በተስፋለም ወልደየስ
የገንዘብ ሚኒስቴር 900 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የመንግስት ዕዳ ሰነድ (ቦንድ) እንዲያወጣ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። ገንዘቡ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልከፈሉትን ዕዳ ለመክፈል እና ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል ነው።
ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 26፤ 2017 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው ይህ አዋጅ፤ “የመንግስት እዳ ሰነድ” የሚል ስያሜን የያዘ ነው። አዋጁን ማውጣት ያስፈለገው፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለበት “ከፍተኛ ዕዳ” በባንኩ የፋይናንስ ገጽታ ላይ “ከፍተኛ ተጽዕኖ ስላስከተለ” መሆኑ በረቂቅ ህጉ ላይ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግስት ለልማት ድርጅቶች ካበደረው ውስጥ እስካሁን ያልተሰበሰበው የገንዘብ መጠን፤ ከ845.3 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል። የልማት ድርጅቶቹ ብድሩን ከመንግስታዊው ባንክ የወሰዱት፤ ለተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ነው።
ከመንግስት የልማት ድርጅቶቹ ውስጥ ያልተከፈለ ከፍተኛ ብድር ያለበት፤ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ነው። ኮርፖሬሽኑ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መክፈል ይገባው የነበረው ብድር ከእነ ወለዱ 191.79 ቢሊዮን ብር እንደሆነ አዋጁን ለማብራራት በቀረበ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል።
ከመንግስት ተቋሟት መካከል ባልተከፈለ ከፍተኛ የብድር መጠን ሁለተኛውን ቦታ የያዘው፤ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ነው። የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በሁለት ዙር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው የገንዘብ መጠን ከእነ ወለዱ 110.68 ቢሊዮን ብር እንደሆነ በአዋጅ ማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።
እንደ ስኳር ኮርፖሬሽን ሁሉ በሁለት ዙሮች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ የተበደረው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፤ ባልተከፈለ የከፍተኛ ብድር መጠን ሶስተኛውን ቦታ ይዟል። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተበደረው የገንዘብ መጠን ከእነ ወለዱ ሲሰላ 80.17 ቢሊዮን ብር ነው።
ከእነዚህ ሶስት የመንግስት ልማት ድርጅቶች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩኘ እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች የተባሉት የመንግስት ተቋማትም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መበደራቸውን ለፓርላማ የቀረበው ሰነድ ዘርዝሯል። የልማት ድርጅቶቹ በዚህ መልክ የተበደሩትን ገንዘብ ለሜጋ ፕሮጀክቶች ቢያውሉትም፤ ፕሮጀክቶቹ “ከጥናት ጀምሮ በርካታ የተወሳሰበ ችግር ያለባቸው” መሆኑን የአዋጅ ማብራሪያ ሰነዱ አትቷል።
በዚህ ምክንያት የመንግስት ልማት ድርጅቶቹ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ዕዳቸውን “ለመክፈል ከማይችሉበት ደረጃ ላይ” በመድረሳቸው፤ የፌደራል መንግስት ለችግሩ መፍትሔ የሚሰጥ ኮርፖሬሽን በ2013 ዓ.ም. ማቋቋሙን ማብራሪያው አስታውሷል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ የተቋቋመው ይህ መስሪያ ቤት፤ የዕዳ እና የሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሚል ስያሜ ያለው ነው።
ይኸው ኮርፖሬሽን የመንግስት የልማት ድርጅቶች በዕዳ ጫና ምክንያት ያጋጠማቸውን ችግር በማቃለል፤ አትራፊ ሆነው ስራቸውን መቀጠል እንዲችሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ብድር እንዲረከብ ተደርጓል። ኮርፖሬሽኑ ከኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ የሚመደብለትን ካፒታል፣ ከንግድ ስራ እንቅስቃሴ ከሚያገኘው ገቢ እንዲሁም ከሌሎች ምንጮች የሚመደብለትን ገንዘብ በመጠቀም፤ የተረከባቸውን ዕዳዎች እንዲከፍል ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር።
“ኮርፖሬሽኑ በታቀደው መሰረት ለዕዳ ክፍያ ሊውል የሚችለውን ገንዘብ ባለማግኘቱ ኃላፊነቱን ሊወጣ ካለመቻሉም በላይ በብድሩ ገንዘብ ላይ ሊከፈል የሚገባው ወለድ እየተጠራቀመ ሄዷል። በዚህም ምክንያት ያልተከፈለው ከፍተኛ ዕዳ፤ ብድሩን ለመንግስት የልማት ድርጅቶች በሰጠው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ ገጽታ ላይ አሉታዊ ውጤትን በማስከተሉ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ይሆናል” ሲል “የመንግስት እዳ ሰነድ” አዋጅን ለማብራራት የቀረበው ሰነድ ያስረዳል።
በዚህም መሰረት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ መንግስት ተረክቦ፤ ዕዳው እንዲከፈል ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አዋጁ አመልክቷል። የዕዳው ክፍያ የሚፈጸመው በመንግስት ዕዳ ሰነድ (ቦንድ) እንደሆነም በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። የመንግስት የዕዳ ሰነዶቹ የሶስት ዓመት የችሮታ ጊዜ ያላቸው ሲሆን በ10 ዓመታት ጊዜ ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው።
የገንዘብ ሚኒስቴር በአዋጁ መሰረት የሚያወጣው 900 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ቦንድ እንደሆነ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። ሚኒስቴሩ ከቦንድ ሽያጩ ከሚያገኘው ገንዘብ ውስጥ 846 ቢሊዮን ብር ያህሉን ማዋል ያለበት፤ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ላልከፈሉት ዕዳ እንደሆነ አዋጁ ደንግጓል። ቀሪው 54.6 ቢሊዮን ብር፤ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ክፍያ መዋል እንዳለበትም አዋጁ ያዝዛል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ የንግድ ባንክ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ቢሆንም፤ የተፈቀደለት ካፒታል አራት ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ አዋጁን ለማብራራት የቀረበው ሰነድ አስታውሷል። “በመሆኑም ባንኩ በገበያው ውስጥ ያለውን ድርሻ ይዞ እንዲቀጥል ለማድረግ ደረጃ በደረጃ የተከፈለውን ካፒታል ማሳደግ አስፈላጊ ይሆናል” ሲል ማብራሪያው አክሏል።
“የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል ማሳደግ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ ባይሆንም መንግስት፤ ለካፒታል ማሳደጊያ የሚውለውን ሀብት በጥሬ ገንዘብ መልክ ለመመደብ የሚያስችል ሀብት በአሁኑ ጊዜ የሌለው በመሆኑ፤ የካፒታል ማሳደጊያውን በመንግስት ዕዳ ሰነድ መልክ መክፈል አማራጭ የሌለው ሆኖ ተገኝቷል” ሲልም የአዋጅ ማብራሪያው ያስረዳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)