የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ትኩረት የሚያሻው” “የገቢ እጥረት” እንደገጠመው ገለጸ  

በናሆም አየለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ የሰበሰበው ገቢ፤ በእቅድ ይዞት ከነበረው በ10 ቢሊየን ብር ያነሰ መሆኑን ገለጸ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከውጭ እርዳታ እና ብድር የተገኘው ገቢም፤ ከታቀደው ከግማሽ በታች መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

በከተማይቱ እየተተገበሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ሆነው ሳለ፤ በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ መቀነሱ “ትኩረት የሚያሻው” መሆኑ ተገልጿል። ይህ የተገለጸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት አመት አንደኛ የሩብ አመት የስራ አፈጻጸሙን ትላንት ማክሰኞ ህዳር 3፤ 2017 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ በገመገመበት ወቅት ነው።  

በዚህ የግምገማ መድረክ ላይ የአስፈጻሚ አካላት የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ  አጠር ባለ መልኩ ቀርቧል። በአቶ አደም በቀረበው ሪፖርት ላይ “በትክክል ያልቀረቡ” እና “ያልተካተቱ ስራዎች አሉ” ያሉ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ አመራሮች፤ ስላከናወኗቸው ስራዎች ሰፊ ሰዓት ወስደው ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

ፎቶ፦ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ

በስራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ላይ ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል የዕለቱ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ የነበረው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢ ሁኔታ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮ በጀት አመት ለመሰብሰብ ያቀደው ጠቅላላ የገቢ መጠን 230 ቢሊየን ብር ነው። የከተማ አስተዳደሩ ይህን ገንዘብ የሚሰበስበው፤ ክታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ ከማዘጋጃ ቤት ገቢዎች፣ ከመንገድ ፈንድ እንዲሁም ከውጭ እርዳታ እና ብድር እንደሆነ በዘንድሮ በጀት አዋጅ ላይ ሰፍሯል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ 54.9 ቢሊየን ብር እንደነበር በትላንቱ የግምገማ መድረክ ላይ ተጠቅሷል። ሆኖም የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ጊዜያት ውስጥ ማሳካት የቻለው የእቅዱን 83.3 በመቶ እንደሆነ አቶ አደም ተናግረዋል። 

“ይህ እንግዲህ ከባለፈው አመት ጋር ሲታይ ወደ 12 ቢሊየን ብር አድጓል። ከእቅዳችን አንጻር ሲታይ ደግሞ 10 ቢሊየን ብር ያህል ልዩነት አለው” ሲሉ የፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊው አብራርተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዝቅ ያለ ገቢ ለመሰብሰቡ በምክንያትነት ከተጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ፤ የውጭ እርዳታ እና ብድር መጠን ማነስ ነው።

“የከተማውን አጠቃላይ የገቢ አቅም መነሻ አድርገን ነው ያቀድነው። እቅዳችንን ደግሞ ማሳካት አለብን። ይህ ደግሞ ገቢ የምትሰበስቡ ሴክተሮችን በአጠቃላይ  ይመለከታችኋል። በዚህ ሩብ አመት የታየው የገቢ እጥረት፤ በሚቀጥለው መሟላት መቻል አለበት”

– የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ

የከተማ አስተዳደሩ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከውጭ ብድር ለማግኘት ያቀደው የገንዘብ መጠን 3.3 ቢሊዮን ብር ነው። በ2017 በጀት ዓመት ከውጭ እርዳታ ይገኛል ተብሎ በእቅድ የተያዘው 490.6 ሚሊዮን ብር እንደሆነ በከተማይቱ የበጀት አዋጅ ላይ ተዘርዝሯል። ሆኖም የከተማይቱ አስተዳደር ከእነዚህ ሁለት ምንጮች ባለፉት ሶስት ወራት ለማግኘት ካሰበው ማሳካት የቻለው “ከ50 በመቶ በታች መሆኑ” በትላንቱ ስብሰባ ላይ ይፋ ተደርጓል።

በገቢ አሰባሰብ ላይ የታየው አፈጻጸም፤ የትላንትናውን የግምገማ መድረክ በመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተተችቷል። “የከተማውን አጠቃላይ የገቢ አቅም መነሻ አድርገን ነው ያቀድነው። እቅዳችንን ደግሞ ማሳካት አለብን። ይህ ደግሞ ገቢ የምትሰበስቡ ሴክተሮችን በአጠቃላይ  ይመለከታችኋል። በዚህ ሩብ አመት የታየው የገቢ እጥረት፤ በሚቀጥለው መሟላት መቻል አለበት” ሲሉ ከንቲባ አዳነች በስብሰባው ለተገኙ አመራሮች ትዕዛዝ ሰጥተዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይም፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከከንቲባይቱ ጋር የተመሳሳለ ሃሳብ አንጸባርቀዋል። በዘንድሮው በጀት አመት ሶስት ወራት ከእቅድ አንጻር ዝቅ ያለ ገቢ መሰብሰቡ፤ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች የገንዘብ እጥረት እንዲገጥማቸው ሊያደርግ ይችላል የሚለውን ስጋታቸውንም ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል። 

ፎቶ፦ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ

“የኮሪደር ፕሮጀክቶቻችን ትልቅ ሀብት የሚፈልጉ ናቸው።  አምና ካቀድነው በላይ ግዙፍ እቅድ ስለሆነ የያዝነው፤ ከወረዳ እስከ ማዕከል ድረስ ያሉ የግብረ ኃይል አባላትም፣ ራሱ ተቋሙም ንቅናቄ አድርገን ካላስተካከልነው ሊፈትነን ይችላል” ሲሉ ገቢን በማሳደግ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮን ጨምሮ ሌሎችም አካላት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ጃንጥራር አሳስበዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች በእቅድ ከተያዘላቸው “ዝቅ ያለ” ገቢ መሰብሰባቸው ሊሻሻል እንደሚገባም በትላንትናው የግምገማ መድረክ ላይ ተነስቷል። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ክፍለ ከተሞች የሰበሰቡት ገቢ፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ100 ሚሊዮን ብር የቀነሰ መሆኑም ተገልጿል።

ከተማይቱ የምትሰበስበውን ገቢ ለማሻሻል፤ እንደ መርካቶ ካሉ ትልልቅ የገበያ ስፍራዎች የሚሰበሰበው ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ በትላንቱ የግምገማ መድረክ ላይ በመፍትሔነት ቀርቧል። በመርካቶ ገበያ ያሉ ነጋዴዎች፣ አስመጪዎች፣ አምራች እና አከፋፋዮች በደረሰኝ እንዲገበያዩ ለማድረግ “የንቅናቄ ስራ” መጀመሩም ተገልጿል። የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ጋር በተያያዘ “የቁጥጥር ስራ መስራት” ሲጀምር “አሉባልታዎች” በሰፊው መሰራጨታቸውን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር፤ በመርካቶ የተጀመረው እንቅስቃሴ “ለምትሸጡት እቃ ደረሰኝ ስጡ” የሚል እንጂ ሌላ ዓላማ ያነገበ እንዳልሆነ አስተባብለዋል።

“ በመርካቶ ‘ሊታሸግብህ ነው’ ፣ ‘ከንግድ እንድትወጣ ሊደረግ ነው’፣ ‘ሊወረስብህ ነው’ የሚሉ አሉባልታዎች በሰፊው የሚነዙበት ሁኔታ ይታያል። ህጋዊ የሆነውን ከህገ ወጡ ጋር እየቀላቀሉ መሄድ አይቻልም።

– የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ

“አንድ ህጋዊ የሆነ የመንግስት አስፈጻሚ ወደ መርካቶ ገብቶ ይህንን ስራ ለመስራት በሚሞክርበት ጊዜ፤ ‘ሊታሸግብህ ነው’ ፣ ‘ከንግድ እንድትወጣ ሊደረግ ነው’፣ ‘ሊወረስብህ ነው’ የሚሉ አሉባልታዎች በሰፊው የሚነዙበት ሁኔታ ይታያል። ህጋዊ የሆነውን ከህገ ወጡ ጋር እየቀላቀሉ መሄድ አይቻልም። ህጋዊ እስከሆነ፣ ደረሰኝ እስከ ቆረጠ ድረስ ስራውን ይሰራል። ንግዱን በተገቢው መንገድ መምራት ይችላል” ብለዋል አቶ ጃንጥራር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)