በቤርሳቤህ ገብረ
ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ከፕሬዝዳንትነታቸው ለተሰናበቱት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፤ በኃላፊነታቸው ላይ ሳሉ ላከናወኗቸው ስራዎች የምስጋና መርሃ ግብር ሊደረግላቸው ነው። ከነገ በስቲያ አርብ ህዳር 6፤ 2017 የሚደረገውን ይህን መርሃ ግብር ያዘጋጁት በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ሰባት ሀገር በቀል እና አለም አቀፍ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መሆናቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ስልጣናቸውን ለተተኪያቸው ታዬ አጽቀ ስላሴ ያስረከቡት፤ የስድስት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ከመገባደዱ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ ነበር። የቀድሟዋ ፕሬዝዳንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ፤ የመክፈቻ ንግግር እንዲያቀርቡ አስቀድሞ ተይዞ የነበረው መርሃ ግብር ተሰርዞ በምትኩ አምባሳደር ታዬ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
በፌደራል መንግስት ደረጃ ይፋዊ የሽኝት ስነ ስርዓት ላልተደረገላቸው ሳህለ ወርቅ፤ የምስጋና መርሃ ግብር የተዘጋጀው በአዲስ አበባው ሸራተን አዲስ ሆቴል ነው። የምስጋና መርሃ ግብሩ ዋና አላማ የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት በሴቶች አመራር ረገድ ላከናወኗቸው ስራዎች በሴቶች አማካኝነት ምስጋና ለማቅረብ መሆኑን ፕሮግራሙን የማዘጋጀት ኃላፊነት የወሰደው የመቅዲ ፕሮዳክሽን ኦፕሬሽን ማናጀር አቶ በሃይሉ ተከተል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በዚሁ የምስጋና መርሃ ግብር ላይ 200 ገደማ የሚሆኑ ታዳሚዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት አቶ በሃይሉ፤ ከተጋባዦች ውስጥ ሚኒስትሮች እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል። ከሚኒስትሮች እና የስራ ኃላፊዎች በተጨማሪ ለቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች፣ የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች አመራሮች እና ታዋቂ ሰዎች በመርሃ ግብሩ ላይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ በሃይሉ አመልክተዋል።
ለግማሽ ቀን በሚቆየው በዚህ መርሃ ግብር ላይ ንግግሮች እና ሙዚቃዎች ይቀርባሉ ተብሏል። በውጭ ግንኙነት ስራ 30 ዓመታት ልምድ ያላቸው አምባሳደር ሳህለ ወርቅ፤ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በመተካት የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ጥቅምት 11፤ 2011 ነበር።
በብሔራዊ፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የካበተ የዲፕሎማሲ ልምድ ያላቸው ሳህለ ወርቅ፤ በፈረንሳይ፣ በጅቡቲ እና በሴኔጋል የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው የሰሩት ሳህለ ወርቅ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የተለያዩ የስራ ክፍሎችን በኃላፊነት መርተዋል።
አምባሳደር ሳህለ ወርቅ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት (ተመድ) በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ለነበረው የተቀናጀ የሰላም ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና ልዩ መልዕክተኛም ነበሩ። የተመድ የቀድሞው ዋና ጸሀፊ በነበሩት ባንኪሙን አማካኝነት የመንግስታቱ ድርጅት ጽህፈት ቤትን በዳይሬክተር ጄነራልነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው፤ ተልዕኳቸውን በአጥጋቢ ሁኔታ ተወጥተዋል።
ሳህለ ወርቅ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሆነው ከመሾማቸው አስቀድሞ፤ የአሁኑ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልእከተኛ አድርገው ሾማቸው ነበር። ከልዩ መልዕክተኝነታቸው በተጨማሪ በዋና ጸሃፊው ስር የሚመራውን የተመድ የአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤትም በበላይነት ሲመሩ ቆይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)