በ2017 ሩብ ዓመት ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ለስራ ወደ ውጭ ሀገራት ተልከዋል?

በቤርሳቤህ ገብረ

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ካለፈው ሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ወራት በውጭ ሀገራት ለስራ ሊያሰማራቸው ከነበሩ 140 ሺህ ዜጎች ውስጥ ማሳካት የቻለው የእቅዱን 62 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታወቀ። በሊባኖስ ለስራ የተሰማሩ ዜጎችን ከጉዳት ለመታደግ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ ቢቀርብለትም፤ አጥጋቢ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ጥያቄውን ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ህዳር 4፤ 2017 በተካሄደ ስብሰባ ላይ ያቀረበው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። ቋሚ ኮሚቴው የትላንት በስቲያውን ስብሰባ የጠራው፤ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን የ2017 እቅድ እና የሩብ አመት የስራ አፈጻጸምን ለመገምገም ነበር። 

በዚሁ ስብሰባ ላይ የሚመሩትን መስሪያ ቤት የሶስት ወራት አፈጻጸም ያቀረቡት የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን በተመለከተ ጥቅል አሃዞችን በሪፖርታቸው አካትተዋል። ወደ ውጭ ለስራ የሚላኩ ዜጎችን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በዘንድሮ በጀት ዓመት ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ ለመላክ ያቀደው 700 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለ2017 የያዘው ይህ እቅድ፤ ባለፈው በጀት አመት ካሳካው አፈጻጻም እጥፍ በላይ ነው። በ2016 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ የተላኩ ዜጎች ብዛት 332 ሺህ እንደነበር ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት ሩብ ዓመት፤ ሚኒስቴሩ በውጭ ሀገራት ለስራ ያሰማራቸው ኢትዮጵያውያን 87,067 እንደሆኑ ሙፈሪያት ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን በህጋዊ መንገድ ለመቀበል፤ ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሰሩ ያሉ ስድስት የመካከለኛው ምስራቅ እና ሁለት የአውሮፓ ሀገራት መሆናቸውን ሚኒስትሯ አመልክተዋል። 

እነዚህ ሀገራት “የሰለጠኑ” (skilled) እና “በከፊል የሰለጠኑ” (semi skilled) ሰራተኞችን ከኢትዮጵያ እንደሚፈልጉ የጠቆሙት ሙፈሪያት፤ በጤና፣ በምህንድስና፣ በአርክቴክቸር፣ በሆቴል እና መስተንግዶ ዘርፎች፣ በኤሌክትሪክ እና ቧንቧ ስራዎች እንደዚሁም የጥበቃ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ፍላጎቶች እንዳሉ አብራርተዋል። በጤናው ዘርፍ፤ በህክምና ተቋማት የሚሰማሩ እና በቤት ውስጥ እንክብካቤ የሚያደርጉ ነርሶችን ከኢትዮጵያ የመውሰድ ፍላጎቶች እንዳሉ ሙፈሪያት ገልጸዋል። 

በጤናው እና ምህንድስና ዘርፍ ያሉ ፍላጎቶች ሆኖም ወደ ተግባር ለመቀየር፤ በሀገራቱም እና በኢትዮጵያ በኩል “መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች” እንዳሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። መፈሪያት “መታለፍ የማይችሉ” ሲሉ ከጠቀሷቸው ቅደመ ሁኔታዎች አንዱ፤ ዓለም አቀፍ እውቅና (certification) የማግኘት ጉዳይ ነው።   

“እነዚህ [ሙያዎች] በአለም አቀፍ ደረጃ አውቅና ያገኙ ትልልቅ ተቋማትን ይፈልጉ ነበር።  የእኛ ድጋፍ ታክሎበት ዘንድሮ በሩብ ዓመቱ በግል ዘርፉ የተደረገው፤ ይህን ሰርተፊኬት ለመስጠት ሚያስችል ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ዝግጅት ነው። ስለዚህ ከጤና አንጻር ከዚህ በኋላ መላክ ለምንፈልገው ሰው የሚገጥመን ችግር አይኖርም ማለት ነው” ሲሉ ሚኒስትሯ አስረድተዋል። 

በዚህ ረገድ ከግሉ ዘርፍ በተጨማሪ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት እየተሰራ ያለ ስራ እንዳለ ሙፈሪያት ጠቅሰዋል። በምህንድስና እና በብየዳ ሙያ በኢትዮጵያ ባሉ ደረጃዎች “መሄድ እንደሚቻል” የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በትራንስፖርት እና በጥበቃ ሰራተኝነት ከሚሰማሩ ዜጎች ጋር በተያያዘ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። 

“የዝግጅት ስራዎች ከተጀመረባቸው ውስጥ መንጃ ፈቃድን አለም አቀፋዊ ማድረግ አንዱ ነው። ትራንስፖርት ማኔጅመንት ላይ የተሰማሩ ሙያተኞችን መላክ ላይ የተጀመረ ስራ አለ። በከፊል የሰለጠነ ከሚባለው ውስጥ ሲቪል ለሆነ አገልግሎት፤ የገበያ አዳራሾች (ሞሎች) አካባቢ ለሚኖሩ ጥበቃዎች ባለሙያ ይፈለጋል። እዚያም አካባቢ ለመላክ የሚያስችል ዝግጅት በእኛ በኩል ተደርጓል” ብለዋል ሙፈሪያት።  

ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት በኩል ኢትዮጵያውያን መሃንዲሶችን፣ አርክቴክቶችን፣ የኤሌክትሪክ እና የቧንቧ ሰራተኞችን የመቅጠር ፍላጎት እንዳለ የጠቆሙት የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ፤ በኳታር እና ኩዌት በሆቴል እና መስተንግዶ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን ለመውሰድ ጥያቄዎች መቅረባቸውን ዘርዝረዋል። ኢትዮጵያውያን ዜጎችን በውጭ ሀገራት በስራ ላይ የሚሰማሩት፤ በመንግስት ለመንግስት፣ በመንግስት እና በኩባንያ እንዲሁም በኩባንያ እና ኩባንያ መካከል በሚደረጉ ስምምነቶች አማካኝነት መሆኑንም አክለዋል።

“ከመንግስት እና ኩባንያ ስምምነት አንጻር የጀመርነው [ስራ አለ]። የስልጠና፣ የዝግጅት ሂደት ላይ ያለው አንዱ የኖርዌይ እና የስዊዲን ገበያ ነው። እነዚህ የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚፈልጉ ገበያዎች ናቸው። ሰው መሄድ አልጀመረም። በተሟላ ደረጃ ስልጠና የወሰዱ፣ ለስምሪቱ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን እያደረጉ ያሉ ሙያተኞች አሉ። ይሄም እየሄደ ያለው፤ በኦንላይን ሲስተም ነው። ኩባንያው የራሱን ሲስተም አልምቷል። ከእኛ ሲስተም እየወሰደ፣ እየፈተነ፣ እያዘጋጀ ለገበያው ዝግጁ የሚያደርግበት ስርአት ነው ያለው” ሲሉ ሚኒስትሯ አብራራተዋል።  

ሙፈሪያት የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን አስመልክቶ ዝርዝር ማብራሪያ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ቢያቀርቡም፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች ስለሚገኙባት ሊባኖስ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ለተጠየቁት የሰጡት ምላሽ ግን ጥቅል ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ለመታደግ እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲያብራራ የጠየቁት የፓርላማው የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ናቸው። 

ከሊባኖስ መንግስት ጋር የስራ ስምምነት በፓርላማ መጽደቁን ያስታወሱት ዶ/ር ነገሪ፤ ከስምምነቱ በኋላ የተሻሻሉ ሁኔታዎች እንዳሉ ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረበ ሪፖርት ተገልጾ እንደነበር ጠቅሰዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚገኙባት ሊባኖስ፤ በአሁኑ ወቅት በጦርነት ውስጥ መሆኗንም  የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በአጽንኦት አንስተዋል። “ጦርነቱ በሩብ አመቱ ውስጥ እየተስተዋለ የመጣ በመሆኑ፤ የታቀደበትም ባይሆን ወቅታዊ ሁኔታን ከማሳወቅ አኳያ፣ ዜጎቻችንን ያሉበትን ሁኔታ ተረድቶ ከጉዳት ከመታደግ አንጻር የተሰሩ ስራዎችን” እንዲያብራሩ ዶ/ር ነገሪ ለሚኒስትሯ ዕድል ሰጥተዋል።

ሙፈሪያት በምላሻቸው፤ በሊባኖስ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የስራ ሁኔታ ላይ ህጋዊ ስምምነት ከተደረገ በኋላ “ቅድመ ዝግጅቶቹን የሟሟላት ስራ እየተሰራ” እንደነበር ጠቅሰዋል። ስምምነቱ በሀገሪቱ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች “የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል” እንደሆነም አመልክተዋል። ኢትዮጵያ እና ሊባኖስ የስራ ስምሪት ስምምነት የተፈራረሙት በሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ነበር።  

https://twitter.com/ethiopiainsider/status/1714313942380552511?t=dwrXtQXO46auhLNs6XX5uQ&s=19

በታህሳስ 2016 ዓ.ም. በፓርላማ የጸደቀው ይህ ስምምነት፤ እስከ 400 ሺህ የሚገመቱ በሊባኖስ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ እና በቀጣይ በተመሳሳይ የስራ መስክ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን “መብት እና ጥቅም ለማስከበር ያለመ” እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል። በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋናነት ግብረ ኃይል አቋቁሞ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ሙፈሪያት በትላንት በስቲያው ምላሻቸው ላይ አስረድተዋል። 

“ ኢ-መደበኛ (informal) በሆነ መንገድ ከዚህ የሚሄዱ ዜጎች እንዳሉ እንገነዘባለን። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባቋቋመው ግብረሃይል መሰረት፤ የእነሱንም ሁኔታ ቢሆን በቅርቡ እየተከታተለ [ነው]። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታው ውስጥ የነበሩትን በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ተሞክሯል። የሌሎች ዜጎቻችንን በተመለከተ ግን ዝርዝር እና የተሟላ መረጃ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይገኛል” በማለት ሚኒስትሯ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚያግዝ የቴክኒክ ኮሚቴ ማቋቋሙን ይፋ ያደረገው በመስከረም ወር መጨረሻ ነበር። በዚሁ ጊዜ 51 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር እንዲመለሱ ማድረጉን ገልጾ ነበር። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መረጃ፤ 125 ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ሁኔታ ከሊባኖስ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)