በናሆም አየለ
አባል በሆኑ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ አዲስ የአመራር ምርጫ ሊያካሄድ ነው። ምክር ቤቱ ነገ እና ከነገ በስቲያ በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢውን እና የስራ አስፈጻሚ አባላቱን ይመርጣል።
በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በመንግስት መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጠር ለማድረግ በመጋቢት 2011 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ በአሁኑ ወቅት ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 59 አባል ፓርቲዎች የታቀፉበት ነው። የጋራ ምክር ቤቱ በጠቅላላ ጉባኤ በወሰነው መሰረት ሰብሳቢውን እና ምክትል ሰብሳቢውን ጨምሮ አምስት የስራ አስፈጻሚ አባላትን በየዓመቱ ይመርጣል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ያለበት ባለፈው ነሐሴ ወር ነበር። ሁለት ወር የዘገየው የጋራ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ከነገ ቅዳሜ ህዳር 7፤ 2017 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚሁ ጉባኤ ላይ እርሳቸው የሚመሩት ስራ አስፈጻሚ በ2016 ዓ.ም ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት ለተሳታፊዎች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

ከነሐሴ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የጋራ ምክር ቤቱን በሰብሳቢነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ደስታ፤ ከነገ በስቲያ እሁድ በሚካሄደው የስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ በድጋሚ የመመረጥ ዕድል አላቸው። ከተመሰረተ አምስት ዓመት ከመንፈቅ ያለፈው የጋራ ምክር ቤቱ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ጸሀፊ የሆኑት አቶ ደስታን ጨምሮ አራት ሰብሳቢዎች እስካሁን መርተውታል።
የጋራ ምክር ቤቱ የመጀመሪያው ሰብሳቢ፤ የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ሙሳ አደም ናቸው። ለሁለት አመት በቆየው የምክር ቤቱ የአመራር ጊዜ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው የሰሩት፤ የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ናቸው።
አቶ ሙሳን በመተካት ሰብሳቢ የሆኑት የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ራሄል ባፌ ናቸው። ለአንድ አመት በቆየው የዶ/ር ራሄል የኃላፊነት ዘመን፤ የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሶስተኛ ሰብሳቢ በመሆን በ2014 ዓ.ም ወደ ኃላፊነት የመጡት፤ በወቅቱ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር መብራቱ አለሙ ናቸው። የነእፓው ሊቀመንበር፤ የዶ/ር መብራቱ ምክትል በመሆን በድጋሚ ለአንድ አመት በአመራርነት ሰርተዋል። በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ መለሰ አለሙ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)