የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ለሀገር አቀፍ ምክክር እንዲቀርቡ የጠቆሟቸው አጀንዳዎች የትኞቹ ናቸው? 

በናሆም አየለ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ማካሄድ የጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል። በክልሉ ከሚገኙ 356 ወረዳዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉት ተሳታፊዎች፤ ከትላንት ማክሰኞ ታህሳስ 8፣ 2017 ዓ.ም ጀምሮ በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ነው። 

በአዳማ ከተማ ገልማ አባገዳ የመሰብሰቢያ ማዕከል ውስጥ እየተካሄደ ባለው በዚህ የምክክር ሂደት ላይ፤ ቁጥራቸው ሰባት ሺህ የሚጠጋ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ። እነዚህ ተወካዮች በአራት ክላስተሮች ስር በተመደቡ 640 ቡድኖች ተከፋፍለዋል። እያንዳንዱ ቡድን በአማካኝ 11 ተወካዮችን በውስጡ እንዲያቅፍ ተደርጓል።   

የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮቹ በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር አጀንዳነት እንዲያዙ ተደጋጋሚ ጥቆማ ካቀረቡባቸው ጉዳዮች ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጉዳይ ይገኝበታል። የፌደራል የስራ ቋንቋ፣ የሰንደቅ አላማ፣ የክልላዊ አስተዳደር ወሰን እንዲሁም ሰላም እና ጸጥታን የተመለከቱት ጉዳዮችም እንዲሁ በተወካዮቹ በተደጋጋሚ የተነሱ አጀንዳዎች ናቸው።

ከምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ጎቢሰዩ ወረዳ ወጣቶችን በመወከል በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው አቶ ቡሻ ጎተታ “አዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነቷ የኦሮሞ ህዝብ መሆኑ በህግ እንዲደነገግ፣ አፋን ኦሮሞ የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ቡድን አባላት እጃቸውን እንዲሰጡ” የሚጠይቁ አጀንዳዎች በትላንትናው የምክክር ውሎ ጎልተው መውጣታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

“መንግስት በሀገሪቱ በሁሉም አከባቢዎች ያሉ የጸጥታ ስጋቶች መስመር እንዲያሲይዝ፣ በአማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ኦሮሞዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ብሔረሰቦች መብቶች እንዲጠበቁ፣ በስራ ያለው የፌደራሊዝም ስርዓት ባለበት እንዲቀጥል” የሚሉ አጀንዳዎችም እንዲሁ በምክክሩ ላይ መቅረቡንም ገልጿል። 

የመንግስት ሰራተኞችን በመወከል ከአርሲ ዞን፣ በሌ ገስካር ወረዳ በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ መለሰ ተፈራ የተባሉ ተወካይ፤ እርሳቸው በሚገኙበት ቡድን ጎልቶ የወጣው የታሪክ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል። በምክክር መድረኩ “ያልተጻፉ የኦሮሞ ህዝብ እና ጀግኖቹ ታሪኮች እንዲጻፉ” ጥያቄ መቅረቡን እንዲሁም “በትክክል ያልተጻፉ ታሪኮች ተስተካክለው እንደገና እንዲጻፉ” እንደ እርሳቸው ያሉ ተወካዮች በአጀንዳነት ማስመዘገባቸውን አብራርተዋል።

በዚሁ ቡድን ውስጥ ያሉ አባላት “የኦሮሚያ ክልል ድንበር በትክክል ተለይቶ እንዲታወቅ” የሚል አጀንዳ ማቅረባቸውንም አቶ መለሰ ተናግረዋል። “በስራ ላይ ያለው ሰንደቅ አላማ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ባለበት እንዲቀጥል” የሚጠይቅ አጀንዳም እንዲሁ መነሳቱንም አክለዋል። 

የማህበረሰብ መሪዎችን በመወከል ከጅማ ዞን፣ ሸቤ ሶንቦ ወረዳ የመጡት አቶ ኢብራሂም አባጅሀድ “በሌሎች ክልሎች ስር ያሉ የኦሮሞ መሬቶች እንዲመለሱ፣ በጫካ ያሉ ኃይሎች ወደ ምክክሩ እንዲመጡ” የሚጠይቁ አጀንዳዎች መቅረባቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “የክልሉ ህዝብ በአካባቢው የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን የመጠቀም መብቱ እንዲረጋገጥለት እንዲሁም የኦሮሞ ህዝብ የራሱን እድል በእራሱ እንዲወስን መደረግ አለበት” የሚሉ አጀንዳዎች በተወካዮቹ አማካኝነት መቅረባቸውን አመልክተዋል።  

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ እያካሄደ ያለው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ እስከ ቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ የሚቀጥል ይሆናል። የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮቹ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በእነርሱ በኩል ያሉ አጀንዳዎችን አደራጅተው መጨረስ ይጠበቅባቸዋል። 

እነዚሁ ተወካዮች ምክክራቸውን ሲያጠናቅቁ፤ በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ የኦሮሚያ ክልልን የሚወክሉ 320 ተሳታፊዎችን ይመርጣሉ። በሀገር አቀፍ ጉባኤ እንዲሳተፉ የተመረጡት ተወካዮች ከመጪው እሁድ ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ባሉት ቀናት፤ ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የኦሮሚያ ክልል የተጠቃለሉ አጀንዳዎችን ያደራጃሉ።

የክልል ባለድርሻ አካላት የሚባሉት፤ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አካላት፣ ማህበራት እና ተቋማት፣ ታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች ናቸው። ባለድርሻ አካላቱ እና 320ዎቹ የሀገር አቀፍ ጉባኤ ተሳታፊዎች ያደራጇቸው የኦሮሚያ ክልል አጀንዳዎች ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሚያስረክቡት በመጪው ማክሰኞ ታህሳስ 15፤ 2017 ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)