● በዛሬው ዕለት ብቻ ሰባት የመሬት መንቀጥቀጦች ተመዝግበዋል
በአፋር ክልል አዋሽ አካባቢ ከሰሞኑ ከደረሱት የመሬት መንቀጥቀጥ ክሰተቶች በመጠኑ ከፍተኛ የሆነ ርዕደ መሬት ዛሬ እሁድ ምሽት መከሰቱን የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል አስታወቀ። በአካባቢው ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ10 ላይ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በሬክተር ስኬል 5.0 የደረሰ እንደሆነ የማዕከሉ መረጃ አመልክቷል።
በሬክተር ስኬል የመለኪያ መሳሪያ ከ2.5 እስከ 5.4 መጠን ያላቸው የመሬት መንቀጥቀጦች አነስተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ እንደሆኑ በዘርፉ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ይገልጻሉ። በዚህ መጠን የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች ንዝረታቸው በበርካታ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባሉ ከተሞች ጭምር የሚሰማ እንደሆነም የተቋማቱ መረጃ ያሳያል።
የምሽቱ የመሬት መንቀጥቀጥ በአዲስ አበባ ጭምር ዘለግ ላሉ ሰከንዶች የቆየ ንዝረት አስከትሏል። ከአዋሽ ከተማ 14 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ስፍራ የተከሰተው የምሽቱ ርዕደ መሬት፤ በዛሬው ዕለት ብቻ በአካባቢው የተመዘገቡ መሬት መንቀጥቀጦችን ቁጥር ሰባት አድርሶታል።
ዛሬ ንጋት ላይ በሬክተር ስኬል 4.5 እና 4.7 የተለኩ የመሬት መንቀጥቀጦች የተከሰቱ ሲሆን ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ገደማ ደግሞ በሬክተር ስኬል 4.9 መጠን ያለው ርዕደ መሬት ተመዝግቧል። ከዚህ ክስተት አራት ሰዓት በኋላ በሬክተር ስኬል 4.7 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጥሟል።
እንደ የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል መረጃ ከሆነ ዛሬ ምሽቱን ብቻ ለሶስት ጊዜያት ያህል በአዋሽ አካባቢ ርዕደ መሬት ተከስቷል። በሬክተር ስኬል 4.8፣ 5.0 እና 4.9 የተለኩት እነዚህ የመሬት መንቀጥቀጦች የተመዘገቡት፤ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ነው።
በህንጻዎች እና በሌሎች ግንባታዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የመሬት መንቀጥቀጦች፤ በሬክተር ስኬል ከ5.5 እስከ 6.0 መጠን ያላቸው ናቸው። በአዋሽ አካባቢ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለው ርዕደ መሬት፤ እስካሁን ድረስ እዚህ መጠን ላይ የደረሰ አይደለም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)