ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስ” ተስማሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን “ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ” ተስማሙ። ሁለቱ መሪዎች በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ “የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና” እንዲኖር በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት “ለማጠናከር” መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

ሁለቱ ሀገራት ለአንድ ዓመት ገደማ ሻክሮ የቆየውን ግንኙነታቸውን ለማደስ የተስማሙት፤ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ዛሬ ቅዳሜ ጥር 3፤ 2017 ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው። አብይ እና ሐሰን ሼክ “በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸውን” የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከውይይቱ በኋላ ያወጣው የጋራ መግለጫ ይጠቁማል።

በመግለጫው መሰረት መሪዎቹ “በሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ገንቢ ውይይት” አድርገዋል። የመሪዎቹ ውሳኔ ከአስር ወራት ገደማ በኋላ በሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ወደ ሞቃዲሾ እንዲመለሱ መንገድ ይጠርጋል። ሶማሊያ ተቀማጭነታቸው በሞቃዲሾ የነበረውን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድን ያባረረችው በመጋቢት 2016 ዓ.ም. ነው። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት የተቆጣችው ሶማሊያ፤ በወቅቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ አምባሳደሯን “ለምክክር” ወደ ሞቃዲሾ ጠርታ ነበር። ከሐርጌሳ ጋር በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ሰበብ፤ የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መንግስት፤ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ “ኢትዮጵያ አትሳተፍም” የሚል አቋም እስከ ማራመድ ደርሷል። 

የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ ባለፈው ሳምንት ወደ ሞቃዲሾ አቅንተው ከሶማሊያ አቻቸው በተነጋገሩበት ወቅት፤ መወያያ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ ኢትዮጵያ በአዲሱ ተልዕኮ ውስጥ የሚኖራት ተሳትፎ ነበር። የግብጽ ወታደሮች በሚካተቱበት አዲሱ ተልዕኮ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚኖራት ሚና፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ውይይት ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚሆን ተነግሯል። 

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሚገኙበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና መረጋጋት፤ “በእምነት፣ መተማመን እና መከባበር” ላይ የተመሰረተ የሁለቱን ሀገሮች “ጠንካራ ትብብር” እንደሚሻ ሁለቱ መሪዎች ማረጋገጣቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። መሪዎቹ “ቀጠናዊ ግንኙነቶችን ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባትን ለማበጀት እና የጋራ ዕድገትን ለመፍጠር” በጋራ ለመስራት መስማማታቸውንም ገልጸዋል።

ፎቶ፦ የቱርክ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ፤ በቱርክ አሸማጋይነት ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ በአንካራ ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ሶስተኛ ውይይት ላይ ፊት ለፊት እስኪገናኙ ድረስ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በብርቱ ሻክሮ ቆይቷል። በቱርክ ፕሬዝዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶጋን አሸማጋይነት ከተደረገው ከዚህ ውይይት በኋላ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “ልዩነቶቻቸውን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ ለመተው” እና “ትብብር ለማበጀት” ተስማምተው ነበር።  

በሶማሊያ ሉዓላዊ ስልጣን ስር ኢትዮጵያ “አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ” የባህር በር “በኮንትራት፣ በኪራይ እና ተመሳሳይ አሰራር” የምታገኝበትን መንገድ ለማመቻቸትም በወቅቱ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። በዛሬውም ውይይት ሁለቱ መሪዎች ለአንካራው ስምምነት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በአንካራ የታቀደውን “ቴክኒካዊ ድርድር” ለማፋጠንም ተስማምተዋል።

በመጪው የካቲት ወር እንዲካሄድ የታቀደው “ቴክኒካዊ ድርድር”፤ የባህር በር ጉዳይን ጨምሮ በአንካራው ስምምነት የተካተቱ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን ነው። ሀገራቱ በቱርክ አመቻቺነት የሚካሄደውን “ቴክኒካዊ ድርድር” በአራት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ፤ አዲስ ስምምነት ለመፈራረም ዕቅድ አላቸው።

ፎቶ፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ግብዣ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ በካምፓላ ከዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና ከኬንያው አቻቸው ዊሊያም ሩቶ ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ሐሰን ሼክ ወደ አዲስ አበባ ሲያቀኑ፤ የሶማሊያ፣ የግብጽ እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የጋራ የሶስትዮሽ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ስብሰባ በካይሮ እየተካሄደ ነበር። 

የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደልላቲ፣ የኤርትራው ኦስማን ሳሌህ እና የሶማሊያ አቻቸው አሕመድ ሙዓሊም ፊቂ የተሳተፉበት የካይሮው የመጀመሪያ ስብሰባ፤ “ቀጠናዊ ትብብርን ማጠናከር፣ በአፍሪካ ቀንድ ደህንነትን እና መረጋጋትን ለማስፈን ያለመ” መሆኑ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)