በተስፋለም ወልደየስ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ካሉት ሰባት ምክትል ፕሬዝዳንቶች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ሳምሶን መኮንን፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ በዕጩነት ቀረቡ። የአዲሱ ዋና ዳይሬክተር ሹመት ነገ ማክሰኞ ጥር 6፤ 2017 በሚካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዋና ዳይሬክተሩን ሹመት እንዲያጸድቅ፤ ጥያቄውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥር 1 በጽህፈት ቤታቸው አማካኝነት ለፓርላማ በላኩት ደብዳቤ፤ የዶ/ር ሳምሶን ሹመት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አማካኝነት እንዲከናወን ጠይቀዋል።
በመጋቢት 2013 ዓ.ም የወጣው ይኸው አዋጅ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሰየም ይደነግጋል። ምክር ቤቱ ዋና ዳይሬከተሩን የሚሰይመው፤ በመንግስት አቅራቢነት እንደሆነ በአዋጁ ተቀምጧል። በባለስልጣኑ ቦርድ አማካኝነት የሚመለመለው ዋና ዳይሬክተር፤ “ከማንኛውም ፓርቲ አባልነት ነጻ መሆን” እንደሚኖርበትም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

ዋና ዳይሬክተሩ፤ መገናኛ ብዙኃን ተግባራቸውን በሕግ መሰረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ ክትትል እና ቁጥጥር የማድረግ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠውን መስሪያ ቤት ስራዎች የመምራት እና የማስተዳደር ኃላፊነት በአዋጅ ተጥሎበታል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የ12 ዓመታት የማስተማር እና የአመራርነት ልምድ እንዳላቸው የተናገረላቸው አዲሱ ተሿሚ፤ በአዋጁ መሰረት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ “ዋና ስራ አስፈጻሚ ይሆናሉ”።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን መስሪያ ቤት መብት እና ግዴታዎች በ2013ቱ አዋጅ የተላለፉለትን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን ከምስረታው ጀምሮ ሲመሩ የቆዩት አቶ መሐመድ እድሪስ ናቸው። አቶ መሐመድ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተሾሙት በመጋቢት 27፤ 2013 ዓ.ም. ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ሹመታቸው፤ በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ የሚታወቁት አቶ ዮናታን ተስፋዬ እና የባለስልጣኑ የህግ ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ግዛው ተስፋዬን የመስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አድርገዋቸዋል። ሁለቱ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በአዋጅ ከተቋቋመ በኋላ በተመሳሳይ የኃላፊነት ደረጃ ቀጥለዋል።

አቶ መሐመድ ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ በሰላም ሚኒስትርነት መሾሟቸውን ተከትሎ፤ መስሪያ ቤቱ ከአንድ ወር በላይ ያለ ዋና ዳይሬክተር ቆይቷል። በእነዚህ ጊዜያት በባለስልጣኑ የተዘጋጀውን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ማሻሻያ አስመልክቶ በተዘጋጁ መድረኮች ላይ መስሪያ ቤቱ ሲወከል የቆየው በሁለቱ ምክትል ዳይሬክተሮች ነው።
በፓርላማ ያልጸደቀው አዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ፤ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በህዝብ ተወካዮች የሚሾመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት እንደሆነ ይደነግጋል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አቅራቢነት ሹመታቸው እንዲጸድቅ ለፓርላማ የቀረቡት ዶ/ር ሳምሶን፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን እና አለምአቀፋዊነት ጽህፈት ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሰሩ የቆዩ ናቸው።
ዶ/ር ሳምሶን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት የትምህርት ዘርፍ ያገኙትም ከዚሁ ዩኒቨርስቲ ነው። አዲሱ ተሿሚ በተማሩበት የትምህርት ክፍልም በአስተማሪነት አገልግለዋል። ዶ/ር ሳምሶን በውጭ ቋንቋዎች የማስተርስ ዲግሪ ባገኙበት አምቦ ዩኒቨርስቲ እና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ አስተምረዋል።

የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ (UNISA) በኮሚዩኒኬሽን ያገኙት ዶ/ር ሳምሶን፤ በተለያዩ የምርምር ህትመቶች ላይ የወጡ ጽሁፎችን በግላቸው እና በጋራ አሳትመዋል። በብሉምበርግ የአፍሪካ ሚዲያ ኢኒሼቴቭ ስር የሚሰጠውን የፋይናንስ ጋዜጠኝነት ስልጠናንም በስራ አስኪያጅነት የመሩት ዶ/ር ሳምሶን፤ በሌሎች ተቋማትም በማማከር ስራዎች ተሳትፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)