በትግራይ ክልል “አስቸኳይ ምርጫ” እንዲደረግ አሊያም “የመማክርት ምክር ቤት” እንዲቋቋም ኢህአፓ ጠየቀ

በደምሰው ሽፈራው

በትግራይ ክልል “አስቸኳይ ምርጫ” እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፖርቲ (ኢህአፓ) ጠየቀ። የትግራይ ህዝብ “በመረጣቸው እንደራሴዎች እስኪወከል ድረስ “፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉንም “ህጋዊ” የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካተተ “የመማክርት ምክር ቤት” እንዲቋቋም ፓርቲው ምክረ ሃሳብ አቅርቧል። 

ፓርቲው ይህን ያስታወቀው ዛሬ ረቡዕ ጥር 14፤ 2017 አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በኢህአፓ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተጠራው የዛሬው መግለጫ፤ በክልሉ በቅርቡ በተከሰቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። 

የትግራይ ክልል በፌደራል ምክር ቤቶች ያለው የውክልና ጉዳይም በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ዓመት የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከመካሄዱ አስቀድሞ ካሉት ወራት ወዲህ፤ ክልሉ በህዝብ ተወካዮችም እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያለው ውክልና ተቋርጧል።     

“የትግራይ ህዝብ እንደ ፌዴሬሽን አባልነቱ በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 ወንበሮች ያሉት ቢሆንም፤ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተወክሎ አያውቅም” ሲል ኢህአፓ በዛሬው መግለጫው አስታውሷል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው “ባለፉት አራት ዓመታት በፓርላማው እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሚተላለፉ ውሳኔዎች፤ የትግራይ ህዝብን ፍላጎቶች ያካተቱ አልነበሩም” ብሏል። 

የክልሉ ህዝብ በተወካዮቹ “እንዲወከል” እና ጉዳዮቹን “በእንደራሴዎቹ እንዲወስን” ለማድረግ፤ “አስቸኳይ ምርጫ” ማካሄድ እንደሚገባ ኢህአፓ በመግለጫው አሳስቧል። ፓርቲው ይህን አቋሙን ይፋ ያደረገው፤ መጪውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ አንድ ዓመት ከሶስት ወራት ገደማ በቀረበት ጊዜ ነው። 

በዛሬው መግለጫ ላይ የተገኙት የኢህአፓ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ፤ የትግራይን ህዝብ “ሌላ ምርጫ እስከሚካሄድ ጠብቅ ማለት፤ አሁንም እዚያ ውስጥ ያለው ችግር፣ ብሶት፣ መከራ እንዲቀጥል ማድረግ ነው” ብለዋል። “ህዝብ ያለ እንደራሴው፤ አንድ ቀንም ማደር አለበት ብለን አናምንም” ሲሉም የፓርቲውን አቋም አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የኢህአፓ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ ይስሀቅ ወልዳይ፤ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ እንዲቋቋም የተደረገው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበረበት ብለዋል። በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመው፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የግጭት ማቆም ስምምነት መሰረት ከተፈረመ ከአራት ወራት በኋላ ነበር።  

አቶ ይስሀቅ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመጀመርያ ስድስት ወር ወደ ምርጫ ለመሄድ ነበር። ነገር ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል እንቅስቃሴ አላደረገም” ሲሉ ተችተዋል። “ትግራይ በፌደራል ብቻ አይደለም ውክልና ያጣችው፣ በክልል ደረጃም ምክር ቤት የላትም። የክልሉ ምክር ቤቶች ፈርሰዋል” ሲሉም አክለዋል።

የክልል ምክር ቤቶችን በተመለከተ በሁለት ቡድኖች ስር ያሉ የህወሓት መሪዎች እያራመዷቸው ያሉ አቋሞችንም አቶ ይስሀቅ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አንስተዋል። “ህወሓት ‘ነባሩ ምክር ቤት ይቀጥል’ ሲል፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ደግሞ ‘ፈርሷል’ ይላል። ‘ፈርሷል’ የምንል ከሆነ፤ ሌላ መማክርት ወይም ምክር ቤት ያስፈልጋል ማለት ነው” ሲሉ አቶ ይስሃቅ አሳስበዋል። 

“ህወሓት ‘ነባሩ ምክር ቤት ይቀጥል’ ሲል፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ደግሞ ‘ፈርሷል’ ይላል። ‘ፈርሷል’ የምንል ከሆነ፤ ሌላ መማክርት ወይም ምክር ቤት ያስፈልጋል ማለት ነው”

– አቶ ይስሀቅ ወልዳይ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የኢህአፓ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል

ኢህአፓ በዛሬው መግለጫውም ይህንኑ የመማክርት ምክር ቤት አስፈላጊነትን በአጽንኦት አንስቷል። “ህጋዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሂዶ፤ የትግራይ ህዝብ በእንደራሴዎቹ እስኪወከል ድረስ ሁሉንም ህጋዊ ፓርቲዎች ያካተተ የመማክርት ምክር ቤት እንዲቋቋም ኢህአፓ በጽኑ ያሳስባል” ሲል ፓርቲው በመግለጫ ላይ አስፍሯል። በዚህ ወቅት “በትግራይ ክልል አስቸኳይ ምርጫ እንዲካሄድ አሊያም የመማክርት ምክር ቤት እንዲቋቋም ለምን አስፈለገ?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበ ጥያቄ አቶ ይስሀቅ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።    

“ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቋቋም ‘አካታች እንዲሆን ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ በተግባር ግን ሙሉ ለሙሉ ለህወሓት የተሰጠ ሆኗል። ሁሉንም ፓርቲዎች፣ የሚመለከታቸው የሲቪል ማህበራት እና የሃይማኖት ተቋማት ያካተተ መሆን ስላልቻለ [ነው]” ብለዋል አቶ ይስሀቅ። በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በሰጧቸው መግለጫዎች፤ “ሁሉን አካታች” እና አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት በተመሳሳይ መልኩ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል። 

ኢህአፓ አዲስ እንዲቋቋም የጠየቀው የመማክርት ምክር ቤት፤ የክልሉን ፕሬዝዳንት “እስከማውረድ የደረሰ ስልጣን” ያለው እንደሚሆን አቶ ይስሀቅ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የመማክርት ምክር ቤቱ “የክልሉ ምክር ቤት ስልጣንን ሙሉ ነው የሚይዘው” ሲሉም ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)