የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አመራሮች ሹመት፤ የፓለቲካ ገለልተኝነትን “ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው” የሚል ትችት ቀረበበት

በቤርሳቤህ ገብረ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሹመታቸውን ያጸደቀላቸው የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አመራሮች የአመራረጥ ሂደት፤ “ከፓለቲካ ገለልተኝነት” ነጻ መሆን የሚለውን መስፈርት “ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው” የሚል ትችት በፓርላማ አባል ቀረበበት። ተሿሚዎቹ ለፓርላማ የቀረቡት፤ የፖለቲካ ገለልተኝነትን ጨምሮ እያንዳንዱ ጉዳይ “በደንብ” እና “በዝርዝር” ታይቶ መሆኑን የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገልጸዋል።

በህግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈጻሚ አካላት መከበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተቋቋመው በ1992 ዓ.ም ነው። የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን የማድረግ ዋና ዓላማ ያለው ተቋሙ፤ የቀረቡለትን የአስተዳደር በደል አቤቱታዎች መሰረት በማድረግ “ስልታዊ ምርመራ” የማካሄድ ኃላፊነት ተጥሎበታል። 

ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው ተቋም፤ ላለፉት ስድስት ወራት የሚመራው ዋና እንባ ጠባቂ አልነበረውም። ይህ የሆነው ተቋሙን ላለፉት ስድስት  ዓመት ሲመሩ የነበሩት ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ የስልጣን ጊዜያቸው በማብቃቱ እና ከዋና እንባ ጠባቂነታቸው በመሰናበታቸው ነው።

የተቋሙን የተጓደሉ ምክትል እና የዘርፍ ዕንባ ጠባቂዎች እንዲያቀርብ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ኮሚቴ ያቋቋመው የተወካዮች ምክር ቤት፤ የተሰናባቹን ዋና ዕንባ ጠባቂ ተተኪ የማፈላለግ ሂደት እንዲጀመር ውሳኔ ያሳለፈው ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ነበር። ፓርላማው ለዋና ዕንባ ጠባቂ የሚሆን ዕጩ የማቅረብ ኃላፊነት የሰጠው፤ የተቋሙን አመራሮች ለመተካት አስቀድሞ ለተቋቋመው ኮሚቴ ነው። 

ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባላትን በውስጡ የያዘው ይህ ኮሚቴ፤ እስከ ታህሳስ ወር መጀመሪያ ባሉ ሁለት ሳምንታት ውስጥ የዋና ዕንባ ጠባቂ ዕጩ ጥቆማን ከህዝብ ሲቀበል ቆይቷል። ለህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሶስት የኃላፊነት ቦታዎች 345 ግለሰቦች ተጠቁመው እንደነበር የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ተናግረዋል። 

ለዋና ዕንባ ጠባቂነት በዕጩነት የተጠቆሙ ሰዎች ብዛት 60 እንደሆነም የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አፈ ጉባኤው አስረድተዋል። ከእነዚህ ዕጩዎች መካከል ተመርጠው፤ ዛሬ ሐሙስ ጥር 15፤ 2017 በተካሄደ የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ሹመታቸው የጸደቀላቸው ወ/ሮ ስመኝ ውቤ ናቸው። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ወ/ሮ ስመኝ፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህግ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በስርአተ ጾታ ይዘዋል። ወ/ሮ ስመኝ ከዚህ ቀደም በሶስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሚኒስትር ዴኤታነት ሰርተዋል። አዲሷ ዋና ዕንባ ጠባቂ የአመራርነት ስልጣን በመያዝ ያገለገሉባቸው እነዚህ የፌደራል ተቋማት፤ የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር እንዲሁም የፍትህ ሚኒስቴር ናቸው።

በህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የእርሳቸው ምክትል እንዲሆኑ በዛሬ ዕለት የተሾሙት ዶ/ር የኔነህ ስመኝም፤ እንደዚሁ ለኃላፊነት ቦታ እንግዳ አይደሉም። በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዳኝነት እስከ ፕሬዝዳንት የደረሰ ኃላፊነት የነበራቸው ዶ/ር የኔነህ፤ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና የህግ አማካሪ ሆነውም ሰርተዋል። ዶ/ር የኔነህ የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በህግ ያገኙ ናቸው።

የዘርፍ እንባ ጠባቂ ሆነው የተሾሙት አቶ አባይነህ አዴቶ በበኩላቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍትህ እና ህግ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ የነበሩ እና የክልሉ ጸረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው የሰሩ ናቸው። እንደ አዲሱ ምክትል የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ሁሉ፤ አቶ አባይነህም የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት በህግ  የትምህርት ዘርፍ ነው።

የሶስቱ አመራሮች ሹመት በፓርላማ ከመጽደቁ አስቀድሞ ግን የዕጩዎቹ አመራረጥ፤ በአዋጅ የተቀመጠውን መስፈርት የተከተለ መሆኑ ላይ በአንድ የፓርላማ አባል ጥያቄ ተነስቶበታል። አንድ ግለሰብ በዋና ዕንባ ጠባቂነት በዕጩነት ለመወዳደር ከፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ መሆን እንዲሁም በህግ ወይም በተዛማጅ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖረው እንደሚገባ በአዋጅ ተደንግጓል። 

ዕድሜው ከ35 ዓመት በላይ ሊሆን የሚገባው ዕጩ ተወዳዳሪ፤ በቂ የስራ ልምድ እንዲኖረውም በመስፈርትነት ተቀምጧል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ ተሿሚ ለመሆን በግልጽ ከተቀመጡ መስፈርቶች መካከል “የፖለቲካ ገለልተኝነትን” በማንሳት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። 

“ከመስፈርቶቹ መካከል አንደኛው ከፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኝነት [ያለው] የሚል ነው። ነገር ግን ሲቪያቸው ሲነበብ፤ ሶስቱም ኃላፊዎች ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎች ሆነው የሰሩ ናቸው። በተለመደው አሰራር ደግሞ ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎች፤ ከገዢው ፓርቲ ነው የሚሆኑት። ስለዚህ ገለልተኝነት የሚለው ነገር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል ዶ/ር አበባው። 

“ሶስቱም ኃላፊዎች ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎች ሆነው የሰሩ ናቸው። በተለመደው አሰራር ደግሞ ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎች፤ ከገዢው ፓርቲ ነው የሚሆኑት። ስለዚህ ገለልተኝነት የሚለው ነገር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል”

– ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል

የፓርላማ አባሉ ከአመልካቾች ውስጥ በሰብአዊ መብት ተቋማት ውስጥ የሰሩ ስለመኖራቸውም ጠይቀዋል። “ለዚህ ቦታ ይመጥናሉ ተብሎ የሚገመተው፤ የሰብአዊ መብት ተቋማት ውስጥ የሰሩ [ናቸው]። ከእዚያ ቢሆኑ effective የሆኑ ተሟጋቾች፣ ለcivil servant የሚሟገቱ ማግኘት ይቻላል። ከዚያ አካባቢ ለመምረጥ ለምን አልተቻለም? ወይስ አመልካቾች አልተገኙም ወይ?” ሲሉ ዶ/ር አበባው ጥያቄያቸውን ለኮሚቴው አባላት አቅርበዋል። 

የአብኑ የፓርላማ ተወካይ የተሿሚዎቹ  የትምህርት ደረጃ እና የስራ ልምዳቸውን የያዘ ሰነድ (CV) “ዘግይቶ” እንደተላከ በማንሳት፤ ይህ ችግር በተደጋጋሚ እየተስተዋለ በመሆኑ መስተካከል እንደሚገባው አሳስበዋል። ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት አፈ ጉባኤ ታገሰ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አመራሮች ሹመት “በግልጽ እና ይፋዊ” በሆነ መንገድ ጥቆማ ቀርቦ ውድድር የሚካሄድበት እንደሆነ አስታውሰዋል። 

አፈ ጉባኤው “ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበት ነው” ባሉት በዚህ ሂደት መሰረት፤ “በርካታ ዕጩዎች” መጠቆማቸውን በአሃዝ አስደግፈው ገልጸዋል። ዕጩዎቹ የተጠቆሙት ከፌደራል ተቋማት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከሁሉም ክልሎች መሆኑንም አመልክተዋል። የዕጩዎቹን ማንነት ለማጣራት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትን እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጨምሮ ሰባት አባላት ያሉበት ኮሚቴ “ለበርካታ ወራት ስራዎችን” ማከናወኑንም አስረድተዋል።    

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“ወደ ክልሎቹ ተሂዶ [ዕጩዎች] የሚሰሯቸው ስራዎች፣ ስነ ምግባራቸው እና ብቃታቸው፣ ለአፈጻጸማቸው ያለው ምስክርነትም ጭምር የሚፈተሽበት ነው” ሲሉም አቶ ታገሰ “ዝርዝር ጉዳዮች” ታይተውበታል ያሉትን ሂደት አብራርተዋል። በእነዚህ ላይ በመመስረት የኮሚቴው አባላት የሚሰጧቸው ነጥቦች “አማካይ” የሚወሰድ መሆኑንም አክለዋል። በአዋጁ መሰረት የፓርላማ አፈ ጉባኤ የኮሚቴ ሰብሳቢ ቢሆንም፤ በፓርላማ የተመረጡ አባላት “በተአማኒነት” ስራቸውን መስራታቸውን እና በሙሉ ድምጽ የተስማሙባቸው ዕጩዎች ለሹመት የቀረቡ መሆኑንም አስገንዝበዋል።  

“የተጠቆሙ ዕጩዎች ገለልተኛ ናቸው ወይ? የትምህርት ዝግጅታቸው ምንድን ነው? ምን ሰርተዋል? በህዝቡ ያላቸው ተቀባይነት ምንድን ነው? በተቋማቸው ያደረጉት ተግባር ምንድን ነው? የምንሾማቸው ሰዎች፤ በህገ መንግስቱ በተቋቋመ የሀገሪቱ ከፍተኛ [በሆነ ተቋም] የሚሾሙ ናቸው። ይህን ኃላፊነት መሸከም የሚችሉ ናቸው ወይ? የሚለው በዝርዝር እና በደንብ ታይቷል” ሲሉም አፈ ጉባኤው ከዶ/ር አበባው ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)