በቤርሳቤህ ገብረ
በቀይ ባህር ላይ ያለው የጸጥታ ቀውስ ለመርከብ ጭነቶች ፍሰት “ትልቅ ተግዳሮት” መፍጠሩን የጅቡቲ የዶራሌህ ኮንቴነር ተርሚናል አስተዳደር ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አብዲላሂ አዳዌህ ተናገሩ። የጸጥታ ችግሩ እንደሚሻሻል የሚያመላክቱ “አዎንታዊ ምልክቶች” በቅርቡ መታየታቸውንም ገልጸዋል።
ከ95 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ የገቢ እና የወጭ ንግድ ጭነት የሚጓጓዝባቸው የጅቡቲ ወደቦች የቀይ ባህርን ተንተርሰው የሚገኙ ናቸው። ከዓለም አቀፍ ንግድ 12 በመቶውን ያህል የሚሸፍኑ ጭነቶች በየዓመቱ የሚጓጓዙበት የቀይ ባህር መስመር፤ ከህዳር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በየመን የሁቲ አማጽያን ተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዘርበት ቆይቷል።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ የሁቲ አማጽያን በየመን እና እና በአፍሪካ መካከል በሚገኘው የባብ ኤል መንደብ የባህር ሰርጥ በሚጓዙ ከ100 በላይ የንግድ መርከቦች ላይ በሚሳኤል እና በድሮን ጥቃቶች ፈጽመዋል። አማጽያኑ ኢላማ የሚያደርጓቸው ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው በሚሏቸው መርከቦች ላይ እንደሆነ ቢገልጹም፤ በርካታ የመርከብ ድርጅቶች ግን ጥቃቱን በመፍራት በመስመሩ የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች ለመቀየር ተገድደዋል።

ጅቡቲ ካሏት ወደቦች አንዱ የሆነውን የዶራሌህ ኮንቴነር ተርሚናል የሚያስተዳድረው ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ የቀይ ባህር የጸጥታ ችግር ለሀገራቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ “እጅግ አስቸጋሪ ነው” ባይ ናቸው። ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህን ያሉት፤ ትላንት ማክሰኞ ጥር 13፤ 2017 በአዲስ አበባው ሸራተን ሆቴል በተካሄደ ኮንፍረንስ ላይ በተካፈሉበት ወቅት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው።
በኢትዮጵያ ሎጀስቲክስ ዘርፍ ማህበራት የተዘጋጀው ይህ ኮንፍረንስ፤ በኢትዮጵያ፣ በጅቡቲ እና በአካባቢው ያለውን ንግድ ማበልጸግ ዓላማ ያደረገ ነው። በኮንፍረንሱ ላይ ለቀጠናዊ የንግድ ትስስር እና ትብብር “ወሳኝ መስመር” የሆነውን የኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደርን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።
በቀይ ባህር ያለው የጸጥታ ቀውስ በአመት በአማካኝ 12.5 ሚሊዮን ቶን የኢትዮጵያ ጭነት የሚጓጓዝበት የጅቡቲ ወደብ አጠቃቀም ላይ “ተጽዕኖ ማሳደሩ” ተነግሯል። የጸጥታ ቀውሱ በወደብ “ተጨማሪ መጓተት” መፍጠሩን እና በኢትዮ ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር “የመጓጓዣ ወጪ መጨመሩን” የኢትዮጵያ ሎጀስቲክስ ዘርፍ ማህበራት ገልጿል።

የዶራሌህ ኮንቴነር ተርሚናል አስተዳደር ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ትላንት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው አጠር ያለ ቆይታ ላይ ይህንኑ አስተጋብተዋል። በቀይ ባህር በሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የመርከቦች የመድረሻ ጊዜ “አስተማማኝ አለመሆኑን” የጠቆሙት አብዲላሂ አዳዌህ፤ ይህም በንግድ ማህበረሰቡ እና በወደቡ የስራ ክንዋኔ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል።
“የሎጀስቲክ ስራ እንደ ወንዝ ፍሰት ነው። የሆነ ቦታ ከቆምክ፤ ሞልቶ መፍሰስ አሊያም መድረቅ ያጋጥምሃል። እንዲህ አይነቱ መቆም በቂ [የጭነት] መጠን እንዳይኖርህ ያደርጋል። አንዳንዴ ደግሞ በጣም ብዙ [የጭነት] መጠን ይኖርሃል። ይህ የስራ ክንዋኔውን ዝብርቅርቅ ያደርገዋል” ሲሉ በወደብ ያለውን ሁኔታ አብዲላሂ አስረድተዋል።
የቀይ ባህር የጸጥታ ችግር፤ ጭነቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዳይደርሱ እንቅፋት እንደፈጠረው ሁሉ በባህር ማጓጓዝንም “በጣም ውድ” እንዳደረገው ዋና ስራ አስፈጻሚው አመልክተዋል። በጸጥታ ችግሩ ምክንያት መርከቦች የሚያጅቧቸውን ኃይሎች ለመጠበቅ በመገደዳቸው ምክንያት የሚፈጠረው መዘግየት፤ ከጅቡቲ ወደብ ስርዓት ጋር የተገናኘ ሳይሆን ከባህር መስመሩ ስርዓት ጋር የተያያዘ እንደሆነም አክለዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው በትላንቱ የጥያቄ እና መልስ ቆይታቸው፤ በቀይ ባህር ያለው የጸጥታ ችግር እንደሚሻሻል የሚያሳዩ “አዎንታዊ ምልክቶች” እንዳሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ሆኖም አዎንታዊ ምልክቶቹ ምን እንደሆነ በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
በእስራኤል እና በፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ መካከል ባለፈው እሁድ የተኩስ ማቆም ስምምነት መደረሱን ተከትሎ፤ በቀይ ባህር የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንደሚቀነሱ የሁቲ አማጽያን ፍንጭ ሰጥተዋል። አማጽያኑ ይህንኑ የሚያመልክት የኤሚይል መልዕክት ባለፈው እሁድ ለመርከብ ድርጅቶች መላካቸውን አሶስቴድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ሎጅስቲክስ ዘርፍ ማህበራት፤ የቀይ ባህር ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ቀድሞ ከነበረው “የተሻሻለ ነው” ባይ ነው። “በቀይ ባህር ዙሪያ ያለው ነገር በጣም አውኮን ሰንብቶ ነበር። አሁን የጅቡቲ እና የመርከብ ድርጅቶች በወሰዱት አንዳንድ ማሻሻያዎች የተሻለ አገልግሎት እያገኘን እንገኛለን” ሲሉ የዘርፍ ማህበራቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ኤልሳቤት ጌታሁን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)