የኢትዮጵያ መንግስት ከስድስት ወራት በፊት ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት፤ የሀገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎች “የብር ፍላጎት” “በእጥፍ እንደጨመረ” የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ። ሚኒስትሩ ባለፉት ስድስት ወራት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የቀረበው ብድር “አጥጋቢ” እንዳልሆነ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል።
አቶ መላኩ የመስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈጻጸም ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ባለፈው መንፈቅ ዓመት ለአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስራ ማስኬጃ ብድር እና የሊዝ ፋይናንስ ለማቅረብ ታቅዶ የነበረው የገንዘብ መጠን 3.4 ቢሊዮን ብር ነው። ሆኖም በዚህ ጊዜ ውስጥ ለኢንዱስትሪዎቹ የቀረበው 7.8 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የገንዘብ መጠኑ ከ2016 ተመሳሳይ ወቅት ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ4.4 ቢሊዮን ብር ገደማ ከፍ ያለ ነው።
ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች 28.7 ቢሊዮን ብር ለማቅረብ ታቅዶ እንደነበር ለፓርላማ አባላት ቤቱ ያስረዱት አቶ መላኩ፤ የተሳካው 24.87 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል። ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሰጠው ብድር ከዕቅዱ አኳያ ዝቅ ቢልም፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን 4.9 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

አቶ መላኩ “ከተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ [ጋር] ተያይዞ የብር ፍላጎት መጠን በእጥፍ ስለጨመረ፤ አቅርቦቱ አጥጋቢ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል አይደለም” ሲሉ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ውሏቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። ዘርፉ የሚሻውን “በቂ እና ውጤታማ ፋይናንስ ለማቅረብ” “ባንክ እና ባንክ ነክ ያልሆኑ ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀም” እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ባንኮች “ለአምራች ኢንዱስትሪው ፋይናንስ ከማቅረብ ይልቅ በተለመደው መንገድ የአጭር ጊዜ ትርፍ ወደ ሚያስገኙ እና ስጋታቸው ዝቅተኛ በሆኑ ዘርፎች ላይ እንደተሰማሩ እንዳይቀጥሉ ማድረግ የሚቻልበትን አሰራር መፈተሽ ይገባናል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግስት በዚህ ረገድ በቀጣይ ሊያደርግ የሚችለውን ጠቁመዋል። ባንኮች ለማምረቻው ዘርፍ የሚሰጡት ብድር፤ ወደ 24 በመቶ እንዲያድግ መንግስት “የፖሊሲ አቅጣጫ” እንደሰጠም ገልጸዋል።
ባንኮች ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሰጡት ብድር ከ13 በመቶ የማይበልጥ እንደነበር በዛሬው የሚኒስትሩ የፓርላማ ማብራሪያ ላይ ተጠቅሷል። ለአምራቾች የተሰጠው ብድር “እስካሁን ድረስ ወደ 16.3 በመቶ መድረሱ”፤ በዘርፉ ለታዩ መሻሻሎች አስተዋጽኦ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኝበት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ለአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስራ ማስኬጃ የሚሰጠው ብድር፤ ባንኮች ካላቸው ካፒታል ከአንድ በመቶ ያልበለጠ እንደነበር ያስታወሱት አቶ መላኩ፤ ይህ መጠን ወደ 10.3 በመቶ “ከፍ እንዲል መደረጉን” በአዎንታ አንስተዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንሲንግ የብድር አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ “ረዥም ሂደቶችን” በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ማሻሻሉ፤ ያለፉትን ወራት አፈጻጸም “የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል” ብለዋል አቶ መላኩ።
በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለማምረቻው ዘርፍ 468.4 ሚሊዮን ዶላር ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የተሳካው 369 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሆነ አክለዋል። የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት ባንኮች የሚጠይቁት የማስያዣ ብር (deposit) መጠን “ከወትሮው ከፍ ያለ መሆኑ”፤ በታቀደው ልክ ለማሳካት እንቅፋት መሆኑም አቶ መላኩ ተናግረዋል። ለማምረቻው ዘርፍ በ2016 ተመሳሳይ ወቅት የቀረበው የውጪ ምንዛሬ መጠን 274 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)