በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የግብጽ ተሳትፎ፤ “የትኛውንም ሀገር የማስፈራራት ዓላማ” እንደሌለው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ተናገሩ

የግብጽ በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ መሳተፍ “የትኛውንም ሀገር የማስፈራራት ዓላማ” እንደሌለው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ተናገሩ። ፕሬዝዳንቱ “የሶማሊያን ደህንነት እና መረጋጋት ለማስፈን” ያለመ ባሉት አዲሱ ሰላም አስከባሪ ውስጥ፤ የግብጽ “ተሳትፎ አዎንታዊ” እንደሆነ ገልጸዋል።

አል ሲሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት ዛሬ ሐሙስ ጥር 15 ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ጋር በካይሮ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ሐሰን ሼክ ወደ ካይሮ ያቀኑት በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተገናኝተው፤ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ በተስማሙ በ12ኛው ቀን ነው። 

ግብጽ እና ሶማሊያ ያላቸውን ግንኙነት ወደ “ስልታዊ አጋርነት (strategic partnership) ለማሳደግ የጋራ ፖለቲካዊ ቃል ኪዳን” እንደተፈራረሙ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ ተደርጓል። በሶማሊያ ያለው ሁኔታ ግብጽን ከ30 ዓመታት በላይ ሲያሳስብ የቆየ እንደሆነ በዚሁ መግለጫ ላይ የጠቀሱት ፕሬዝዳንት አልሲሲ፤ ሀገራቸው በሰላም አስከባሪው ተልዕኮ ውስጥ የሚኖራት ተሳትፎ በዋናነት “ለሶማሊያ ህዝብ ያላትን አጋርነት ለማሳየት ያለመ” እንደሆነ አስረድተዋል። 

የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መንግስት፤ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ የሚሳተፉ ሀገራት 11,000 ወታደሮች ለማዋጣት ቃል መግባታቸውን ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ማስታወቁ ይታወሳል። ተልዕኮው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በጸደቀበት ስብሰባ ላይ የሶማሊያ ተወካይ ባደረጉት ንግግር፤ በስምሪቱ የሚሳተፉ ወታደሮች ድልድል የተወሰነው በሁለትዮሽ ስምምነት እንደሆነ ገልጸው ነበር። 

ከሶማሌላንድ ጋር በተፈረመ የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት፤ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተልዕኮው አይሳተፉም የሚል አቋም ስታራምድ ቆይታለች። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ በቱርክ አሸማጋይነት በአንካራ ከደረሱበት “ቃል ኪዳን” በኋላ የሞቃዲሾ መንግስት አቋሙን አለሳልሷል። 

በመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ የተመራ የልዑካን ቡድን በሞቃዲሾ ያደረገውን ጉብኝት ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ በአዲሱ ተልዕኮ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ለማዋጣት ያቀረበችውን ጥያቄ ሶማሊያ ለማጤን ፈቃደኛ መሆኗን አስታውቃ ነበር። ከተያዘው ጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ ተልዕኮ፤ ከግብጽ በተጨማሪ የጅቡቲ፣ ኬንያ እና ኡጋንዳ  ወታደሮች ይካተቱበታል ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)