ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከባለቤታቸው፣ ከሚኒስትሮች እና ከሌሎችም እንግዶች ጋር በመሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በትላንትናው ዕለት ተዘዋውረው ጉብኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ጉብኝት በኋላ በሰጡት ገለጻ፤ በጅማ ከተማ ለተከናወኑ “የገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች “በትንሹ 15 ሺህ ቤቶች መፍረሳቸውን” ተናግረዋል።
በከተማይቱ የነበረ መስጂድ እና ከአንድ ሺህ በላይ የመቃብር ቦታ ቀድሞ ከነበሩባቸው ቦታዎች መነሳታቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የጅማ ከተማ ነዋሪዎች “ቤቶቻቸውን ሲያፈርሱም” ሆነ ቦታዎችን ለፕሮጀክቶቹ ሲያስረክቡ “ካሳ አለመጠየቃቸውን” አብይ በአድናቆት አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተወለዱበት በሻሻ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የጅማ ከተማ ህዝብ፤ ካሳ ከመጠየቅ ይልቅ “ ‘እስቲ ሃሳባችሁን አፍሱት፤ ልየው ነው’ ያለው” ሲሉም በገለጻቸው ላይ ጠቅሰዋል። “የጅማ አካባቢ ማህበረሰብ ለእነዚህ ህልሞች፣ ለእነዚህ ሃሳቦች መወለድ የነበረው ሚና፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትምህርት መሆን ያለበት ነው” ሲሉም አብይ በገለጻቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 350 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው ጅማ፤ ከሌሎች ቦታዎች በተለየ መንግስት ለሚያፈልቀው ሃሳብ “የተከታይነት” (followership) አመለካከት እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። “ሃሳብ እና መሰጠት ጥሩ ተከታይ ካላገኘ፤ ዕውን አይደረግም ብቻ ሳይሆን፤ ብትጀምረውም ይቆማል፣ ይፈርሳል፣ ወደኋላ ይመለሳል” ሲሉ አብይ የጉዳዩን አስፈላጊነት አስገንዝበዋል።
የጅማ ህዝብ “አስደማሚ እና ለማመን የሚከብድ ቁርጠኝነት አሳይቷል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “ሌላ ቦታ ሊታሰቡ፣ ሊሞከሩ የማይችሉ በጣም በርካታ ጉዳዮች፤ የጅማ ህዝብ በቅንነት አምኖ በሃሳቡ፣ ገንዘቡን፣ ጊዜውን፣ ጉልበቱን ሰውቶ፤ ይሄ ህልም እንዲከወን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል” ሲሉ የከተማይቱን ነዋሪ አሞግሰዋል።
“መልካም ነገር፣ ጥሩ ነገር፤ እንዲሁ በዋዛ አይመጣም። የትም ዓለም ያየነው መልካም ነገር፤ በብዙ ስቃይ የተወለደ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ “ጨከን ማለት አለብን” ሲሉ ተደምጠዋል። አብይ ባለፈው ሳምንት በጎበኙት የጎንደር ከተማን በምሳሌነት በማንሳትም፤ “በጣም ብዙ ጥሩ ስራ ተሰርቷል። መጨከን የሚያስፈልገው፤ የሚቀር ነገር ደግሞ አለ” ብለዋል።
“ጎንደር ትንሽ ጨከን ብለን ተጨማሪ ማፍረስ፣ ተጨማሪ መትከል ብናደርግ፤ ምንም ጥርጥር የለውም በአውሮፓ እንዳሉ ውብ ከተሞች ይሆናል”
– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
“ጎንደር ትንሽ ጨከን ብለን ተጨማሪ ማፍረስ፣ ተጨማሪ መትከል ብናደርግ፤ ምንም ጥርጥር የለውም በአውሮፓ እንዳሉ ውብ ከተሞች ይሆናል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንቱ ገለጻቸው ላይ ተናግረዋል። በጅማ የታየውን አይነት ስራ እንደ አርባ ምንጭ እና ባህር ዳር ባሉ ብዙ ቦታዎች መደገም እንዳለበትም አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)