በቤርሳቤህ ገብረ
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል 550 ሚሊዮን ዶላርን ያካተተ የብድር ስምምነት፤ ዛሬ ሰኞ ጥር 19፤ 2017 በፓርላማ ጸደቀ። የካፒታል ማሳደጊያው፤ ባንኩን “የተሻለ ተወዳዳሪ” እና በቀጠናው መስራት የሚችል “ጠንካራ ባንክ እንዲሆን የሚያስችለው” ነው ተብሏል።
ለመንግስታዊው ባንክ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውለው ገንዘብ፤ ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ለኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው 700 ሚሊየን ዶላር ብድር አካል ነው። በዓለም ባንክ ስር የሚገኘው ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ብድሩን የሰጠው፤ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓትን ለማጠናከር በማሰብ ነው።
ይህንኑ በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አጭር መግለጫ ያቀረቡት በፓርላማ ረዳት የመንግስት ተጠሪ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ፤ በብድሩ በዋነኛነት ተጠቃሚ የሚሆኑት ሶስት የመንግስት የገንዘብ ተቋማት እንደሆኑ አስታውቀዋል። ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ብድሩን ለካፒታል ማሳደጊያነት ከማዋል በተጨማሪ “መሰረታዊ የመዋቅር ማሻሻያ ለማድረግ” “እና “የዘርፉን የስጋት አስተዳደር ከአለም አቀፍ የባንኪንግ ደረጃዎች ጋር በማጣጣም ለማጎልበት” እንዲጠቀምበት የቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአጠቃላይ የብድሩ ማዕቀፉ ውስጥ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሻሻያ፣ ማዋቀር እና መልሶ ማቋቋም የተያዘው የገንዘብ መጠን 560 ሚሊዮን ዶላር ነው። ከዚህ ውስጥ 550 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ፤ ለባንኩ የካፒታል ማሳደጊያ የሚውል መሆኑን ለፓርላማ በቀረበው የማብራሪያ ሰነድ ላይ ሰፍሯል።
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፒታል ማሳደጊያ የሚውል ገንዘብ በፓርላማ እንዲጸድቅ ሲቀርብ፤ በአምስት ወራት ውስጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ባለፈው ጥቅምት ወር ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ አዋጅ፤ ለባንኩ የካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል 54 ቢሊዮን ብር የፈቀደ እንደነበር ይታወሳል።
በኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ ድርሻው ከፍተኛ የሆነው መንግስታዊው ባንክ፤ የተፈቀደለት ካፒታል አራት ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል። ባንኩ በገበያው ውስጥ ያለውን “ድርሻ” ይዞ መቀጠል እንዲችል ለማድረግ፤ የተከፈለውን ካፒታል “ደረጃ በደረጃ” ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ አዋጁን ለማብራራት የቀረበ መግለጫ አትቶ ነበር።
በዚህም መሰረት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ለማሳደግ የሚውል፤ የ54 ቢሊዮን ብር ቦንድ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲያወጣ የሚያስችል አዋጅ በፓርላማ እንዲጸድቅ ተደርጓል። “የመንግስት እዳ ሰነድ” የሚል ስያሜ ያለው ይህ አዋጅ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር 900 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የመንግስት ዕዳ ሰነድ (ቦንድ) እንዲያወጣ የሚፈቅድ ነው።
በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ላይ፤ የባንኩን የካፒታል ማሳደጊያ ያካተተ የብድር ስምምነት መቅረቡ ከፓርላማ አባላት ጥያቄ ተነስቶበታል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በርታ፤ “ባንክን በምናይበት ሰዓት በተሻለ የኢኮኖሚ ማመንጨት አቅም ላይ ያሉ ናቸው። በተለይ ንግድ ባንክ ሪፖርቱን ሲያቀርብ ‘ትርፋማ ነኝ’ የሚል ነው የምንሰማው። በምን መስፈርት ነው ለእነዚህ ተቋማት ይሄ ብድር ሊሰጥ የቻለው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ማሳደጊያ የተመደበው 660 ሚሊየን ዶላር ብድር፤ ለፓርላማው በ“ዝርዝር” አለመቅረቡ “ለቁጥጥር እና ማረጋገጥ” (check and balance) ስራ አስቸጋሪ እንደሆነ እኚሁ የፓርላማ ተናግረዋል። ለፕሮጀክቱ ትግበራ በብድር ስምምነቱ ላይ የተመደበውን ተጨማሪ ገንዘብም “ግልጽ ያልሆነ” ብለውታል።

ለጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፤ የንግድ ባንክ የካፒታል አቅም ማሳደግ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የተካተተ መሆኑን አስረድተዋል። የኢኮኖሚ ማሻሻያው “በማክሮ”፣ “በዘርፍ” እና “በመዋቅራዊ” መስኮች የተከፋፈለ እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል። በማክሮ ማሻሻያ ስር ካሉ ጉዳዮች አንዱ “የፋይናንሺያል ስርዓቱን ማጠናከር” የሚለው አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ ማዕቀፍ ከሚመለከታቸው ተቋማት አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ “የካፒታል አቅም” “ክፍተት” መታየቱን ዶ/ር እዮብ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ባንክ ጋር በበርካታ ዘርፎች ስራዎች እንደሚያከናወን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የካፒታል አቅም ማሳደግ በአሁኑ የብድር ስምምነት ውስጥ “ቀዳሚ ትኩረት” እንዲሰጠው ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን ገልጸዋል።
“አብዛኛው ገንዘብ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፒታል ማሳደጊያ የሚውል ነው። ይሄ ማለት ገንዘቡ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገባል። የካፒታል አቅሙን ይጨምራል። ባንኩ የተሻለ ተወዳዳሪ መሆን ይችላል። የውጭ ባንኮች ሲመጡ መወዳደር የሚችል፣ regionally መስራት የሚችል ጠንካራ ባንክ እንዲሆን [ያደርገዋል]” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው አብራራተዋል።
“አብዛኛው ገንዘብ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፒታል ማሳደጊያ የሚውል ነው። ይሄ ማለት ገንዘቡ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገባል። የካፒታል አቅሙን ይጨምራል። ባንኩ የተሻለ ተወዳዳሪ መሆን ይችላል። የውጭ ባንኮች ሲመጡ መወዳደር የሚችል [ያደርገዋል]”
በብድሩ የሚከናወነው ፕሮጀክት “የፋይናንስ ሴክተሩን መረጋጋት እንዲረጋገጥ የሚያግዝ ነው” ሲሉም ዶ/ር እዮብ አስገንዝበዋል። ይህን ማብራሪያ ተከትሎ፤ የብድር ስምምነቱ በሶስት የፓርላማ አባላት ድምጸ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)