ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ጠቅላላ ጉባኤው የከፍተኛ አመራሮች ምርጫ ሊያካሄድ ነው

በደምሰው ሽፈራው

ከመጪው አርብ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚካሄደው የገዢው ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ፓርቲውን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮች እንደሚመረጡ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ። ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የብልጽግና ፓርቲ “ከፍተኛ የአመራር አካል” የሆነው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲውን ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደንብ የማጽደቅ እና የማሻሻል ስልጣን ያለው ነው። ፓርቲው የሚመራባቸውን “አጠቃላይ አቅጣጫዎችን እና ውሳኔዎች” የማስቀመጥ ኃላፊነት የተጣለውም በጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው። 

የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ፤ የጠቅላላ ጉባኤ ማካሄጃ ጊዜ ከሶስት ዓመት መብለጥ እንደሌለበት ይደነግጋል። አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመጋቢት 2014 ዓ.ም ያካሄደው ብልጽግና ፓርቲ፤ ሁለተኛው መደበኛ ስብሰባውን የሚያደርገው ከሁለት ዓመት ከ10 ወር በኋላ ነው።  

ከአርብ ጥር 23 እስከ እሁድ ጥር 26 በአዲስ አበባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በሚካሄደው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ፤ በፓርቲው ፕሮግራም እና ደንብ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች የሚጸድቁበት እንደሆነ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ባለፈው ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች አፈጻጸም በአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚገመገም አቶ አደም ተናግረዋል። 

“ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ብልጽግና ፓርቲ “በሚቀጥሉት አመታት ሊያሳካቸው ያሰባቸውን ስኬቶች በተመለከተ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት” እንደሆነ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ ፓርቲውን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮችም በዚሁ ጉባኤ ላይ እንደሚመረጡ አቶ አደም አክለዋል። 

ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ከምስረታው ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት በመምራት ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው። በአንደኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከተመረጡ ሁለት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንቶች አንዱ የሆኑት አቶ አደም ፋራህ፤ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊም ናቸው።

በመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ተደርገው የነበሩት የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በተደረገ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ መሰናበታቸው ይታወሳል። እርሳቸውን በመተካት በዚሁ የኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡት የአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው።

የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች የኃላፊነት ዘመን ጣራ 10 ዓመት እንደሆነ በብልጽግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ሰፍሯል። በሁለተኛው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች ምርጫ እንደሚካሄድ ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ከእነዚህ ከፍተኛ አመራሮች በተጨማሪ የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ በተመሳሳይ መልኩ እንደሚካሄድ ምንጮቹ ገልጸዋል። የፓርቲው የኢንስፔክሽን እና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላትም በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚመረጡ ምንጮች አክለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በአንደኛው ጉባኤ ያስመረጣቸው የኢንስፔክሽን እና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላትን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውድቅ አድርጎ እንደነበር አይዘነጋም። ቦርዱ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፤ ፓርቲው አስቸኳይ ጉባኤ በመጥራት በህዳር 2015 ዓ.ም የኮሚሽን አባላቱን በድጋሚ መርጧል።

በአስቸኳይ ጉባኤው የተመረጡት የኮሚሽኑ አባላት፤ በአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ “በቀጥታ እንደሚሳተፉ” አቶ አደም ገልጸዋል። በተመሳሳይ መልኩ በጠቅላላ ጉባኤ የመሳተፍ ዕድል የሚያገኙት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንደሆኑም አቶ አደም አመልክተዋል። የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያለው የአባላት ብዛት 225 ነው። 

ከእነዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀቶች የተወከሉ አባላትም፤ በመጪው ጠቅላላ ጉባኤ ይሳተፋሉ። የጉባኤው ተሳታፊ የሚሆኑት እነዚህ የፓርቲው አባላት፤ “ድምጽ የመስጠት መብት ያላቸው” እንደሆኑ አቶ አደም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።  

በብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በድምጽ ከሚሳተፉ 1,700 አባላት በተጨማሪ ከአገር ውስጥ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል የተወከሉ ግለሰቦች “በተጋባዥ እንግድነት” ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚሁ ጉባኤ ላይ ከሀገር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ የ15 የተለያዩ አገራት ፓርቲ ተወካዮችም ይሳተፉበታል ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)