የግብርና ምርምር ተቋማት 312 ሄክታር መሬት “መነጠቃቸውን” የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ይፋ አደረገ

የግብርና ምርምር እና የእንስሳት ብዜት ተቋማት “312 ሄክታር መሬት መነጠቃቸውን” በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይፋ አደረገ። መሬታቸውን ከተነጠቁ መካከል አንጋፋዎቹ የሆለታ፣ የጅማ እና የቢሾፍቱ የግብርና ምርምር ማዕከላት እንደሚገኙበት ቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል።

ጉዳዩ የተነሳው የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ የመስሪያ ቤታቸውን የ2017 የመጀመሪያ መንፈቅ የስራ ሪፖርት፤ ትላንት ሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው። ሚኒስትሩ ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ ቋሚ ኮሚቴው ከሰጣቸው አስተያየቶች እና ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል የግብርና ምርምር ተቋማትን የተመለከተው ይገኝበታል።

ቋሚ ኮሚቴው ያዘጋጀውን ጥያቄ እና አስተያየት በንባብ ያቀረቡት አቶ አለሙ ዳምጠው የተባሉ የፓርላማ አባል “በአንዳንድ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ያሉ የግብርና ምርምር እና የእንስሳት ብዜት ተቋማት፤ የመሬት ይዞታቸው በከተማ አስተዳደሮች እየተነጠቀ ይገኛል” ብለዋል። ተቋማቱ እና በስራቸው የሚገኙ ንዑስ ማዕከላት፤ ለምርምር እና ለስራቸው የሚጠቀሙበት “መሬታቸውን እያጡ” በመሆኑ “ህልውናቸው ለአደጋ ተጋልጧል” ሲሉ የፓርላማ አባሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት አጽንኦት ሰጥተዋል። 

“የሆለታ፣ የጅማ የቁልምሳ፣ የቢሾፍቱ ማዕከላት እና ሌሎችም በጠቅላላው ወደ 312 ሄክታር የምርምር መስሪያ መሬታቸውን የተነጠቁ እና በስጋት ላይ ያሉ” መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው በቅርቡ ክትትል ሲያደርግ ከተቋማቱ ያሰባሰበውን መረጃ ዋቢ አድርጎ ለምክር ቤቱ አስታውቋል። የክልል መንግስታት እና የከተማ አስተዳደሮች የወሰዱት እርምጃ፤ የምርምር እና የእንስሳት ብዜት ተቋማት “ለግብርናው ዕድገት ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ለመወጣት እንቅፋት ሆኖባቸዋል” ሲልም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል። 

የጉዳዩን አሳሳቢነት የቀድሞው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፈቶ ኢሴሞ ባለፈው ዓመትም ለምክር ቤቱ አንስተው ነበር። ምክር ቤቱ የግብርና ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ባዳመጠበት ስብሰባ የተገኙት ዶ/ር ፈቶ፤ “በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ብዙ የመሬት ነጠቃዎች እየተካሄዱ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።

የምርምር ማዕከሉ ከ30 ዓመታት በላይ የተገለገለበት “ካርታ” እና “ፕላን” ጭምር ያለው በኦሮሚያ ክልል ኮፈሌ አካባቢ የሚገኝ የምርምር ጣቢያ ቦታ “ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ እንዳንጠቀምበት ተደርገናል” ሲሉ የቀድሞው የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በወቅቱ አስረድተዋል። በአማራ ክልል አረርቲ አካባቢ የሚገኙ ሶስት ቦታዎችም ከማዕከሉ የተነጠቁ መሆናቸውን በተጨማሪ ማሳያነት አቅርበዋል።

“ይሄ ነገር አሳሳቢ ነው” ሲሉ በግንቦት 2016 በተካሄደ የፓርላማ ስብሰባ ላይ የተናገሩት ዶ/ር ፈቶ፤ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቤቱታ አቅርቦ “ብዙ ቦታዎች ላይ ጣልቃ ገብነት ስራዎች ቢሰሩም አሁንም በተመሳሳይ መልኩ ነጠቃዎች እየተካሄዱ ነው” ብለው ነበር። በትላንቱ የፓርላማ ልዩ ስብሰባ ላይ ስለጉዳዩ ምላሽ የሰጡት የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ ችግሩ መኖሩን አምነዋል።  

የግብርና የምርምር ማዕከሎችን ጨምሮ አብዛኞቹ የመንግስት ተቋማት “በጣም ለረዥም ጊዜ የቆየ ቦታ የያዙት” “የይዞታ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው” መሆኑን ገልጸዋል። ጉዳዩ ከዚህ በፊት “ችግር” እንዳልነበር ያነሱት ዶ/ር ግርማ፤ የግብርና ምርምር ተቋማት የይዞታ ማረጋገጫ ለማግኘት ሲጠይቁ ከከተሞች አጥጋቢ ምላሽ እንደማይሰጣቸው አመልክተዋል። 

ከተሞች “የራሳቸውን ማስተር ፕላን እየሰሩ” “የመሬት አጠቃቀሙን ቀይረናል” የሚል ምክንያት ለተቋማቱ እንደሚሰጧቸውም ሚኒስትሩ አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት “መሬቶች የመሻማት ሁኔታዎች አጋጥመዋል” ብለዋል። ችግሩን በአካል በመገኘት ጭምር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ዶ/ር ግርማ፤ የግብርና ምርምር ማዕከላት “ራሳቸውን relevant ማድረግ አለባቸው” የሚል ምክር ለግሰዋል። 

“ከዚህ በፊት የቢሾፍቱ የምርምር ማዕከል ጤፍ እና ሽምብራ ላይ ምርምር የሚሰራ ከሆነ፤ አሁን ደግሞ ከተማ ግብርና ላይ ምርምር መስራት አለበት። ‘ለከተሞች ቴክኖሎጂ generate ማድረግ አለበት’ የሚለው ላይ ነው የተስማማነው” ሲሉ መስሪያ ቤታቸው ለችግሩ መፍትሔ ለማበጀት የተከተለውን አካሄድ አብራርተዋል።“ይህ የሚደረግ ከሆነ እኛንም ይጠቅመናል” ብለዋል የግብርና ሚኒስትሩ።  

የሆለታ የግብርና ምርምር ማዕከል ለገጠመው ችግር መፍትሔ ለማስገኘትም ተመሳሳይ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የምርምር ማዕከሉ የተሻሻሉ እና አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና መረጃዎችን በማመንጨት፤ “የደጋው አካባቢ የግብርና ምርት እድገት እንዲኖረው” ለማድረግ በማሰብ የተቋቋመው በ1958 ዓ.ም ነው።  

የግብርና ሚኒስትሩ የሆለታን እና የሌሎችን የምርምር ማዕከላት ችግር ለመፍታት፤ የፓርላማ አባላትን ድጋፍ ጭምር ጠይቀዋል። “አንዳንድ ቦታ ላይ ተገቢነት በሌለው መንገድ እነዚህን ሰፋ ተብለው የተቀመጡትን የምርምር ማዕከላት ለጊዜያዊ ችግሮች ለመወጣጫ የሚደረጉባቸው ሁኔታዎች አሉ” ያሉት ዶ/ር ግርማ፤ መሬት የሚሰጡት የክልል መንግስታት በመሆናቸው የፓርላማ አባላት በተመረጡባቸው አካባቢዎች ባሉ መዋቅሮች ላይ ጫና በማሳደር እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)