ኢዜማ ከመጪው ምርጫ ጋር “የተያያዘ በሚመስል መልኩ”፤ “አባላቶቼ እየታሰሩብኝ ነው” አለ

በደምሰው ሽፈራው

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) 75 አባላቶቹ በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታወቀ። ፓርቲው በአባሎቹ ላይ እስር እና ማዋከብ እየተፈጸመ የሚገኘው፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ ጋር “የተያያዘ በሚመስል መልኩ ነው” ሲል ወንጅሏል። 

ኢዜማ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 20፤ 2017 ባወጣው መግለጫ፤ በአባሎቹ ላይ ድርጊቶቹ እየተፈጸሙ ያሉት በአማራ፣ ሀረሪ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንደሆነ ገልጿል። ፓርቲው “ታስረውብኛል” ካላቸው አባላቶቹ ውስጥ አብዛኞቹ የሚገኙት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ፣ ዘይሴ ቀበሌ መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። 

የዘይሴ ቀበሌ በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ ኢዜማ የተወካዮች ምክር ቤት ያሸነፈበት ነው። የኢዜማ የህግ እና የአባላት ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስዩም መንገሻ፤ በቀበሌው ባሉ የኢዜማ አባላት ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው እስር እና መዋከብ “ከፍተኛ” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

አቶ ስዩም እነዚህ እርምጃዎች በቀበሌው በሚገኙ የጸጥታ አካላት እየተወሰዱ ያሉት፤ ኢዜማ በአካባቢው “ጠንካራ የፖለቲካ መሰረት ስላለው ነው” ባይ ናቸው። “የፖለቲካ መሰረታችን ጠንካራ የሆነባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም ጠንካራ ዱላ አለ። ዘይሴ አንዱ ነው” ይላሉ የፓርቲው የመምሪያ ኃላፊ። 

በዘይሴ አካባቢ ያለው ሁኔታ ባለፈው ጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በተካሄደ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ተነስቶ ነበር። ከዘይሴ ልዩ የምርጫ ክልል ተመርጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አብርሃም አሞሼ፤ የእስር እርምጃው እየተወሰደ ያለው ከምርጫው በኋላ ካሉት ጊዜያት ጀምሮ እንደሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።   

“በክልሉ ምክር ቤት የዘይሴ ህዝብ ተወካይን ጨምሮ፤ ባለሀብቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የኢዜማ ፓርቲ አመራር አባላት፤ በአጠቃላይ ከ120 በላይ ሰዎች ወንጀል ባልሰሩበት በሀሰት ክስ ተከሰው በእስር ላይ ይገኛሉ’’ ሲሉ የፓርላማ አባሉ በወቅቱ አስታውቀዋል። 

ኢዜማ በዛሬው መግለጫው በዘይሴ ቀበሌ በእስር ላይ የሚገኙ አባላቱ ቁጥር 50 መሆኑን ገልጿል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ በተመሳሳይ ክልል በሚገኘው አሪ ዞን፣ ባኮ ጋዘር 1 ምርጫ ክልል የሚገኙ አባላቱ “በጅምላ እየታሰሩ” መሆኑን አክሏል። ድርጊቱን እየፈጸሙ የሚገኙት “የገዢው የብልጽግና ፓርቲ እና የመንግስት አካላት” ናቸው ሲል ፓርቲው በመግለጫው ከስሷል።

እነዚህ አካላት በአሪ ዞን “ከብልጽግና ፓርቲ ውጪ የሚንቀሳቀስ ሊኖር አይችልም” የሚል “ኢ-ዴሞክራሲያዊ” አካሄድ እንደሚከተሉም ኢዜማ አመልክቷል። ይህን መንገድ በመከተልም 18 የኢዜማ አባላት በዞኑ ታስረው እንደሚገኙ ፓርቲው ገልጿል። የአካባቢው ፖሊስ የፓርቲውን አባላት ለሁለት ጊዜ ያህል ፍርድ ቤት ማቅረባቸውን የጠቀሰው የኢዜማ መግለጫ፤ “ማስረጃ ባለማቅረቡ” ለሶስተኛ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ አብራርቷል።

ኢዜማ በሀረሪ ክልል የታሰረበት አንድ አባል መሆኑን በዛሬው መግለጫው ላይ አመልክቷል። እኚህ የፓርቲው አባል የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ መሆናቸውን የጠቀሰው ኢዜማ፤ ከጥር 8፤ 2017 ጀምሮ “ያለ በቂ ምክንያት” “የዋስ መብታቸው ተከልክሎ” በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጿል። 

ማህሌት ዘውዱ የተባሉት የፓርቲው አባል ለእስር የተዳረጉት፤ በክልሉ እየተካሄደ ካለው የኮሪደር ልማት ስራ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የኢዜማ የህግ እና የአባላት ደህንነት መምሪያ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በሐረር ከተማ የኢዜማ አስተባባሪ የሆኑት ማህሌት የታሰሩት፤ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው ለሚነሱ ነዋሪዎች የተሰጠን ደብዳቤ በክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በማቅረባቸው እንደሆነ የፓርቲው ኃላፊ አስረድተዋል።

የሀረሪ ክልል የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ባለስልጣን ለአባድር ወረዳ ነዋሪዎች የላከው ይህ ደብዳቤ፤ ለኮሪደር ስራ ልማት ተነሺዎች “መተማመኛ ለመስጠት” የተጻፈ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ደብዳቤ፤ ነዋሪዎቹ ደብዳቤው ከደረሳቸው ቀን ጀምሮ “ንብረታቸውን በአስቸኳይ እንዲያነሱ” ያሳስባል።

የክልሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ ለኮሪደር ስራ ልማት ተነሺዎች እየተሰራ እንደሆነ በደብዳቤው የተገለጸው “የካሳ ግምት” ሳይጠናቀቅ ነው። ለተነሺዎቹ የካሳ ግምት የሚከፈለው፤ የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ እንዲሁም የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ባለስልጣን “በወረዳዎች በኩል” የጠየቋቸው “ማስረጃዎች ሲሟሉ” እንደሆነ በደብዳቤው ላይ ሰፍሯል። 

“በቢሮ ውስጥ የተጀመረው ሂደት ሲጠናቀቅ ካሳ የሚከፈል መሆኑን” የክልሉ መስሪያ ቤቱ በደብዳቤው ላይ አስታውቋል። የኢዜማ የሐረር ከተማ አስተባባሪ ይህን ደብዳቤ ለክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ያቀረቡት “ለውይይት” እንደነበር አቶ ስዩም ገልጸዋል። “ሰላማዊ ትግልን እንደዚህ እያደረግህ ከከለከልከው፤ ወደማይፈለገው አዙሪት ውስጥ እንገባለን” ሲሉም የኢዜማው የመምሪያ ኃላፊ የአባላቸው እስር ኮንነዋል። 

“ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው በአባሎቻችን ላይ የሚደርሰው እስር ወከባና ግፍ፤ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ላይ አደጋ መደቀን እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቁርጠኛ አለመሆን አድርገን እንወስደዋለን”

– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)

ኢዜማ በዛሬ መግለጫው ማጠቃለያ ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ አስተጋብቷል። “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው በአባሎቻችን ላይ የሚደርሰው እስር ወከባና ግፍ፤ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ላይ አደጋ መደቀን እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቁርጠኛ አለመሆን አድርገን የምንወስደው ሲሆን ሀገራችንን ወደኋላ እየጎተቱ የተለመደ አዙሪት ውስጥ እንዳይከተን ያሰጋናል” ሲል ኢዜማ በመግለጫው አመልክቷል። ፓርቲው አባላቱ ከእስር ነጻ እንዲሆኑም በአጽንኦት ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)