በቤርሳቤህ ገብረ
የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊዎች የሩብ፣ የመንፈቅ፣ የዘጠኝ ወር አሊያም የዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለማቅረብ ወደ ፓርላማ በሚመጡበት ጊዜ ሁልጊዜም ከአንድ ጉዳይ ጋር የተያያዙ በርከት ያሉ ጥያቄዎች ይቀርቡላቸዋል። ጉዳዩ አብዛኛውን የሀገሪቱን ህዝብ ብዛት የሚወክለውን አርሶ አደር በቀጥታ የሚመለከተው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት ነው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ሰኞ ጥር 19፤ 2017 ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ላይ ይህ ጉዳይ ተነስቶ መወያያ ሆኗል። ለልዩ ስብሰባው በቀዳሚነት የተያዘው አጀንዳ፤ “የግብርና ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ማዳመጥ” የሚል ነበር።
በዚህም መሰረት የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ የመስሪያ ቤታቸውን የመንፈቅ ዓመት የስራ አፈጻጸም፤ ግማሽ ሰዓት ያህል ወስደው በንባብ አሰምተዋል። ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ካነሷቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የአፈር ማዳበሪያን የተመለከተው ይገኝበታል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለዘንድሮ በጀት ዓመት ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ የሚውል 1.3 ቢሊዮን ዶላር እና 156 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ዶ/ር ግርማ በሪፖርታቸው ላይ አስታውሰዋል። በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት፤ ለመኸር፣ ለበልግ የምርት ወቅቶች እና ለመስኖ ልማት የሚውል 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት በእቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ የተገዛው እና ከባለፈው የምርት ዘመን “የከረመ” 3.15 ሚሊየን ኩንታል በድምሩ 5.78 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ ለመስኖ ልማት ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አመልክተዋል። ለዘንድሮ የምርት ዘመን የሚውለው ቀሪ የማዳበሪያ ግዢ፤ “የተሻለ ዋጋ እና ሁኔታ” እንዲሁም የምርቶችን ፍላጎት “ታሳቢ” ባደረገ መልኩ እንደሚፈጸምም አክለዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ሪፖርት ከተጠናቀቀ በኋላ በተከተለው የጥያቄ እና መልስ ጊዜ የመናገር ዕድል ያገኙ የፓርላማ አባላት የአፈር ማዳበሪያን ጉዳይ በድጋሚ አንስተዋል። የግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን የመከታተል ኃላፊነት ያለበት የፓርላማው የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ባደረገው የክትትል እና ቁጥጥር ስራ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በማድረስ ረገድ መዘግየት እንዳስተዋለ አስታውቋል።

የቋሚ ኮሚቴውን አስተያየት እና ጥያቄ በንባብ ያቀረቡት አቶ አለሙ ዳምጠው የተባሉ የፓርላማ አባል፤ በበልግ እና መስኖ እርሻ በቅርቡ በሚጀምሩ ክልሎች ባሉ መጋዘኖች የተከማቸ የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሮች ዘንድ መድረስ ላይ ችግር እንዳለ ለማወቅ መቻሉን ገልጸዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ አለሙ፤ በስርጭት ረገድ ለሚስተዋለው ችግር “ብልሹ አሰራር፣ ፍትሃዊ ያልሆነ ስርጭት እና ቅድሚያ የሚፈለገው የማዳበሪያ አይነት ዳፕ የዘር ጊዜ ጠብቆ አለመድረስ” ምክንያት መሆኑን ዘረዝረዋል።
አቶ አለሙ ማዳበሪያን የተመለከተ የቋሚ ኮሚቴውን የክትትል አስተያየት የቋጩት “ለክልሎች የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ በኩል ምን እየተሰራ ነው?” የሚል ጥያቄ ለግብርና ሚኒስትሩ በማቅረብ ነው። እርሳቸውን ተከትሎ የመናገር ዕድል በአፈ ጉባኤው የተሰጣቸው የፓርላማ አባላትም ተያያዥ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
አቶ ነዚፍ ዝናብ የተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል፤ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ “በጣም መዘግየት” የታየበት ነበር ሲሉ ተችተዋል። በምርት ዘመኑ ለማቅረብ ከታቀደው 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን የቀረበው 3.13 ሚሊዮን ኩንታል እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ነዚፍ፤ የቀረውን “22 ሚሊዮን ኩንታል ማቅረብ ይቻላል ወይ?” ሲሉ ጥያቄ ሰንዝረዋል። ይህ አካሄድ የግብርና ምርት ላይ ችግር ይፈጥር እንደሆነ እና በምን መልኩ ለመፍታት እንደታሰበም ማብራሪያ ጠይቀዋል።

ጥያቄዎቹን ተከትሎ ምላሽ የሰጡት የግብርና ሚኒስትሩ፤ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት “በጣም ለረጅም ጊዜ የቆየ ችግር” እንደሆነ ተናግረዋል። ከዓመታት በፊት ከወረዳ አንስቶ እስከ ክልል ድረስ፤ የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር በመጋዘን “የሚበሰብስበት” እና “የሚያድርበት ጊዜ” እንደነበርም አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ለአፈር ማዳበሪያ ያለው ፍላጎት እንደጨመረ የገለጹት ዶ/ር ግርማ፤ “ይህ እንደ ስጋት የሚታይ ነገር አይደለም” ሲሉ ለፓርላማ አባላት ማስተማመኛ ሰጥተዋል።
በአርሶ አደሮች ዘንድ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መጨመር ተገቢውን ምላሽ ለመስጠትም፤ የግዢ ስርዓቱ መመሪያ ባለፈው ዓመት መቀየሩን ተናግረዋል። ቀድሞ የነበረውን የግዢ ስርዓት “obsolete የሆነ፣ እሴት የማይጨምር እና የተንዛዛ” የግብርና ሚኒስትሩ ጠርተውታል። ነባሩን መመሪያ ከመቀየር ባሻገር የአፈር ማዳበሪያን ግዢ የሚያስፈጽም ቦርድ “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሰጡት አቅጣጫ” መቋቋሙንም በበጎ ጎን አንስተዋል።
በዚህ የግዢ ቦርድ ውስጥም የውጭ ምንዛሬ እና የብድር አርቦትን እንደዚሁም የማጓጓዝ ስራን የሚወስኑ አመራሮች መካተታቸውን ዶ/ር ግርማ አስረድተዋል። በቦርዱ አማካኝነትም፤ የአፈር ማዳበሪያን በቀጥታ ድርድር መግዛት እና ከአምራቾች የሚገዛበት ደረጃ ላይ መደረሱን አብራርተዋል። ይህ ማሻሻያ ከመደረጉ በፊት የአፈር ማዳበሪያ በአንድ ጨረታ ለሁሉም ወቅቶች ይገዛ እንደነበር የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ባለፈው ዓመት ብቻ በተለያየ ጊዜ 15 ጨረታዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል። በዚህም 20 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

የግብርና ወቅቶች አልፎ የሚደርስ የማዳበሪያ ስርጭትን በተመለከተም፤ የግብርና ሚኒስትሩ በትላንቱ ማብራሪያቸው ምላሽ ሰጥተዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት ከክልሎች ጋር በመሆን ለየትኛው ወቅት፣ ምን ያህል ማዳበሪያ ያስፈልጋል? የሚለውን የመለየት ስራ መሰራቱን አስረድተዋል። “ከክልሎች ጋር ባደረግነው ውይይት፤ የፍላጎት ወቅቶች ለይተናል። ደቡብ ምዕራብ መቼ ነው ማዳበሪያ የሚፈልገው? በልግ መቼ ነው የሚገባው? መኸር መቼ ነው የሚወጣው? የሚለውን ለይተናል” ያሉት ዶ/ር ግርማ፤ ፍላጎቱ ከግዢ ስርዓቱ ጋር እንዲጣጣም መደረጉን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በግዢ ወደ ሀገር ውስጥ ከምታስገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነው 55 በመቶ የሚፈለገው ለመኸር ወቅት ነው። በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የበጋ ወቅት እና የመስኖ ልማት ነው። ለሁለቱ የሚፈለገው የአፈር ማዳበሪያ መጠን፤ በዓመት ውስጥ ከሚታቀደው 25 በመቶውን ይሸፍናል። ቀሪው 20 በመቶ የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ለበልግ ወቅት የሚውል ነው።
የፌደራል መንግስት የፍላጎት እና የወቅት ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ የአፈር ማዳበሪያን ለክልሎች በማሰራጨት ላይ እንደሚገኝም የግብርና ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። የክልሎችን ፍላጎት በማገናዘብም ለሚቀርብላቸው የማዳበሪያ መጠን ላይ ጭማሪ መደረጉንም ገልጸዋል። ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ይቀርብ የነበረው የማዳበሪያ መጠን 800 ሺህ እንደነበር በምሳሌነት የጠቀሱት ዶ/ር ግርማ፤ በአሁኑ ወቅት ከዚህ እጥፍ ሆኖ በመቅረብ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

በጅቡቲ ወደብ የደረሰ የአፈር ማዳበሪያን በቶሎ ወደ ክልሎች ለማጓጓዝ እየተደረገ ያለውን ጥረትም የግብርና ሚኒስትሩ በትላንቱ ማብራሪያቸው አንስተዋል። ከትራንስፖርት ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በዚህ ሳምንት በቀን ከ80 ሺህ እስከ 100 ሺህ የአፈር ማዳበሪያ እየተጓጓዘ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። “ተሳካልን ብለን መናገር የምንችለው፤ ከጅቡቲ እስከ ክልሎች መጋዘን ጋር ብቻ ማድረስ ሳይሆን፣ አርሶ አደር ጋር ሲደርስ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
በፓርላማ አባላቱ ጥያቄ የተነሳው፤ የአፈር ማዳበሪያን ከክልል መጋዘኖች ወደ አርሶ አደሮች በማድረስ ላይ የሚስተዋለው መዘግየት እርሳቸው በሚመሩት መስሪያ ቤት ምክንያት የተከሰተ እንዳልሆነም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። “[እንደ] ፌደራል መንግስት ከእኛ የሚጠበቀው ማዳበሪያውን ገዝቶ ማዕከላዊ መጋዘን ማድረስ ነው። ከማዕከላዊ መጋዘን ወደ ህብረት ስራ ማህበራት እና ወደ መጋዘን የሚያሰራጩት ክልሎች ናቸው። እዚህ አካባቢ ላይ የበለጠ ድጋፍ እና ክትትል፤ ከቋሚ ኮሚቴው ጋር ጨምሮ ስናደርግ ነው የቆየነው” ብለዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ፍትሃዊነትን በተመለከተ፤ ማዳበሪያ ተገዝቶ፣ ድጎማ ተደርጎ ሲቀርብ የነበረው ለአራት ዋና ዋና ክልሎች ብቻ እንደነበር ዶ/ር ግርማ አስታውሰዋል። “ይሄ የፍትሃዊነት ጉድለት የነበረበት ነው። አሁን እያደረግን ባለነው ሪፎርም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሁለት አመት በፊት ወደማዳበሪያ ስርጭት ስርአት ገብቷል። አምና አፋር ክልል የገባበት ሁኔታ አለ። ዘንድሮ የመጨረሻ ሶማሌ እና ጋምቤላ ክልል ቀጥታ በእነሱ ቦታ ላይ ማዳበሪያ እናደርሳለን። ስለዚህ ማዳበሪያ መግዛት ብቻ ሳይሆን የመጠቀም መጠናቸው አነስተኛ ቢሆንን ያቺኑ ሚፈልጓትን ፍትሃዊነት እና ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየሰራን ነው” ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)