መኢአድ ፓርቲውን በፕሬዝዳንት እና በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚመሩ አዲስ አመራሮችን መረጠ 

በደምሰው ሽፈራው

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ትላንት እሁድ ጥር 25፤ 2017 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲው ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ አብርሃም ጌጡን ፓርቲውን እንዲመሩ መረጠ። ፓርቲው በዚሁ ጉባኤው፤ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ማሻሻያ አድርጓል።

በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ መሰረት በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ህጋዊነት ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ቢያንስ በሶስት ዓመት አንድ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አለባቸው። ሀገር አቀፍ ፓርቲ የሆነው መኢአድ፤ በትላንትናው ዕለት ያካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለ10ኛ ጊዜ የተካሄደ ነው።

በአዲስ አበባ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመኢአድ ዋና ጽህፈት ቤት በተካሄደው በትላንትናው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ 550 ገደማ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። በዚሁ ጉባኤ ላይ በተደረገው የአመራር ምርጫ፤ መኢአድን ስድስት ለሚጠጉ ዓመታት ሲመሩ በቆዩት አቶ ማሙሸት አማረ ምትክ አቶ አብርሃም ጌጡ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። 

አቶ አብርሃም በአቶ ማሙሸት የኃላፊነት ዘመን የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል። አዲሱ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ይዘው የቆዩትን የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታ በጉባኤው ምርጫ የተረከቡት አቶ ሰማኝ አብርሃም ናቸው። 

ፓርቲው ቀድሞ በነበረው አደረጃጀት የነበረው የምክትል ፕሬዝዳንትነት የኃላፊነት ቦታ፤ በዚህኛው ጉባኤ በተደረገ የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ እንዲሰረዝ ተደርጓል። አዲሱ መተዳደሪያ ደንብ፤ ከዚህ ቀደም የነበረውን የፓርቲውን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብዛት ከ21 ወደ 13 ቀንሷል። 

መኢአድ በእሁዱ ጉባኤው ካሻሻላቸው የመተዳደርያ ደንብ አንቀጾች መካከል፤ ፓርቲው አመራሮቹን ለመምረጥ ተግባራዊ ሲያደርገው የቆየውን የድምጽ አሰጣጥ ስርአት የሚመለከተው ይገኝበታል። እስካሁን በስራ ላይ በቆየው የመኢአድ መተዳደሪያ ደንብ፤ ፓርቲው የአመራር ምርጫ የሚያካሄደው እጅ በማውጣት እና በሌሎችም ማንኛውም መንገድ እንደሆነ ሰፍሯል።

ፓርቲው ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በሚያዝያ 2014 ዓ.ም. ባካሄደበት ወቅት፤ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አባላትን ያስመረጠው የጉባኤው ተሳታፊዎችን እጅ በማስወጣት ነበር። ይህ አካሄድ በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ ከተደነገገው ስርዓት ጋር የሚስማማ ባለመሆኑ፤ መኢአድ በዚህ አሰራሩ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ በታህሳስ 2015 ዓ.ም. አስተላልፎ ነበር። 

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ፤ በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ምርጫ “ግልጽ፣ ነፃና ፍትሐዊ” እንዲሁም “በሚስጥር በሚሰጥ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት” መካሄድ እንዳለበት ይደነግጋል። ይህን መሰረት በማድረግ መተዳደሪያ ደንቡን ያሻሻለው መኢአድ፤ የከፍተኛ አመራሮቹን ምርጫ ያደረገውም በዚሁ አግባብ መሆኑን የፓርቲው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

መኢአድ ይህንን ጨምሮ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ጋር “የማይጣጣሙ እና የአተረጓጎም ችግር ያለባቸው ናቸው” በተባሉ አራት የፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ምንጮች ገልጸዋል። ማሻሻያ ከተደረገባቸው አንቀጾች ውስጥ የፓርቲው የቀጠና ኃላፊዎችን የሚመለከተው አንዱ መሆኑን ምንጮች አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)