የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን አዋጅ እንዲያሻሽል፤ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ለተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት አቅጣጫ ሰጠ 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የቦርድ ውክልናን ጨምሮ “በርካታ ክፍተቶች አሉበት” ያለውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ እንዲሻሻል ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ። ባለስልጣኑ “አላሰራ ያሉ አዋጆችን እንዲሻሻሉ ለማድረግ” ለሚያከናወናቸው ስራዎች፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ተገቢውን ድጋፍ” እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው የፓርላማው የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን የስራ እንቅስቃሴ ትላንት ሰኞ ጥር 26፤ 2017 ተዘዋውሮ በተመለከተበት ወቅት ነው። በመስክ ምልከታው የተገኙ አምስት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የስራ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞችን እና ተገልጋዮችን ማነጋገራቸውን ከተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚሁ ጊዜ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን ያለፉትን የስድስት ወራት የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ፤ የመስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገለጻ አድርገዋል። አቶ ሳምሶን በዚሁ ገለጻቸው፤ ባለስልጣኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅን ለማሻሻል “እየሰራ” እንደሆነ መናገራቸውን የተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ ላይ አስፍሯል።

አሁን በስራ ላይ ያለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ በፓርላማ ጸድቆ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው፤ በመጋቢት 2011 ዓ.ም. ነበር። ይህ የህግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ የተደረገው፤ በ2001 ዓ.ም የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ “የነበሩበትን ክፍተቶች ለመሸፈን” እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። 

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ፤ “የመደራጀት መብትን የሚገድብ”፣ “አፋኝ” እና “ጨቋኝ” እንደሆነ ትችቶች  ሲቀርቡበት ቆይተዋል። ይህ አዋጅ በሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ በመልካም አስተዳደር፣ በጸረ-ሙስና፣ በግጭት አፈታት እና ተመሳሳይ ጉዳዩች ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ላይ የገቢ ምንጭ ገደብ የጣለ ነው። 

አዋጁ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችን ስራ ለመከታተል እና ለመቆጣጠር ለተቋቋመው ኤጀንሲ፤ “ሰፊ ጣልቃ ገብነትን የሚፈቅዱ” እና “የሲቪል ማህበራትን ነጻነት የሚጻረሩ ስልጣኖችን ሰጥቷል” በሚል በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ነቀፋዎች የሚቀርቡበት ነበር። ለአስር ዓመት በህግነት የቆየው ይህ አዋጅ፤ ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ከኢፌዲሪ ህገ መንግስት ጋር “የሚቃረኑ አንቀጾችን በውስጡ የያዘ” እንደሆነ የቀድሞው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት በወቅቱ ማስታወቁ ይታወሳል።

የአሁኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ የተዘጋጀው፤ በጽህፈት ቤቱ ስር በተቋቋመው የፍትህና ህግ ሥርዓት ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት ነበር። አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ “በርካታ ችግሮችን የፈታ ቢሆንም የቦርድ ውክልናን ጨምሮ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን” የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በትላንትናው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ የመስክ ምልከታ ወቅት ተናግረዋል ተብሏል።

በ2011 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ቦርድ 11 አባላት እንደሚኖሩት ይደነግጋል። ከእነዚህ አባላት ውስጥ ሶስቱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተወካዮች እንደሚሆኑ ያሰፈረው አዋጁ፤ ሌሎች ሶስት የቦርድ አባላት ደግሞ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እንደሚሰየሙ ያትታል።

የሴቶችና ወጣቶች ማህበራት በራሳቸው አደረጃጀት የሚወከሉ ሁለት አባላት በቦርዱ ውስጥ እንደሚኖራቸው በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ብሔራዊ ፌዴሬሽንም በተመሳሳይ ሁለት አባላትን በቦርዱ ውስጥ የመወከል ድርሻ በአዋጁ ተሰጥቶታል። “በሲቪል ማህበረሰብ ስራ ተገቢ እውቀት እና ልምድ ያለው ባለሙያ” የቦርዱ ሌላው አባል እንደሚሆንም በአዋጁ ተመላክቷል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“የውክልና ጥያቄ” የተነሳበት ይህ ቦርድ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የሚቀርቡ ይግባኞችን “የመመርመር” እና “ውሳኔ የመስጠት” ስልጣን አለው። ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ጉዳዩን የሚመረምር “ገለልተኛ አቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ” የመሰየም ስልጣን በአዋጁ ተሰጥቶታል። 

ይህ ኮሚቴ በሚያቀርበው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት፤ ቦርዱ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንደሚሰጥም በአዋጁ ተደንግጓል። የስራ ዘመናቸው ሶስት ዓመት የሆነው እነዚህ የቦርድ አባላት፤ የተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱን ዋና ዳይሬክተር እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች የስራ አፈጻጸም በየጊዜው የመገምገም ስልጣን ያላቸው ናቸው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በትላንቱ የመስክ ምልከታ ወቅት፤ አዋጁን ለማሻሻል ለሚደረገው ስራ የተወካዮች ምክር ቤት እና የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ “የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል” ተብሏል። ቋሚ ኮሚቴው ያነጋገራቸው የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞችም፤ “አላሰራ ያሉ ህጎች እንዲሻሻሉ” በተመሳሳይ መልኩ ጥያቄ ማቅረባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በመስክ ምልከታው፤ እነዚህን “አላሰራ ያሉ አዋጆች” ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቀጣይ እንዲሻሻሉ ማድረግ እንዳለበት “አቅጣጫ አስቀምጧል” ተብሏል። የቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ቡድን አስተባባሪ ወ/ሮ ከድጃ ያሲን፤ “አላሰራ ያሉ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻልን” በተመለከተ ፓርላማው እና እርሳቸው አባል የሆኑበት ቋሚ ኮሚቴ “ተገቢውን ጥረት” እና “ድጋፍ እንደሚያደርጉ” በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ መናገራቸውን የተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)