በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች “ጠንሳሽ” እና “ጨማቂዎች”፤ “ትላንትና ፖለቲካ ሲያንቦራጭቁ የነበሩ ሰዎች ናቸው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወነጀሉ። አብይ በሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ዛሬ አርብ ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ “ሰው torture አይደረግም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ገዢው ፓርቲ እስከ መጪው እሁድ ጥር 25፤ 2017 የሚቆየውን ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ እያካሄደ ያለው፤ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት አብይ፤ ፓርቲው ቃል ከገባቸው ጉዳዮች መካከል “በኢትዮጵያ ቶርቸር ይቁም” የሚለው አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል።
ብልጽግና ፓርቲ “ባለፉት ጥቂት ዓመታት” በተጓዘበት “የመጀመሪያ ምዕራፍ” ካሳካቸው ጉዳዮች አንዱ፤ ይኸው እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉባኤው ታዳሚያን ተናግረዋል። “ላለፉት ስድስት ዓመታት፤ ብታምኑም ባታምኑም አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ torture አይደረግም። በዚህ እኛ እንኮራለን” ብለዋል አብይ።
“ላለፉት ስድስት ዓመታት፤ ብታምኑም ባታምኑም አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ torture አይደረግም። በዚህ እኛ እንኮራለን”
– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
የፓርቲውን ያለፉት ዓመታት ጉዞ “የመነሳት ዘመን” ሲሉ የጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ከጥልቅ እንቅልፍ፣ ከብዙ ዕዳ፤ መንቃት፣ መነሳት፣ የጀመርንበት ምዕራፍ ነበር” ሲሉ ጊዜውን ገልጸውታል። “የመጀመሪያው የመነሳት ምዕራፍ አብቅቶ፤ አሁን በዚህ ጉባኤ የሚጸድቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የማንሰራራት ዘመን ነው” ሲሉም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ በፓርላማ በቀረቡበት ወቅትም ይህንኑ አገላለጽ ተጠቅመው ነበር። አብይ በተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ስብሰባ፤ “2017 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
አብይ በዛሬው ንግግራቸው “የማንሰራራት ዘመን፤ የቁልቁለት ጉዞ፣ የጎንዮሽ ጉዞ የሚያበቃበት ማለት ነው” ሲሉ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ትርጓሜውን አስረድተዋል። ከገዢው ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ባሉት ወራት፤ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች “የሚመረቁበት” እንደሆነም ጥቆማ ሰጥተዋል።

“ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለማስቆም፣ ከግራ ከቀኝ፣ ከውስጥ ከውጭ ጥረት ቢደረግም፤ ጨክነን ጨርሰን፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብስራት የምናበስርበት ዘመን ከፊታችን ባሉት ወራት የሚገለጽ ይሆናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ። ብልጽግና ፓርቲ “ፈተናዎችን ጨፍልቆ ማለፍ የሚችል አቅም ፈጥሯል” ሲሉም አክለዋል።
ብልጽግና ፓርቲን “ትልቅ ተቋም” ሲሉ የጠሩት አብይ፤ 15.7 ሚሊዮን እንደደረሱ ለተገለጹት የፓርቲው አባላትም ተስፋ ያዘለ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል። “አሁን ያለውን የፖለቲካ ጩኸት እንዳትመለከቱ። ፊታችን አስደማሚ ዘመን ነው ያለው” ብለዋቸዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የፓርቲው ዕጣ ፈንታ እና ውጤት የሚወሰነው “በልጆቻችን ነው” ያሉት አብይ፤ “እያደጉ ያሉ ልጆች ብልጽግና ምን አይነት መሰረት እየጣለ እንዳለ ያውቃሉ” ሲሉ የፓርቲው አባላት መስራት ያለባቸው ለመጪው ጊዜ መሆኑን አሳስበዋል። “አዲሱ ትውልድ የሚፈልገው “ልማት” እና “ብልጽግና” እንደሆነም ጠቁመዋል።

አብይ በዚህ ንግግራቸው “ፖለቲካን በቅጡ አልተለማመዱም” ያሏቸውን “አባቶች” ወርፈዋቸዋል። “አባቶቻችን ሀገርኛ ሀሳብ አላፈለቁም። በተዋሱት ሃሳብ ሲጨቃጨቁ፣ ሲጋደሉ የኖሩ ስለሆነ፤ አሁንም ያንን ማስቀጠል ይፈልጋሉ” ብለዋል።
ይህንን አባባላቸውን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ካሉት ግጭቶች ጋርም አስተሳስረውታል። “በኦሮሚያ ግጭት አለ። በአማራ ግጭት አለ። በትግራይ ግጭት አለ። በተለያዩ ቦታዎች ግጭት አለ። የእዚህ ግጭት ጠንሳሽ፣ ጨማቂዎች፤ ትላንትና ፖለቲካ ሲያንቦራጭቁ የነበሩ ሰዎች ናቸው” ሲሉ አብይ ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በጉባኤው ለኢትዮጵያ ህዝብ ማስተላለፍ የሚፈልገው መልዕክት፤ “ግጭት በቃን”፣ “እንሰልጥን”፣ “እንነጋገር” የሚል እንደሆነም የፓርቲው ፕሬዝዳንት አስታውቀዋል። አብይ በዚሁ ንግግራቸው “በ60ዎቹ የታጠቃችሁትን ክላሽ አውርዱ” ሲሉ ማንነታቸውን በግልጽ ላልጠቀሷቸው ወገኖች “የድርድር እና የውይይት” ጥሪ አስተላልፈዋል።
“ብልጽግና በሰላም፣ በድርድር፣ በውይይትና በሃሳብ ለሚደረግ የፖለቲካ ትግል፤ ግማሽ መንገድ የመሄድ ልምምድ ባለፈው አሳይቷል። አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል አብይ። ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፤ የጉባኤው ተሳታፊዎች በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)