በቤርሳቤህ ገብረ
በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በሚገኘው ሃላይዳጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርክ ከትላንት በስቲያ የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት እስከ ዛሬ ሰኞ እኩለ ቀን ድረስ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ እድሪስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በሰደድ እሳቱ 200 ሄክታር የሚገመት የፓርኩ ክፍል መቃጠሉን ኃላፊው ገልጸዋል።
ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታ ሆኖ የቆየው ሃላይዳጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርክ፤ 1099 ገደማ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ነው። ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ብሔራዊ ፓርክ ደረጃ ያደገው ጥብቅ ቦታው፤ የ325 የእጽዋት ዝርያ፣ የ244 የአእዋፍ ዝርያ እና ከ42 በላይ አጥቢ እንስሳት መኖሪያ ነው።
በኢትዮጵያ እና በኬንያ ብቻ የሚገኝ የሜዳ አህያ ዝርያ እንዲሁም ሳላ የተሰኘው አጥቢ እንስሳ በብዛት በሚገኝበት በዚህ ፓርክ፤ የእሳት አደጋ የተከሰተው ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ የካቲት 1፤ 2017 ከቀኑ ስምንት ሰዓት በኋላ ባለው ጊዜው ውስጥ ነው። እሳቱ በከፍተኛ ንፋስ የታገዘ በርካታ ቦታ ማዳረሱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ እሳቱን ለማጥፋት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የአካባቢው አስተዳደር ሰራተኞች ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፓርኩ ስፋት የተነሳ ሰደድ እሳቱን ሙሉ ለሙሉ በውሃ ለማጥፋት የማይቻል በመሆኑ፤ ቃጠሎውን “በቅጠል በማፈን ለማጥፋት” እየተሞከረ እንደሚገኝ አቶ አህመድ አስረድተዋል። በፓርኩ ውስጥ ያሉ ተቀጣጣይ የሆኑ ነገሮች በእሳት እንዳያያዙ አስቀድሞ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
አቶ አብዶ አሊ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ፤ እሳቱ የማይቆም ከሆነ በሰዎች ላይ ጭምር ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ስጋታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ነዋሪው ለዚህ በማስረጃነት የሚጠቅሱት፤ እሳቱ ከተቀሰቀሰበት አካባቢ በአራት ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሰዎች መኖሪያ ቤቶች መኖራቸውን ነው።
ሰደድ እሳቱ የተከሰበት አካባቢ የሚገኘው በአፋር ክልል ሀሩካ እና አሚባራ ወረዳዎች ውስጥ ነው። የአሚባራ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ መሀመድ ባሪኢ በፓርኩ የተቀሰቀሰው እሳት እስከ ዛሬ ሰኞ ረፋድ ድረስ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

የሃላይዳጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ እሳቱ እስካሁን በቁጥጥር ስር አይዋል እንጂ በፓርኩ ዙሪያ የእሳት ማገጃ (firebreak) ስላለ “ወደ ሌሎች ቦታዎች አይዛመትም” ባይ ናቸው። ሰደድ እሳቱ የተቀሰቀሰው በፓርኩ መካከል እንደሆነ ያመለከቱት ኃላፊው አቶ አህመድ፤ ተሰፋፍቶ እስከ አዋሽ አርባ ከተማ ሊደርስ እንደማይችል ይሟገታሉ።
ሆኖም ሰደድ እሳቱ “መራመድ፣ መሮጥ እና ማምለጥ የማይችሉ” ባሏቸው እንደ ኤሌ ባሉ እንስሳት ላይ “ከፍተኛ ጉዳት” ሊያደርስ እንደሚችል የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይቀበላሉ። አቶ አብዶ የተባሉት የአካባቢው ነዋሪ፤ በእሳት ቃጠሎው ሶስት ኤሊዎች ሞተው መመልከታቸውን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
የሃላይዳጌ አሰቦት ብሄራዊ ፓርክ ተመሳሳይ የእሳት አደጋ ሲያጋጥመው በዚህ ዓመት ብቻ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑን ከፓርኩ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከዚህ ቀደም ከደረሱ የእሳት ቃጠሎዎች ውስጥ ሁለቱ የተከሰቱት፤ በከሰል አክሳዮች እና በተጣለ ሲጃራ ምክንያት እንደሆነ ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)