በቤርሳቤህ ገብረ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖች፤ 469.9 ሚሊዮን ብር ከአርሶ አደሮች ያልተሰበሰበ “ቀሪ የማዳበሪያ ዕዳ” እንዳለባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ። ዞኖቹ ዕዳቸውን ወቅቱን ጠብቀው ባለመክፈላቸው፤ ለልማት ሊውል ይገባ የነበረ “ሰፊ ሀብት” በወለድ መልክ ከበጀታቸው ተቀንሶ ለባንክ እየተላለፈ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የገለጹት፤ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 4፤ 2017 በተርጫ ከተማ በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ነው። ዶ/ር ነጋሽ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ ክልሉ ያለበትን የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ እና የወለድ ክምችት “አሳሳቢ ጉዳይ” እንደሆነ ለምክር ቤቱ አባላት አስገንዝበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተበት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለአርሶ አደሮች የተሰራጨውን የአፈር ማዳበሪያ መጠን በዝርዝር ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በሶስት የምርት ዘመኖች ብቻ በክልሉ በአጠቃላይ ያልተከፈለ የማዳበሪያ ዕዳ እና ወለድ ግማሽ ቢሊዮን ብር እንደሚጠጋ አስታውቀዋል። ዕዳው እንዲከማች ያደረጉ የክልሉ ዞኖች፤ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ እና ኮንታ መሆናቸውንም ይፋ አድርገዋል።

ካልተከፈለው ቀሪ የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ውስጥ ከፍተኛ መጠን በመያዝ ቤንች ሸኮ ዞን ቀዳሚው ነው። ዞኑ ያልተከፈለ 203 ሚሊዮን ብር የማዳበሪያ እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አመልክተዋል። የምዕራብ ኦሞ ዞን 105.1 ሚሊዮን ብር የማዳበሪያ ዕዳ በመያዝ በሁለተኛነት እንደሚከተል በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የዳውሮ ዞን 72.1 ሚሊዮን ብር የማዳበሪያ ዕዳ የተከማቸበት ነው። ከፋ ዞን 52.6 ሚሊዮን ብር ማዳበሪያ ዕዳ ያለበት ሲሆን ሸካ ዞን በበኩሉ 20.9 ሚሊዮን ብር ተመሳሳይ ዕዳ አስመዝግቧል። በንጽጽር ሲታይ አነስተኛ የማዳበሪያ እዳ ያለበት ኮንታ ዞን 16.1 ሚሊዮን ብር ቀሪ የማደበሪያ ዕዳ ይጠበቅበታል።
“ይህ ዕዳ ወቅቱን ጠብቆ ባለመከፈሉ ምክንያት፤ በዞኖች እና ወረዳዎች ውስጥ ለልማት ሊውል የሚገባ ሰፊ ሀብት በወለድ መልክ ከበጀታቸው እየተቀነሰ ለባንክ እየተላለፈ ይገኛል። ስለሆነም የምክር ቤት አባላት ከዞኖች እና ከወረዳዎች ጋር በሚያደርጉት ውይይት እና ምክክር ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በአንክሮ እንዲያነሱ እና አቅጣጫ እንዲያስቀመጡ በአክብሮት እጠይቃለሁ” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በዛሬው መደበኛ ጉባኤ ላይ አሳስበዋል።
“ይህ ዕዳ ወቅቱን ጠብቆ ባለመከፈሉ ምክንያት፤ በዞኖች እና ወረዳዎች ውስጥ ለልማት ሊውል የሚገባ ሰፊ ሀብት በወለድ መልክ ከበጀታቸው እየተቀነሰ ለባንክ እየተላለፈ ይገኛል”
– ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
የኢትዮጵያን ፌዴሬሽን በመቀላቀል አስራ አንደኛ ሆኖ የተመዘገበው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በ2014/2015 የምርት ዘመን ለአርሶ አደሮች ማዳበሪያ ያቀረበው በቀድሞው የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ዋስትና እንደነበር ዶ/ር ነጋሽ በዛሬው ሪፖርታቸው አስታውሰዋል። ክልሉ በዚህ የምርት ዘመን ለአርሶ አደሮች ያሰራጨው የአፈር ማዳበሪያ 49,758 ኩንታል ነው።
አዲሱ ክልል ለተረከበው ለዚህ ማዳበሪያ መክፈል የሚገባው ዕዳ ከእነ ወለዱ 213.3 ሚሊዮን ብር ደርሶ እንደነበር ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። ክልሉ ካለበት ከዚህ ዕዳ ውስጥ 165.6 ሚሊዮን ብር ያህሉን ለፌደራል መንግስት መመለስ ቢችልም፤ ወለድን ጨምሮ ቀሪ 47.7 ሚሊዮን ብር ዕዳ እስካሁንም አለመክፈሉን ዶ/ር ነጋሽ ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከምስረታው አንድ ዓመት በኋላ በነበረው የምርት ዘመን ለአርሶ አደሮች ላሰራጨው የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ የሚጠበቅበትን ክፍያ ባለመክፈሉ፤ ዕዳው ለዘንድሮው በጀት ዓመት መትረፉን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል። “በ2015/2016 የማዳበሪያ ዕዳ በወቅቱ ለባንክ ገቢ ባለመደረጉ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ከክልሉ ድጎማ በጀት ተቆራጭ ያደረገው አጠቃላይ ቀሪ ዕዳ 181.2 ሚሊዮን ብር [ነው]። ዕዳው ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ፤ በክልሉ የፋይናንስ ቢሮ በኩል ከየዞኖች በጀት ተቀናሽ እየተደረገ ይገኛል” ሲሉ ዶ/ር ነጋሽ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል።

ክልሎች ከፌደራል መንግስት የተበደሩትን ገንዘብ መልሰው እንዲከፍሉ የማድረግ ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ለገንዘብ ሚኒስቴር ነው። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮው የምርት ዘመን እስካሁን የአፈር ማዳበሪያ የከፈለው የገንዘብ መጠን፤ ከሚጠበቅበት 45 በመቶ ብቻ እንደሆነ ለክልሉ ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ለ2016/ 2017 የምርት ዘመን ክልሉ በአጠቃላይ ከሚያስፈልገው የማዳበሪያ መጠን ውስጥ 151,879 ኩንታል ነው። ከዚህ ውስጥ 79,396 ኩንታል ያህሉን ለአርሶ አደሮች ማሰራጨቱን የገለጹት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ ቀሪውበዞኖች እና በማዕከላዊ መጋዘን የሚገኝ እንደሆነ አመልክተዋል።
በክልሉ ባለፉት ወራት የተሰራጨው የማዳበሪያ መጠን 337.6 ሚሊዮን ብር የሚተመን እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር ነጋሽ፤ የሚመሩት ክልል እስካሁን ለፌደራል መንግስት ያስገባው የገንዘብ መጠን 153.3 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። ክልሉ መክፈል ያለበት ቀሪ ገንዘብ፤ በመጋዘን የሚገኘው ማዳበሪያ በበልግ የምርት ወቅት “ለአርሶ አደር ተሽጦ እና ተሰራጭቶ ገቢ የሚደረግ መሆኑንም” አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)