በተስፋለም ወልደየስ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለሶስት ወራት “በምንም አይነት” ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳይሳተፍ አገደ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ የሚያስችል “የእርምት እርምጃ” ካልወሰደ፤ የፓርቲው ምዘገባ በቀጥታ እንደሚሰረዝ ቦርዱ አስታውቋል።
ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው፤ ህወሓትን በተመለከተ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 6፤ 2017 ባወጣው መግለጫ ነው። ቦርዱ ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት “በልዩ ሁኔታ” መስጠቱን የገለጸው፤ በነሐሴ 2016 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነበር።
ይህ እርምጃ በጥር 2013 ዓ.ም. በምርጫ ቦርድ አማካኝነት ከፓርቲነት የተሰረዘው ህወሓትን፤ ወደ “ህጋዊ ሰውነት” የመለሰ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ቦርዱ ህወሓትን ከፓርቲነት ሰርዞ የነበረው፤ “ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን” እንዳረጋገጠ በመጥቀስ ነበር።

ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ማጣት በምክንያትነት ተጠቅሶ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደ የግጭት ማቆም ስምምነት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. መቋጨቱ ይታወሳል። ስምምነቱን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተፈራረመው ህወሓት፤ ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ለቦርዱ ያቀረበው ጥያቄ “በህግ የተደገፈ አይደለም” በሚል ውድቅ ተደርጎ ነበር።
ህወሓትን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ ያነሳውን የህግ ክፍተት የሚደፍን የአዋጅ ማሻሻያ፤ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል። ይህ የአዋጅ ማሻሻያ “በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበሩ” የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገቡ የሚያስችላቸው ነው።
ይህን ተከትሎ የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት አካልን በመወከል፤ ህወሓት “በልዩ ሁኔታ” በፖለቲካ ፓርቲነት መመዝገብ እንዲችል ለምርጫ ቦርድ ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ጥያቄ አቅርቧል። ከዘጠኝ ወር በፊት የተሻሻለው አዋጅ፤ ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ የፖለቲካ ቡድን “በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ የሚችለው” በሚመለከተው የመንግስት አካል ከተረጋገጠ እንደሆነ ይደነግጋል።

ይህን ማረጋገጫ ከፍትሕ ሚኒስቴር ማግኘቱን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር የገለጸው ምርጫ ቦርድ፤ ህወሓትን በክልላዊ ፓርቲነት በድጋሚ መዝግቦታል። ፓርቲው ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ፤ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግም ምርጫ ቦርድ በወቅቱ ቀነ ገደብ ሰጥቷል።
ቦርዱ ለፓርቲው የሰጠው የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ፤ የህወሓትን የቀድሞው ህልውናው “ወደነበረበት የማይመልስ” በመሆኑ እንደማይቀበለው በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ጎራ በወቅቱ አስታውቋል። ይኸው የህወሓት ጎራ ያለ ምርጫ ቦርድ እውቅና በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ዶ/ር ደብረጽዮንን በድጋሚ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል።
በዚሁ አወዛጋቢ ጉባኤ በተደረገ ምርጫ፤ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በአቶ አማኑኤል አሰፋ መተካታቸው ይፋ ተደርጓል። በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች እውቅና እንደማይሰጥ አስቀድሞ ያሳወቀው ምርጫ ቦርድ፤ በጥቅምት እና ታህሳስ ወር ለፓርቲው በጻፋቸው ደብዳቤዎች ህወሓት “አስፈላጊውን ቅደመ ዝግጅት በማከናወን” ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ አሳስቦ ነበር።

ህወሓት “በህግ የተጣለበትን ግዴታ” በቀነ ገደቡ ሳይፈጽም ቢቀር፤ ምርጫ ቦርድ “ሕግን መሰረት በማድረግ” “ተገቢ ነው” የሚለውን ውሳኔ እንደሚሰጥ በታህሳሱ ደብዳቤው አስታውቋል።ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ባለፈው ሰኞ የካቲት 3፤ 2017 መጠናቀቁን ተከትሎ፤ መስሪያ ቤቱ ሲጠበቅ የቆየውን ውሳኔ በማግስቱ ባደረገው ስብስባ ማሳለፉን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ቦርዱ በዚሁ መግለጫው፤ ህወሓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን “ህግ፣ መመሪያና ውሳኔዎችን አክብሮ መንቀሳቀስ ሲገባው”፤ “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገብ ባስቻለውን አዋጅ እና እርሱን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ የተካተቱ ድንጋጌዎችን “ጥሶ ተገኝቷል” ብሏል። ህወሓት በአዋጁ እና በመመሪያው ከተጣለበት ኃላፊነትና ግዴታዎቹ መካከል በቦርዱ ከተመዘገበ ጊዜ አንስቶ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ “የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ” አንዱ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ህወሓት የሚያከናውናቸውን “የቅድመ ጉባኤ ዝግጅት የተመለከቱ ስራዎችን” ምርጫ ቦርድ መከታተል ይችል ዘንድ፤ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማድረጉ 21 ቀናት አስቀድሞ የስብሰባውን ዕለት ማሳወቅ ይገባው እንደነበር በመግለጫው ሰፍሯል። ህወሓት በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤው፤ የፓርቲ ሰነዶቹን “ከአዋጁ ጋር አጣጥሞ ማጽደቅ” እና “አመራሮቹን ማስመረጥ” ይጠበቅበት እንደነበርም የምርጫ ቦርድ መግለጫ አትቷል።

ፓርቲው እነዚህን በአዋጅ እና መመሪያ ላይ የተቀመጡ ኃላፊነትና ግዴታዎቹን ባለመክበር “ጉልህ ጥሰት” መፈጸሙን በመግለጫው ያመለከተው ምርጫ ቦርድ፤ በዚህም መሰረት ህወሓት የቦርዱ ውሳኔ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ “በምንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይሳተፍ እንዲታገድ” ውሳኔ መተላለፉን ገልጿል።
ህወሓት “ለእግዱ ምክንያት የሆነውን ጥሰት በማረም”፤ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ለመስራት ለምርጫ ቦርድ “በጹሁፍ ሲያሳውቅ”፤ ቦርዱ እግዱን የሚያነሳ መሆኑም በዛሬው መግለጫ ላይ ይፋ ተደርጓል። ምርጫ ቦርድ እገዳውን የሚያነሳው፤ የቅድመ ጉባኤ ዝግጅትን የተመለከቱ ስራዎችን በራሱ “ሲያረጋግጥ” መሆኑንም አስታውቋል።
ፓርቲው በተሰጠው የሶስት ወራት የእግድ ጊዜ ውስጥ “የእርምት እርምጃ ካልወሰደ”፤ ምርጫ ቦርድ “የተለየ አካሄድ ሳይከተል” የህወሓት ምዝገባ እንዲሰረዝ ውሳኔ ማሳለፉም በዛሬው መግለጫ ላይ ሰፍሯል። ምርጫ ቦርድ ይህንኑ ማስጠንቀቂያ ለህወሓት በጻፈው ይፋዊ ደብዳቤ ላይም አካትቶታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]