በቤርሳቤህ ገብረ
ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው ግማሽ ዓመት 61.9 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። በዚሁ ጊዜ ውስጥ 32.8 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዘገቡን የገለጸው ተቋሙ፤ የደንበኞቹን ቁጥር 80.5 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉንም ይፋ አድርጓል።
ይህ የተገለጸው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የተቋማቸውን የግማሽ አመት አፈጻጸም ዛሬ ረቡዕ የካቲት 5፣ 2017 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል ባቀረቡበት ወቅት ነው። ኢትዮ ቴሌኮም በ2017 በጀት ዓመት ለማግኘት ያቀደው አጠቃላይ ገቢ 163.7 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ባለፈው መስከረም አስታውቆ ነበር።
መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያ በመንፈቅ ዓመቱ ያገኘው ገቢ፤ ከእቅዱ 90.7 በመቶ ያሳካ መሆኑን አመልክቷል። ኩባንያው በዚሁ ወቅት ያስገባው ገቢ፤ በ2016 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ19 ቢሊዮን ብር ጨምሯል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለገቢው መጨመር በምክንያትነት ከጠቀሳቸው ውስጥ፤ የሞባይል ስልክ ደንበኞቹ የዳታ እና የድምጽ አጠቃቀም ማደግ ይገኝበታል። የኩባንያው ደንበኞች የዳታ አጠቃቀም፤ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ሲነጻጸር በ48.8 በመቶ እድገት ያስመዘገበ መሆኑ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነስቷል።
በግማሽ አመቱ ለገቢው እድገት ሌላው ጉልህ ሚና እንደነበረው የተገለጸው፤ የሞባይል ድምጽ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች ላይ የታየው የደቂቃ እድገት ነው። በዚሁ ጊዜ በድምጽ አገልግሎት አጠቃቀም የታየው እድገት 12.7 በመቶ እንደሆነ ተነግሯል።
ባለፈው መንፈቅ ዓመት በተመዘገበው የኩባንያው ገቢ፤ የዓለም አቀፍ አገልግሎቶች የነበረው ድርሻም እንዲሁ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነስቷል። ኢትዮ ቴሌኮም በዚሁ ጊዜ ከዓለም አቀፍ አገልግሎቶች ያገኘው ገቢ፤ 64.4 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ተገልጿል። ይህ ገቢ ኩባንያው በእቅዱ ከያዘው 63.8 በመቶውን ያሳካ ነው ተብሏል።

ኩባንያው በዘንድሮው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ፤ 3.24 ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራት መቻሉንም አስታውቋል። ይህ የደንበኞች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 7.9 በመቶ እድገት የታየበት ሲሆን፤ አጠቃላይ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞችን 80.5 ሚሊዮን አድርሶታል።
ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ካሉት ደንበኞቹ ውስጥ 77.7 ሚሊዮን የሚሆኑት፤ የሞባይል ድምጽ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። የኩባንያው ሞባይል ኢንተርኔት እና ዳታ ተጠቃሚዎች ቁጥር፤ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 43.5 ሚሊዮን ደርሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]