ከመተሐራ ከተማ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ላይ በሬክተር ስኬል 6.0 የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። ዛሬ አርብ ምሽት 5 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ላይ የደረሰው ርዕደ መሬት፤ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ከተመዘገቡት ሁሉ በመጠን ከፍተኛው ነው።
የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ንዝረት “በጣም ጠንካራ” ሆኖ የተሰማው በመተሐራ ከተማ ይሁን እንጂ መዲናይቱን አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ ከተሞችን ማዳረሱን የአሜሪካው የምርምር ተቋም ገልጿል። የርዕደ መሬቱ ንዝረት በአዋሽ ከተማ “መጠነኛ” እንደነበር ያመለከተው ተቋም፤ በአዳማ፣ ሞጆ፣ ቢሾፍቱ እና ደብረ ብርሃን ከተሞችም በተመሳሳይ መጠን መከሰቱን ጠቁሟል።
በመተሐራ እና አዋሽ ከተሞች አቅራቢያ ያሉ አካባቢዎች፤ ባለፉት ወራት የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ ሲከሰትባቸው የቆዩ ናቸው። በአካባቢዎቹ በመስከረም እና ጥቅምት ወራት ሲከሰት የነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ በህዳር ወር ጋብ ያለ ቢመስልም፤ በታህሳስ እና ጥር ወራት ግን በቀን ለበርካታ ጊዜያት ጭምር ሲመዘገብ ቆይቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦችን የሚመዘግበው “ቮልካኖ ዲስከቨሪ”፤ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ መጠናቸው በሬክተር ስኬል 4.0 እና ከዚያ በላይ የሆኑ 173 ርዕደ መሬቶች በኢትዮጵያ መከሰታቸውን አስታውቋል። እስከ ዛሬ ምሽቱ ክስተት ድረስ በመጠኑ ከፍተኛ የነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ታህሳስ 26 ለሊት የተከሰተው እና በሬክተር ስኬል 5.8 የተለካው ርዕደ መሬት ነበር።
በሬክተር ስኬል ከ5.5 እስከ 6.0 መጠን ያላቸው የመሬት መንቀጥቀጦች፤ በህንጻዎች እና በሌሎች ግንባታዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ እንደሆኑ በክስተቶቹ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ይገልጻሉ። ከ6.1 እስከ 6.9 መጠን ያላቸው ርዕደ መሬቶች፤ በተለይ በርካታ ህዝብ በሰፈረባቸው ቦታዎች ላይ ብዙ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ እነኚሁ ተቋማት ያስረዳሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]