በቤርሳቤህ ገብረ
በአማራ ክልል እስከ ትላንት ድረስ በእስር ላይ የነበሩ ዳኞች ሙሉ ለሙሉ መለቀቃቸውን የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር አስታወቀ። ካለፈው ሁለት ወር ወዲህ እስከ አርብ የካቲት 14፤ 2017 ድረስ ባሉት ጊዜያት ከእስር የተለቀቁት ዳኞች ብዛት 36 እንደሆነ የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ አሰፋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በክልሉ ታስረው የነበሩ ሁሉም ዳኞች መፈታታቸው የተገለጸው፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት የዳኞች ያለመከሰስ መብትን ያካተተ የህግ ማሻሻያ ካጸደቀ ከአስር ቀናት በኋላ ነው። በአማራ በተለያየ እርከን በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የሚሰሩ ዳኞች ለእስር ይዳረጉ የነበረው፤ በሚይዟቸው መዝገቦች ላይ በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ምክንያት እንደሆነ አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።
“አብዛኞቹ ከስራ ጋር የተገናኘ ነው። ምክንያቱ ‘ዋስትና ጋር ተያይዞ ለምን ፈቀዳችሁ? ለምን ትዕዛዝ ሰጣችሁ? ለምን እግድ ሰጣችሁ?’ [የሚል ነው]። ያው በፍርድ ቤት ዳኞች በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን መሰረት አድርገው ሲሰሩ፤ ከአስፈጻሚው ጋር የሚገናኙ አለመግባባቶች ጋር መነሻ በማድረግ የታሰሩ ናቸው” ሲሉ የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት የእስሮቹን መንስኤ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

በአማራ ክልል የዳኞች እስር ቀደም ብሎ “አልፎ አልፎ” ይከሰት እንደነበር የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ እርምጃው “እየተበራከተ” የመጣው በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በክልሉ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በነሐሴ 2015 ዓ.ም. ማጽደቁ ይታወሳል።
የተፈጻሚነት ቀነ ገደቡ በጥር 2016 ዓ.ም. ይጠናቀቅ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ በፓርላማው ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ተደርጎ ነበር። የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በነበረበት ወቅት እና ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ በድምሩ 35 ዳኞች መታሰራቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ጥር ወር ባወጣው ሪፖርት ላይ አስታውቋል።
ብሔራዊው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም በዚሁ ሪፖርቱ፤ ዳኞቹ የታሰሩት“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊነት” እና “የህግ ማስከበር ዘመቻ” እንደሽፋን በመጠቀም መሆኑን ገልጿል። የዳኞቹን እስራት “ህገወጥ” ሲል የጠራው ኢሰመኮ፤ በክልሉ ከዚህም በተጨማሪ በዳኞች ላይ “ጥቃት፣ ማስፈራራት እና ጣልቃ ገብነት” እንደሚፈጸምባቸው በሪፖርቱ አመልክቷል።

በክልሉ ያሉ ዳኞች በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን መሰረት አድርገው ስራቸውን እስከ ሰሩ ድረስ ሊታሰሩ እንደማይገባ የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ዳኞች ጥፋት ቢኖርባቸው እንኳ “በህግ አግባብ” በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ መጠየቅ እንደሚችሉም አክለዋል።
“ዳኞች ነጻ ሆነው ውሳኔ ካልሰጡ፣ የሚታሰሩ ከሆነ፣ በሚሰጡት ትዕዛዝ ነጻ ሆነው ለመወሰን እና ነጻ ሆነው ትዕዛዝ ለመስጠት መሰናክል ነው። ይህ ችግር እንዲቀረፍ ነበር በተደጋጋሚ ጥረት ስናደርግ የነበረው” ሲሉ በአማራ ክልል ዳኞች ማህበር በኩል ጥሪዎች ሲቀርቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ማህበሩ በዳኞች ላይ “የሚፈጸመው እስር እንዲቆም”፣ “የታሰሩ ዳኞች እንዲፈቱ” እና “የዳኞች ያለመከሰስ መብት በህግ ጥበቃ እንዲያገኝ” ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ ለክልሉ ምክር ቤት እና ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በደብዳቤ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል።
ከማህበሩ ተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላ በማረሚያ ቤቶች እና በተሃድሶ ማቆያዎች ውስጥ ታስረው የቆዩ ዳኞች በተለያዩ ጊዜያት ሙሉ በሙሉ እንዲፈቱ መደረጉን አቶ ብርሃኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከተለቀቁት አብዛኛዎቹ የወረዳ ፍርድ ቤቶች እና የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዳኞች እንደሆኑ የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ የታሰሩትም በዚህ ዓመት እንደነበር ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ከዳኞች መፈታት በተጨማሪ ያነሳው “የዳኞች ጥበቃ እና ከለላ” መከበር ጉዳይ ከሳምንት በፊት እልባት አግኝቷል። የአማራ ክልል ምክር ቤት የካቲት 7፤ 2017 ባጠናቀቀው መደበኛ ጉባኤው ያጸደቀው “የፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ”፤ የዳኞች ጥበቃ እና ከለላን የያዙ ድንጋጌዎች የተካተቱበት ነው።
በ2014 ዓ.ም. የወጣው የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ “የዳኝነት ነጻነት ከማረጋገጥ አንጻር እንደ አንድ ዋስትና የሚወሰደውን የዳኞች ያለመከሰስ መብት ጥበቃ የማያደርግ ነው” ሲል ኢሰመኮ ባለፈው ጥር ወር ባወጣው ሪፖርት አመልክቶ ነበር። ይህም “በክልሉ እየታየ ላለው የዳኞች እስር እና ወከባ በር የከፈተ” እንደሆነ መረዳቱን ኢሰመኮ በዚሁ ሪፖርቱ አስፍሯል።
ኢሰመኮ በዚሁ ሪፖርቱ ማጠቃለያ ካቀረባቸው ምክረ ሃሳቦች መካከል “ዳኞች ከዳኝነት ስራቸው ጋር በተያያዘ በፍትሐ ብሄርም ሆነ በወንጀል ጉዳዮች ያለመከሰስ መብት የህግ ዋስትና ይሰጣቸው” የሚል ነበር። እንደ ኢሰመኮ ሁሉ ተመሳሳይ ምክረ ሃሳብ ሲያቀርብ የቆየው የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት፤ የህግ ማሻሻያው በክልሉ ምክር ቤት መጽደቁን “በጣም ጥሩ እርምጃ” ሲሉ አሞካሽተውታል።
የህግ ማሻሻያው መደረጉ በእስር ላይ የነበሩ ቀሪ ዳኞች እንዲለቀቁ ምክንያት መሆኑን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ብርሃኑ፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ እርግጠኛ ምላሽ እንደሌላቸው ተናግረዋል ። በማህበራቸው በኩል ቀደም ብሎም ቢሆን ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸው ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፤ “የለቀቀው አካል ይህንን ታሳቢ አድርጎ መሆን አለመሆኑን እርግጠኛ አይደለሁም” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)