በቤርሳቤህ ገብረ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከነገ በስቲያ ሐሙስ መጋቢት 11፤ 2017 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት፤ ከፓርላማ አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሊሰጡ ነው። የሐሙሱ የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ፤ የፌደራል መንግስት የስድስት ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለምክር ቤት አባላት መላኩን ተከትሎ የሚካሄድ ነው።
በ57 ገጾች የቀረበው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ሪፖርት፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት የመንፈቅ ጊዜ ውስጥ የፌደራል መንግስት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ስራዎች የሚዘረዝር ነው። ሪፖርቱ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ልማት፣ በሰላም እና ደህንነት ግንባታ፣ በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ እንዲሁም በፍትህ እና አስተዳደር ዘርፎች የነበሩ አፈጻጸሞችን ዳስሷል።
ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ አፈጻጸምም በሪፖርቱ ላይ ተካትቷል። የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሪፖርቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄ በጽሁፍ አስገብተው ያጠናቀቁት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ እንደሆነ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የፓርላማ ምንጮች ገልጸዋል።

በ2008 ዓ.ም በወጣው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ መሰረት፤ “ማንኛውም የቃል መልስ የሚፈልግ ጥያቄ የሚያቀርብ አባል፤ ጥያቄውን ቢያንስ ከአስር ቀናት በፊት ለአፈ ጉባኤው በጽሁፍ ማሳወቅ እንዳለበት” ተደነግጓል። ይኸው ደንብ የፓርላማ አባላቱ የሚያቀርቡትን ጥያቄ “መርምሮ የመቀበል” ወይም ውድቅ “የማድረግ ስልጣን” የሰጠው ለአፈ ጉባኤው ነው።
በዚህ መሰረት የፓርላማ አባላቱ ጥያቄዎቻቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽሁፍ እንዲያቀርቡ የተነገራቸው፤ የአንድ ወር የእረፍት ጊዜያቸው በተጠናቀቀ ማግስት ነው። የፓርላማ አባላቱ የሚመሩበት የአሰራር እና የስነ ምግባር ደንብ፤ የየካቲት ወርን እንዲሁም ከሐምሌ እስከ መስከረም የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ድረስ ያለውን ጊዜ ለእረፍት መድቦላቸዋል።
ይኸው ደንብ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያዝላቸው ፕሮግራም መሰረት የመንግስትን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት የሚያቀርቡት በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሆነ አመልክቷል። በዚሁ ደንብ ላይ የፓርላማው ዕለታዊ አጀንዳ እና የተመደበው የውይይት ጊዜ ከምክር ቤቱ ስብሰባ 48 ሰዓት በፊት አባላት እንዲያውቁት መደረግ እንዳለበትም ሰፍሯል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የፓርላማ አባላት ግን እስከ ማክሰኞ እኩለ ቀን ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቼ በፓርላማ እንደሚቀርቡ እንዳልተገለጸላቸው አስረድተዋል። የተወካዮች ምክር ቤት የሚወያይበትን ማንኛውንም አጀንዳ የሚቀርጸው አማካሪ ኮሚቴ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፓርላማ ውሎ አጀንዳ ያጸደቀው ማክሰኞ ረፋድ እንደሆነ የፓርላማ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የሐሙሱ የፓርላማ ስብሰባ የፌደራል መንግስት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም የተመለከቱ ጥያቄዎችን የሚቀርቡበት እንደሆነ ቢገለጽም፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን ያስገቡ አንድ የፓርላማ አባል ግን ከመልካም አስተዳደር፣ ከማንነት፣ የሰላም እና አስተዳደር ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ማንሳታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ሌሎች ሁለት የፓርላማ አባላት፤ በስብሰባው ላይ “ወቅታዊ ጉዳዮች በጥያቄ መልክ ይቀርባሉ ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለመጨረሻ ጊዜ ለፓርላማ ቀርበው ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ባለፈው ከአራት ወራት በፊት ነበር። የፓርላማ አባላቱ በጥቅምት ወር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ በህዝብ ተወካዮች እና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ የተንተራሱ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)