በቤርሳቤህ ገብረ
የመንግስት እና የግል ተቋማት ከሚሰጧቸው የተለያዩ አገልግሎቶች “ለአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ” የሚሆን ገቢ እንዲሰበስቡ የሚያስገድድ የአዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ ቀረበ። የሚጠበቅበትን ገቢ ሰብስቦ ወደ ፈንዱ የባንክ ሂሳብ ያላስተላለፈ ድርጅት ወይም ተቋም፤ ከሚጠበቅበት ገንዘብ በተጨማሪ አስር ከመቶ የባንክ ወለድ ቅጣት እንዲከፍል በአዋጁ ይገደዳል።
እነዚህን ግዴታዎች ያካተተው እና ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 9፤ 2017 ለፓርላማ የቀረበው የህግ ረቂቅ፤ “የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር አዋጅ” የሚል ስያሜ ያለው ነው። የአዋጅ ረቂቁ ካሉት ሰባት ክፍሎች መካከል አንዱ “ለአደጋ ስጋት ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል የሚሰበሰብ የገንዘብ ሃብትን” የተመለከተ ነው።
“የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ” የሚል መጠሪያ ያለው ይህ የገንዘብ ሃብት፤ “በቅድመ አደጋ፣ በአደጋ እና በድህረ አደጋ ወቅቶች” ለሚወሰዱ፤ “የአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ ምላሽ እና መልሶ ማቋቋም” ተግባራት የሚውል እንደሆነ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። ይህ ገንዘብ “ቅጽበታዊ አደጋ ሲፈጠር” እና “የተከሰተው አደጋ በአስቸኳይ ምላሽ ቅድሚያ መስጠቱ አስፈላጊ መሆኑ ሲታመንበት” ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል የአዋጅ ረቂቁ ያስረዳል።
የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ ምግብ እና ምግብ-ነክ ያልሆነ “የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ክምችት”፤ “ለማምረት” አሊያም “ግዢ ለመፈጸም” ይህን ፈንድ መጠቀም እንደሚቻል በአዲሱ አዋጅ ላይ ተገልጿል። የክምችት መጋዘኖችን አቅም ለማሳደግ እና ተያያዥ መሰረተ-ልማት ለማስፋፋትም ፈንዱ አገልግሎት ላይ ሊውል ይችላል።
ፈንዱን “በበላይነት የመምራት” እና “የማስተባበር” ሚና በአዋጁ የተሰጠው፤ ለኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ነው። ይኸው አዋጅ፤ ለፈንዱ የሚሆን ገንዘብ የሚሰበሰብባቸው ምንጮች የትኞቹ እንደሆኑም በዝርዝር አስቀምጧል። የፌዴራል መንግስት፣ የአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፤ ከጠቅላላ ዓመታዊ በጀታቸው ውስጥ የተወሰነ “ድርሻ” ለፈንዱ እንደሚያዋጡ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተደንግጓል።
የፈንዱ ሌላኛው የገቢ ምንጭ የሚሆነው፤ “ከለጋሽ አካላት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ግለሰቦች” የሚሰበሰብ ገንዘብ ነው። “የሀገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰቢያ ስልቶችን” በመጠቀም የሚገኝ ገንዘብም እንደዚሁ የፈንዱ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን የአዋጅ ረቂቁ ያትታል። ከእነዚህ ምንጮች ውስጥ “የመንግስት እና የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሰራተኞች ከሚከፈላቸው የተጣራ ደመወዝ ላይ የሚታሰብ” ገንዘብ አንዱ እንደሆነ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

አዲሱ አዋጅ “የሀገር ውስጥ ሃብት” በሚል ከዘረዘራቸው 15 የገቢ ምንጭ አይነቶች ውስጥ አብዛኞቹ የመንግስት እና የግል ተቋማት የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ናቸው። በአዋጁ ላይ የተካተቱት የተለያዩ የገቢ ምንጮች “በተጠቃሚው ሰው ላይ እንዲሆን የተደረገው”፤ “የተቋማቱን ተወዳዳሪነት በየትኛውም መልኩ እንዳይነካ” ለማድረግ እንደሆነ አዋጁን ለማብራራት የቀረበው ሰነድ አስረድቷል።
በገቢ ምንጭነት ከተጠቀሱ ተቋማት ውስጥ “የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች” ይገኙበታል። ድርጅቶቹ “ለድምጽ እና ዳታ አገልግሎት ከሚያስከፍሉት የአየር ሰዓት ዋጋ ላይ” “ለኢትዮጵያ አደጋ ምላሽ ፈንድ” ገንዘብ መሰብሰብ እንደሚጠበቅባቸው በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተመላክቷል። የነዳጅ ሽያጭ አቅራቢ ድርጅት ከሚያገኘው ገቢ ላይ ለፈንዱ የሚውል የተወሰነ ገንዘብ መስጠት ይጠበቅበታል።
ከበረራ ትኬት ሽያጭ፣ ከፓስፖርት እና ቪዛ አገልግሎት ክፍያ፣ የንግድ ፈቃድ በሚወጣበት እና በሚታደስበት ጊዜ በቁርጥ የሚታሰብ፣ የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ለሚሰጠው አገልግሎት ከሚከፈለው ዋጋ ላይ የሚታሰብ ገንዘብ በተመሳሳይ የፈንዱ የገቢ ምንጭ ይሆናል። የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ከሚከፍሉት የአገልግሎት ክፍያ ላይ የሚታሰብ ገንዘብም በተመሳሳይ ለፈንዱ ይውላል።

ባንኮች፣ አነስተኛ እና ጥቃቅን የፋይናንስ ድርጅቶች ከሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የሚታሰብ ገንዘብ፤ ሌላው የፈንዱ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን የአዋጅ ረቂቁ ጠቁሟል። የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለሚሰጡት አገልግሎት ከሚሰበስቡት የአረቦን (premium) ክፍያ እና ከማንኛውም የአክሲዮን ትርፍ (dividend) ድርሻ ላይ የሚታሰብ ገንዘብም ወደ ፈንዱ የባንክ ሂሳብ እንዲተላለፍ ይጠበቃል።
የፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን ከኮንትሮባንድ ንግድ የሚይዛቸውን እቃዎች፤ በአይነት ወይም በጨረታ ከሸጠ በኋላ ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ ለፈንዱ ገቢ ማድረግ እንደሚገባው የአዋጅ ረቂቁ ያዝዛል። የኬሚካል አምራች ድርጅቶች ከሚሰጡት የምርት ሽያጭ አገልግሎት፣ የትንባሆ እና የአልኮል ምርቶች ሽያጭ አገልግሎት ላይ የሚሰበሰብ ገቢ ለፈንዱ ገቢ ከሚደረጉ የገቢ አይነቶች መካከል መሆናቸው የአዋጅ ረቂቁ ይገልጻል።
የባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎቶች ሽያጭ ላይ የሚሰበሰብ ገንዘብ ሌላው ለፈንዱ የሚውል የገቢ ምንጭ ነው። “ከሌሎች ምንጮች የሚገኝ ገንዘብን” ፈንዱ በገቢነት ሊጠቀም እንደሚችል በአዲሱ አዋጅ ላይ ተቀምጧል። “ተጨማሪ የገቢ ምንጮች”፤ አዋጁን ለማስፈጸም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ መሰረት ሊወሰኑ እንደሚችሉ የህግ ረቂቁ አመልክቷል።
“የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድን በወቅቱ አለመሰብሰብ፣ የተሰበሰበውን ገንዘብ በየወሩ መጨረሻ ወደ ፈንድ አካውንቱ ገቢ አለማድረግ፤ መዘግየት ወይም በሪፖርት አለመግለጽ የተከለከለ ነው”
– የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር የአዋጅ ረቂቅ
ወደፊት በሚወጣው በዚህ ደንብ፤ “እያንዳንዱ ዘርፍ ምን ያህል መጠን መዋጣት እንዳለበት እንደሚወሰንም” የአዋጅ ረቂቅ አክሏል። በአዲሱ አዋጅ የተዘረዘሩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት፤ በደንቡ የሚወሰነውን ክፍያ ሰብስበው ለፈንዱ ሂሳብ በወቅቱ ገቢ የማድረግ ግዴታም በአዋጁ ተጥሎባቸዋል።
“የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድን” “በወቅቱ አለመሰብሰብ”፣ “የተሰበሰበውን ገንዘብ በየወሩ መጨረሻ ወደ ፈንድ አካውንቱ ገቢ አለማድረግ”፤ “መዘግየት ወይም በሪፖርት አለመግለጽ” የተከለከለ እንደሆነ አዋጁ ያስጠንቅቃል። የፈንዱን ገቢዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣው ደንብ መሰረት ሰብስቦ ለፈንዱ የባንክ ሂሳብ ገቢ ያላደረገ ድርጅት ወይም ተቋም፤ “ዋናውን ገንዘብ እና የባንክ ወለድ አስር ከመቶ ቅጣት ጨምሮ እንዲከፍል” እንደሚገደድም በአዋጁ ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር )