በአፋር ክልል በሬክተር ስኬል 5.5 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

በአፋር ክልል በሬክተር ስኬል 5.5 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ዛሬ እሁድ መጋቢት 7 ምሽት መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት ገለጸ። ንዝረቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰማው ይህ ርዕደ መሬት፤ ከአዋሽ ከተማ በስተሰሜን 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተከሰተ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል።

የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ የተመዘገበ ርዕደ መሬት ሆኗል። እሁድ የካቲት 23፤ 2017 እኩለ ለሊት አቅራቢያ ከአዲግራት ከተማ 46 ኪሎ ሜትር በስተምስራቅ ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ የተከሰተው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 5.2 ሆኖ ተመዝግቦ ነበር

በተመሳሳይ ዛሬ እሁድ ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ53 ደቂቃ ላይ የተከስተው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በአካባቢው በየካቲት መጀመሪያ ገደማ ከተከሰተው በመጠን ያነሰ ቢሆንም በበርካታ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ጠንከር ያለ የንዝረት ስሜት አስከትሏል። ልክ የዛሬ ወር ከመተሐራ ከተማ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ የተመዘገበው ርዕደ መሬት፤ በሬክተር ስኬል 6.0 የደረሰ ነበር


ሆኖም ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተበት ጥልቀት፤ እንደ ዛሬው በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስላልነበር በአካባቢው የከፋ ጉዳት አለማድረሱን የዘርፉ ባለሙያዎች በወቅቱ አስታውቀዋል። በሬክተር ስኬል ከ5.5 እስከ 6.0 መጠን ያላቸው ርዕደ መሬቶች፤ በህንጻዎች እና በሌሎች ግንባታዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ እንደሆኑ በክስተቶቹ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት መረጃዎች ያመለክታሉ።

የምሽቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ንዝረት ከአዋሽ ከተማ በተጨማሪ በመተሐራ፣ በሚኤሶ፣ በአቦምሳ እና በገለምሶ ከተሞች መሰማቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ርዕደ መሬቶችን የሚመዘግበው “ቮልካኖ ዲስከቨሪ” በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል። እንደነዚህ ከተሞች ሁሉ በቆቦ፣ በሮቢት እና በደብረ ሲና የተሰማው ንዝረት “ቀላል” የሚባል እንደሆነ ድረገጹ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ የታከለበት ሲሆን በርዕደ መሬቱ ልኬት ላይም ማስተካከያ ተደርጎበታል]