የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የስልጣን ጊዜ ለማራዘም የሚያስችል የአዋጅ ማሻሻያ በፓርላማ ጸደቀ

በቤርሳቤህ ገብረ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 23፤ 2017 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የስልጣን ጊዜን ለማራዘም የሚስችል የአዋጅ ማሻሻያ አጸደቀ። የአዋጅ ማሻሻያው በአብላጫ ድምጽ ሲጸድቅ፤ ሁለት የፓርላማ አባላት ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል። 

ፓርላማው ማሻሻያውን ያጸደቀለት አዋጅ፤ የፌደራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበት ስርዓት ለመደንገግ ከ21 ዓመት በፊት የወጣ ነው። በዛሬው ስብሰባ የአዋጅ ማሻሻያውን የተመለከተ አጭር ማብራሪያ በንባብ ያሰሙት፤ በፓርላማ የመንግስት ዋና ተጠሪው ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።

ዶ/ር ተስፋዬ በዚሁ ማብራሪያቸው “የአዋጁን ትግበራ አስፈላጊ የሚያደርጉ እጅግ ውስብስብ የጸጥታና የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስፈልገው ጊዜ እንደጉዳዩ ክብደት ሊለያይ የሚችል መሆኑ ታይቷል” ብለዋል። በስራ ላይ ባለው አዋጅ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ “ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ሆኖ በመገኘቱ ክፍተት መፈጠሩንም” አስረድተዋል።  

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በነባሩ አዋጅ አተገባበር ወቅት የታዩ “ክፍተቶችን ለመሙላት” እና የአዋጁን አፈጻጸም በቀጣይነት “ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በማስፈለጉ” ማሻሻያው መዘጋጀቱን የመንግስት ዋና ተጠሪው ገልጸዋል። ዛሬ በጸደቀው የአዋጅ ማሻሻያ፤ በአንድ ክልል ውስጥ ለሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር የሚሰጠው የሁለት ዓመት የቆይታ ጊዜ እንደተጠበቀ ሆኖ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም የሚያስችሉ አዳዲስ ድንጋጌዎች ተካተውበታል።

በዚህም መሰረት የፌደራል መንግስት በአንድ ክልል ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ምክንያት ከሆነው ሁኔታ “ውስብስብነት አኳያ”፤ “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ” የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በክልሉ የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር የስልጣን ዘመን ለማራዘም እንዲችል በአዋጅ ማሻሻያው ስልጣን ተሰጥቶታል። አፈ ጉባኤው የጊዜያዊ አስተዳደሩን ቆይታ ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንዲራዘም ሊወስን የሚችልበት ድንጋጌም በዚሁ የአዋጅ ማሻሻያ ላይ ተቀምጧል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አማካኝነት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቆይታ እንዲራዘም የተላለፈ ውሳኔ “ለሁለተኛ ጊዜ ማራዘም ካስፈለገ”፤ አፈ ጉባኤው ለአስተዳደሩ የሚሰጠው ተጨማሪ የቆይታ ጊዜ ከአንድ ዓመት ያልበለጠ መሆን እንዳለበትም በዚሁ የአዋጅ ማሻሻያ ላይ ሰፍሯል። ሆኖም በአፈ ጉባኤው የሚሰጡ የማራዘሚያ ውሳኔዎች፤ በፌደሬሽን ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርበው መጽደቅ እንዳለባቸው የአዋጅ ማሻሻያው ደንግጓል። 

ይህ ማሻሻያ ለፓርላማ የቀረበው፤ በትግራይ ክልል የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በነባሩ አዋጅ መሰረት የተሰጠው የሁለት ዓመት የቆይታ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው። የፓርላማ አባላትን ጥያቄዎች ለመመለስ ከአንድ ሳምንት በፊት በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የስልጣን ዘመን ለማራዘም የህግ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዛሬው ስብሰባቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠቀሰውን የህግ ማሻሻያ ከማጽደቃቸው አስቀድሞ ጥያቄ እና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። በዛሬው መደበኛ ስብሰባ ጥያቄ ካቀረቡ ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር አወቀ አምዛዬ፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “እስካሁን ምን ተግባራትን እንደፈጸመ ለተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ማቅረብ ነበረበት” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አወቀ፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለምን ሪፖርት እንዳላቀረበም ጠይቀዋል። ይኸው ጊዜያዊ አስተዳደር፤ “ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ የተንቀሳቀሱ የአስተዳደር እና ወታደራዊ አካላትን ለምን ለፍርድ አላቀረበም” ሲሉም ተጨማሪ ጥያቄ አንስተዋል።

እኚሁ የፓርላማ አባል፤ ህወሓት “በከፍተኛ የጦር ጄነራል አማካኝነት በሌሎች ክልሎች ገብቶ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር” በቅርቡ የመከላከያ ሰራዊት ባወጣው መግለጫ መስማታቸውን አስታውሰዋል። ይሄ ሁኔታ ባለበት “ህወሓትን እንደ ድርጅት እያሽሞነሞንን እስከ መቼ ድረስ ነው የምንቀጥለው?” ሲሉም አቋም አዘል ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ዶ/ር አወቀ፤ ህወሓት ከአሸባሪነት መዝገብ በፓርላማው እንዲነሳ የተደረገበትን የቀደመ ሂደትም “አነጋጋሪ” ብለውታል። እንደ እርሳቸው ሁሉ የኢዜማ የፓርላማ ተመራጭ የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በርታም፤ ህወሓትን የተመለከቱ ጉዳዮችን በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አንስተዋል። 

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተፈረው የፕሪቶሪያ ስምምነት፤ ህወሓትን “ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ” እንደሚያስገድደው ጠቅሰዋል። የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት እና የማቋቋም ሂደቱ (DDR) አለመጠናቀቁ፤ በአሁኑ ወቅት ህወሓትን “ብቸኛው መሳሪያ የታጠቀ ፓርቲ” እንዳደረገውም ዶ/ር አብርሃም ገልጸዋል። 

ይህ ሁኔታ ከትግራይ ህዝብ ሰላም መደፍረስ አልፎ፤ ህወሓት አጠቃላይ የሀገሪቱ “የሰላም ጠንቅ እንዲሆን አድርጎታል” ሲሉ የኢዜማው የፓርላማ ተወካይ በአጽንኦት ተናግረዋል። ህወሓት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማፍረስ “ሰፊ እንቅስቃሴ” አድርጓል ሲሉ የወነጀሉት ዶ/ር አብርሃም፤ በቀጣይ በሚቋቋመው የጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ “ይህ እንዳይሆን ምን የታሰበ ነገር አለ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትሯ ሃና አርአያ ስላሴ፤ የፌደራል መንግስት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሰፊ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል። የፌደራል መንግስት ይህንኑ ጥረቱን አሁንም እንደሚቀጥል ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል። 

ዛሬ ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ማሻሻያ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜን ለማስቀጠል የሚያስችል እንደሆነ ሃና ገልጸዋል። የአዋጁ መሻሻል “ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚሰጠው የስራ ኃላፊነት መሰረት እንዲሰራ የሚያስችል” እንደሆነም ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በአዋጁ ማሻሻያ ላይ ከተካተተው “እንዴት ይራዘማል?”፣ “በምን መልኩ ይራዘማል?” ከሚለው በተጨማሪ፤ የቆይታ ጊዜውን የሚያራዘም ውሳኔ ሲተላለፍ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ነገር በማስተካከል የሚሰራቸው ተግባራት በዝርዝር ሊካተት እንደሚችል የፍትህ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። ሃና ለዚህ በማሳያነት ያነሱት፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ወደ መደበኛ ምርጫ ለመግባት ሊያደርጋቸው የሚገባቸውን ተግባራት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)