የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመበት “ህግ ተሻሽሎ”፤ የስልጣን ጊዜው ለተጨማሪ አንድ ዓመት ሊራዘም እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥቆማ ሰጡ። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራ ከተገመገመ በኋላ፤ “በግለሰቦች ደረጃ ለውጥ ሊካሄድ እንደሚችልም” አብይ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የትግራይ ጉዳይ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታን በተመለከተ፤ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 11፤ 2017 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የትግራይን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄ ያቀረቡት ሁለት የፓርላማ አባላት ናቸው።
ከጠያቂዎቹ አንዷ የሆኑት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተወካይ ብርቄ ባህሩ፤ በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ “ወደ ግጭት እንዳያመራ” ያላቸውን ስጋት አንጸባርቀዋል። በክልሉ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ “ድጋሚ ዋጋ እንዳያስከፍለን ምን እየተሰራ ይገኛል?” ሲሉ ከኦሮሚያ ክልል፣ ያያ ጉለሌ ምርጫ ክልል የተመረጡት የፓርላማ አባሏ ጥያቄቸውን ሰንዝረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲን በመወከል ከጉራጌ ዞን፣ እዣ ምርጫ ክልል ፓርላማውን የተቀላቀሉት አቶ ባርጠማ ፍቃዱም፤ “ለትግራይ ሁኔታ የማዕከላዊ መንግስት እልባት ለምን አይሰጥም?” ሲሉ ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተዋል። ህወሓት “እስከመቼ ሰላም እየነሳ ይኖራል?” ሲሉም አቶ ባርጠማ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ህወሓት ባለው “የስልጣን ሱስ” “የትግራይ ህዝብን እረፍት በመንሳት” “ሰላም እንዳይኖር የፕሪቶሪያ ስምምነት እየጣሰ ይገኛል” ሲሉ የወነጀሉት አቶ ባርጠማ፤ የህወሓት ሰዎች “አደብ እንዲገዙ መደረግ አለበት” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የፓርላማ አባሉን አስተያየት በሚያደምጡበት ወቅት ፊታቸው ላይ ፈገግታ ታይቷል።
አቶ ባርጠማ በጥያቄያቸው ማጠቃለያ የፌደራል መንግስት የትግራይ ሁኔታን “ማስተናገድ ያለበት” በፕሪቶሪያ በተፈረመው ስምምነት “መሰረት” መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል። “ተደራዳሪ የፌደራል መንግስትን ጨምሮ፣ ብልጽግናን ጨምሮ፣ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ያካተተ፣ ክልሉን የሚመራ ጤነኛ አደረጃጀት መፈጠር ያለበት ይመስለኛል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ የኢዜማው የፓርላማ ተወካይ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የትግራይ ክልልን በአሁኑ ወቅት እየመራ የሚገኘው ጊዜያዊ አስተዳደር “የተሰጠው” የሁለት ዓመት ጊዜ ማለቁን ጠቁመዋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩን የስልጣን ጊዜ ለማራዘም፤ “የፕሪቶሪያውን ስምምነት በሚያከብር መንገድ” “የህግ ማሻሻያ” እንደሚያስፈልግም ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።
በትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የሚያስችል ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው መጋቢት 9፤ 2015 ነበር። ደንቡ የተዘጋጀው፤ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ያደረጉትን የግጭት ማቆም ስምምነት መሰረት በማድረግ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
ይህንን ተከትሎ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በመጋቢት 14፤ 2015 ጊዜያዊ አስተዳደሩን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተሹመዋል። አቶ ጌታቸው “በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ውክልና የሚያረጋገጥ እና አካታች የሆነ አስተዳደር የማዋቀር ኃላፊነት” እንደተጣለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ከሹመቱ ሁለት ሳምንት በኋላ አቶ ጌታቸው 27 አባላት ያሉበትን ካቢኔ ይፋ አድርገዋል። በዚህ ካቢኔ ውስጥ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፤ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ደግሞ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊነት ቦታን አግኝተዋል።
“በፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ በምክትል ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ እና ጻድቃን ገብረትንሳኤ የሚመራው አስተዳደር፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጨማሪ ጦርነት እንዳይፈጠር፣ ያሉ ጥያቄዎች በንግግር እንዲመለሱ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል። “ምንም እንኳን ቀድሞ በነበረው ውጊያ ብንወቅሳቸውም፤ ላለፉት ሁለት አመታት በሰጡት አመራር ግን ማድነቅ ማመስገን እንፈልጋለን” ሲሉም አሞግሰዋቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሶስቱን አመራሮች “ተጨማሪ ውጊያ እንዳይነሳ ሙከራ በማድረግ” ቢያሞካሹም፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፈው ሁለት ዓመት የነበረው አፈጻጸም ግን “መገምገም አለበት” ብለዋል። በትግራይ በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ “በቅርቡ” እንደሚገመገም የተናገሩት አብይ፤ ከዚያ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተቋቋመበትን ህግ ወደማሻሻል እንደሚገባ አስረድተዋል።
“ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተገምግሞ፣ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎ፤ የፕሪቶሪያን ስምምነት በሚያከብር መንገድ ፣ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ስራውን እየሰራ፣ ህዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀት እና ህዝቡን የስልጣን ባለቤት የማድረጉን ሂደት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል”
– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
“ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተገምግሞ፣ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎ፤ የፕሪቶሪያን ስምምነት በሚያከብር መንገድ፣ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ስራውን እየሰራ፣ ህዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀት እና ህዝቡን የስልጣን ባለቤት የማድረጉን ሂደት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል” ሲሉ የቀጣይ ሂደቱን አካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። ይህንን ለማድረግ ከአቶ ጌታቸው፣ ከሌተናል ጄነራል ታደሰ እና ከሌተናል ጄነራል ጻድቃን ጋር “ልዩ ልዩ ውይይቶች” ሲያካሄዱ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በተመለከተ “የተለያዩ ፕሮፖዛሎች” መቅረባቸውን ያስረዱት አብይ፤ ስለዚሁ ጉዳይ ከሶስቱ አመራሮች በተጨማሪ “ከህወሓት እና ከሌሎች ፓርቲዎች” ጋር ንግግሮች እያደረግን ነው” ብለዋል። “በዚህ ንግግር መሰረት ህግ አሻሽለን፣ መጠነኛ ማሻሻያ አድርገን፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለሚቀጥለው አንድ አመት ይቀጥላል የሚል እምነት ነው በእኛ በኩል ያለው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የስልጣን ጊዜ በአንድ ዓመት ሲራዘም “በግለሰቦች ደረጃ ለውጥ ሊካሄድ እንደሚችልም” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው ፍንጭ ሰጥተዋል። “ግለሰቦች ሊቀያየሩ ይችላሉ። የነበረው ስራ ተገምግሞ፣ በጠንካራ ጎናቸው ተሞግሰው፣ በደካማ ጎናቸው ተወቅሰው፣ የሚቀያየሩ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)