በቤተልሔም ሠለሞን
በአማራ ክልል፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ጃዊ ወረዳ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ጀምሮ በተከሰተ የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት (አተት) መሰል ወረርሽኝ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው አስተዳደር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ። በወረዳው በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 40 ገደማ መድረሱን የወረዳው የጤና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
አተት መሰል ወረርሽኙ መጀመሪያ የታየው፤ በወረዳው በሚገኘው ብሔራዊ ቀበሌ ፍልውሃ በሚባል ጸበል ቦታ እንደሆነ የጃዊ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንበር ግርማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች፤ ወደዚህ ጸበል ቦታ ከመምጣታቸው አስቀድሞ በባህርዳር ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው አንዳሳ በሚባል ጸበል ቦታ እንደነበሩ መረጋገጡንም አስረድተዋል።
በአተት መሰል ወረርሽኝ መያዛቸው በምርመራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠው ሁለት ሰዎች እንደነበሩ የገለጹት የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ከሁለት ቀን በኋላ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 38 መድረሱን የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል። “በሁለት ቀን ውስጥ ይሄንን ያህል ኬዝ ገጥሞን አያውቅም። ከዚህ በፊት እንደዚህ አልገጠመንም። በ24 ሰዓት ውስጥ ወደ 20 ሰዎችን ማግኘት ማለት በጣም ከባድ ነው” ሲሉ አቶ መንበር የሁኔታውን አሳሳቢነት አመልክተዋል።
በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ውስጥ 30 የሚሆኑት በወረዳው ወደሚገኘው ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተከታተሉ መሆኑን የተናገሩት የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊው፤ ቀሪ ስምንት ሰዎች ወረርሽኙ በተከሰተበት የጸበል ቦታ እያታከሙ መሆኑን አክለዋል። ወረርሽኙ ከተከሰተበት የጸበል ቦታ ወደ ጃዊ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከተወሰዱ ህሙማን መካከል፤ የሁለቱ ህይወት ማለፉን የጃዊ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል አዳነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል።
“ሆስፒታል ላይ ልየታ ተደርጓል። ባለሙያ ተመድቦ፣ ለብቻ ነው የሚታከሙት። ጸበል ቦታ አካባቢ የታመሙትን ወደ ጎን አድርገው፤ ምልክቱ ያልታየባቸውን ለብቻ አድርገው፣ ትምህርት እንዲሁም የድንገተኛ ህክምና እየተሰጠ ነው” ሲሉ ጃዊ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የአተት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት አብራርተዋል።
በወረርሽኙ በተጠቁ ሰዎች ላይ አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት፣ ኃይለኛ የድካም ስሜት እና የአፍ መድረቅ ምልክቶች እንደሚታዩ አቶ መንበር ጠቁመዋል። “ምልክቶቹ በጣም ወደ ኮሌራ ያመዝናሉ። ለማረጋገጥ ናሙና መላክ አለበት። በተጨባጭ ኮሌራ ነው ብለን ለማረጋገጥ ልከናል” ሲሉ በትላንትናው ዕለት ናሙና ወደ ባህር ዳር መላካቸውን አስረድተዋል።
ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በማስከተል፤ በሰውነት ውስጥ የሚገኝን ፈሳሽ አሟጦ በማስወጣት፤ አቅምን በማዳከም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ካለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ እስከ የካቲት ወር መጀመሪያ ድረስ በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ ከተጠቁ 228 ሰዎች መካከል የአራቱ ህይወት ማለፉን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሯ” አሚናት ሙሀመድ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጋለች]