የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የበይነመረብ ሚዲያ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የዋስትና መብት ላይ ፖሊስ ያቀረበው አቤቱታ ላይ ውሳኔ አስተላለፏል። የሰበር ሰሚ ችሎቱ የፖሊስን ማመልከቻ ጭብጥ ከመመልከቱ በፊት የቀረበለት ጉዳይ “ይግባኝ ያስቀርባል” ወይስ “አያስቀርብም” የሚለውን ዛሬ ጠዋት መርምሯል። በዚህም ሰበር ሰሚ ችሎቱ ባሳለፈው ውሳኔ የፖሊስን ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ አፅንቷል። ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ለሶስተኛ ጊዜ የዋስትና መብቱ ተረጋግጦለታል። ይሁንና ይህ መግለጫ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ ከእስር አልተፈታም።
በአዲስ አበባ ከሚገኘው ግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች እሁድ ሰኔ 1 ቀን፤ 2017 በቁጥጥር ሥር የዋለው ተስፋለም ወልደየስ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የቂርቆስ ምድብ ችሎት በ15,000 ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ የወሰነው ሰኔ 3 ቀን፤ 2017 ነበር።
መርማሪ ፖሊስ ለአዲስ አበባ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ለጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የተፈቀደው የዋስትና መብት ላይ ያቀረበው ይግባኝ ትላንት ሰኔ 4 ቀን፤ 2017 ተቀባይነት አላገኘም። የይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ለሁለተኛ ጊዜ የጋዜጠኛ ተስፋለምን የዋስትና መብት በድጋሚ አክብሮለታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ ሐሙስ የተሰየመው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የህግ ስሕተት አለበት በማለት ፖሊስ አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ ነበር። የፖሊስ ይግባኝ አቤቱታ “ያስቀርባል” ወይስ “አያስቀርብም” የሚለውን የመረመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት “አያስቀርብም” የሚል ውሳኔ አስተላልፏል።
በተጨማሪም የስር ፍርድ ቤቶች የጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስን የዋስትና መብት እንዲከበር መፍቀዳቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት ያልተፈጸመበት እና ህግን የተከተለ ሆኖ ስላገኘው ውሳኔዎቹ እንዲጸኑ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ሶስቱም ፍርድ ቤቶች ያስተላለፉት ውሳኔ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ በፖሊስ አልተተገበሩም። ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ፖሊስ በፍርድ ቤቶቹ የተላለፉትን ትዕዛዞች በማክበር ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በተከበረለት ዋስትና መሰረት ከእስር እንዲፈታ በአጽንዖት ጥሪውን ያቀርባል።

