በጋምቤላ ክልል በጸጥታ ስራ ከተመደቡ የሰራዊት አባላት ውጪ “የትኛውንም የጦር መሳሪያ” ይዞ የሚገኝ እና የሚንቀሳቀስ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ የጸጥታ ኃይሎች “አስፈላጊው እርምጃ” እንደሚወሰዱ የክልሉ መንግስት አስጠንቀቀ። ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል፤ የፌደራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት “ሰፊ ስራዎችን” እያከናወኑ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
የክልሉ መንግስት ይህን ያስታወቀው፤ ወቅታዊ የክልሉም ሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ምሽቱን ባወጣው መግለጫ ነው። በጋምቤላ ከተማ እና በክልሉ ወረዳዎች ከሰሞኑ በተከሰተ “የጸጥታ ችግር” የሰው ህይወት መጥፋቱን እና ጉዳት መድረሱን የክልሉ መንግስት በዚሁ መግለጫው አንስቷል።
የጸጥታ ችግሩን “ትርምስ” ሲል የጠራው የክልሉ መንግስት መግለጫ፤ ለዚህ ተጠያቂ ያደረጋቸው “የክልሉ ህዝብ ሰላም መሆን እንቅልፍ የሚነሳቸው” እና “ግጭትና የሰው ሞት የሚያስደስታቸው” ያላቸውን “ኃይሎች” ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ መደፍረስ እና ግጭት ይከሰት እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፤ “የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት ለማረጋገጥ” መንግስት “የአመራር ለውጥ” ማደረጉን ጠቅሷል።
አዲስ የመጡት አመራሮች የነበረውን “የጸጥታ ችግር በመፍታት”፤ በልማት እና በሰላም ግንባታ ስራዎች “በርካታ ውጤቶች” እንዲመዘገቡ “ጥረቶች እያደረጉ” እንደሚገኙ የክልሉ መንግስት ገልጿል። የክልሉን ሰላም እና ልማት “ወደ ኋላ ለመመለስ የሚሰሩ” ሲል የክልሉ መንግስት የጠራቸው ኃይሎች፤ “በየቦታው ሰዎችን በመግደል፣ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ እና ህይወት እንዲጠፋ በማድረግ” ወንጅሏቸዋል።
“በእኩይ ተግባራት ላይ የተሰማሩ” በሚል በመግለጫው የተጠቀሱት ኃይሎች፤ የጸጥታ አካላትን እና አመራርን “ኢላማ” አድርገዋል ሲል የክልሉ መንግስት በመግለጫው ጠቅሷል። እነዚህ ኃይሎች “ወደ ለየለት የሕዝቦች እልቂት ለማስገባት የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል” ያለው መግለጫው፤ መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ተጠርጣሪዎችን “አድኖ በመያዝ ላይ” እንደሆነ ገልጿል።
የክልሉ ህዝብ “በጥፋት ላይ የተሰማሩ አካላትን” ሲመለከት “ጥቆማ” እንዲያደርግ ያሳሰበው የክልሉ መንግስት፤ ለፀጥታ ስራ ተመድበው ከሚሰሩ የሰራዊት አባላት ውጪ የትኛውንም የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን አግዷል። የጦር መሳሪያ ይዞ በሚገኝ እና በሚንቀሳቀስ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ የጸጥታ አካላት “አስፈላጊውን እርምጃ” እንደሚወስዱም የክልሉ መንግስት በዛሬው መግለጫው አስጠንቅቋል።
የክልሉ መንግስት ይህን ማስጠንቀቂያውን የሰጠው፤ በጋምቤላ ከተማ ከትላንት ማክሰኞ ረፋድ ጀምሮ የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው። በጋምቤላ ከተማ ተኩስ መሰማት የጀመረው፤ የከተማይቱ ፖሊስ አዛዥ በሆኑት ኮማንደር ኡሞድ ኡጁሉ ላይ ትላንት ረፋድ ላይ ግድያ መፈጸሙን ተከትሎ እንደሆነ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በተኩሱ ምክንያት ሰዎች መሞታቸውን እና መጎዳታቸውንም የከተማይቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ከትላንትናው ክስተት በኋላ የጋምቤላ ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውንም ነዋሪዎች አመልክተዋል። በጋምቤላ ከተማ ባለፈው ሳምንት ከተፈጸመ ጥቃት በኋላ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ በሚደረግ የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የሰዓት እላፊ መጣሉ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































