ኢዜማ በትምህርት ሚኒስቴር ባገኘሁት ኃላፊነት “ለምርጫ ቅስቀሳ የሚጠቅሙኝን ሥራዎች ሠርቻለሁ” አለ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ለምርጫ ቅስቀሳ የሚጠቅመውን ሥራ መሥራቱን አስታውቀ። የፓርቲው መሪ የትምህርት ሚኒስቴርን ለመምራት ባገኙት ዕድል፤ የፓርቲውን የትምህርት ፖሊሲ “ማስፈጸማቸውን” ገልጿል፡፡

ፓርቲው ይህን ያለው፤ ሰባተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ አስመልክቶ ዛሬ ታኅሣሥ 7፤ 2018 ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው። ኢዜማ በዚሁ መግለጫው፤ በዝምታ ውስጥ ያለው ሰፊው ማኅበረሰብ፣ ከምርጫ 2013 ልምድ በመውሰድ “የተለያዩ ኃሳቦች የሚንጸባረቁባቸው ምክር ቤቶች” እንዲኖሩ በሚያስችል መልኩ በምርጫው ይሳተፋል የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል። 

ኢዜማ ፈተናዎችን ተቋቁሞ በምርጫው ለመሳተፍ መወሰኑን ባስታወቀበት በዛሬው መግለጫው፤ በየደረጃው የመንግሥት ኃላፊነትን ለመውሰድ እንደሚወዳደርም ጠቁሟል። የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢዮብ መሣፍንት፤ ኢዜማ ምርጫው በሚካሔድባቸው አስቻይ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንደሚወዳደር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የአማራ እና የትግራይ ክልልን ጨምሮ፤ “የጸጥታ ችግር ሊቀረፍባቸው ይችላል ወይም ከነችግሩም ቢሆን ምርጫ ማካሔድ እንችላለን ተብሎ በሚታሰብባቸው ቦታዎች በሙሉ ኢዜማ ይወዳደራል” ብለዋል። ኢዜማ በ2013 ዓ.ም. በተካሔደው ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ ቀጥሎ በርካታ ተወዳዳሪዎችን ያቀረበ ፓርቲ እንደነበር ይታወሳል። 

በዚሁ ምርጫ አራት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ያሸነፈው ኢዜማ፤ የክልል መቀመጫዎችን ባሸነፈበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አባላቱ የተለያዩ ኃላፊነቶች ተሰጥቷቸው ሲሰሩ ቆይተዋል። የፓርቲው ሁለት አመራሮችም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሉ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተሹመው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። 

ኢዜማ የመንግሥትን ኃላፊነት በመጋራቱ እና በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ያላቸውን ይዘት በመተቸት በፓርቲው ላይ ቅሬታዎችን የሚያቀርቡ አካላት ቢኖሩም፤ ፓርቲው ትችቶቹን ሲያስተባብል ቆይቷል። ፓርቲያቸው ከፌዴራል ጀምሮ በተለያዩ የመንግሥት እርከኖች ላይ በተወካዮቹ አማካኝነት ያገኛቸውን የአስፈጻሚነት ኃላፊነቶች አምኖበት መቀበሉን በዛሬው አቶ ኢዮብ በዛሬው መግለጫ ላይ አስታውሰዋል።

ፓርቲው እነዚህን ኃላፊነቶች ተጠቅሞ ለምርጫ ቅስቀሳ የሚረዱትን ተግባራት ማከናወኑን የገለጹት የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፤ ለዚህም በማስረጃነት የትምህርት ሚኒስቴርን ጉዳይ አንስተዋል። ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ፤ የኢዜማ መሪ የሆኑትን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን የትምህርት ሚኒስትር አድርገው መሾማቸው አይዘነጋም። 

ላለፉት አራት ዓመታት ይህን መስሪያ ቤት የመሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ያለማንም ጣልቃ ገብነት “ያመኑበትን ሲሰሩ መቆየታቸውን” አቶ ኢዮብ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አንስተዋል። ኢዜማ ያገኘውን ይህን ኃላፊነት ተጠቅሞ የፓርቲውን “የትምህርት ፖሊሲ አስፈጽሟል” ሲሉም ተናግረዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር ከተከናወኑ ተግባራት መካከል “የኢዜማ ፖሊሲ ውስጥ የሌለ የለም” ያሉት አቶ ኢዮብ፤ ስትራቴጂ ከመንደፍ ጀምሮ የፓርቲያቸው መሪ የፈጸሟቸው የሚያኮሩ መሆኑንም ገልጸዋል። በትምህርት ሚኒስቴር “የምንኮራበት እና ለቀጣዩ ምርጫ ቅስቀሳ የምንጠቀምበትን ሥራ ሰርተናል” ሲሉ የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፓርቲው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በሌሎች ክልሎች በተወካዮቹ አማካኝነት ባገኘው የኃላፊነት ቦታም መሰል ለምርጫ ቅስቀሳ የሚጠቅሙትን ተግባራት ማከናወኑን አቶ ኢዮብ አስረድተዋል። “በመንግሥት ውስጥ በተሰጡን ኃላፊነቶች፤ ለሕዝብ የሚጠቅም እና ሰርተን ማሳየት እንደምንችል የሚያመለክቱ ሥራዎችን ሰርተናል” ሲሉም ተደምጠዋል። 

ኢዜማ የቀጣዩ ምርጫ ዕቅዱ “መንግሥት መሆን ነው” ያሉት አቶ ኢዮብ፤ ካለፈው ምርጫ ማግስት ጀምሮ ለቀጣዩ ምርጫ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል። ፓርቲው በአሁኑ ወቅት ዕጩዎችን እያዘጋጀ እንደሚገኝም አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)