ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ሀገራዊ ምርጫ ዘንድሮ እንደሚካሄድ ማረጋገጫ ሰጡ

የኢትዮጵያ መንግስት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በተያዘው ዓመት እንደሚካሄድ ማረጋገጫ ሰጠ። የመንግስትን ማረጋገጫ ዛሬ ሰኞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ላይ በይፋ ያሳወቁት፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ናቸው። 

ታዬ በህዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የስራ ዘመን መክፈቻ ላይ ባደረጉት በዚሁ ንግግር፤ የፌደራል መንግስትን ዓመታዊ እቅድ አቅርበዋል። የፕሬዝዳንቱ ንግግር አርባ ደቂቃ ገደማ የፈጀ ቢሆንም፤ የምርጫ ጉዳይ የተነሳው በማገባደጃው ላይ ነበር። 

በኢፌዲሪ ህገ መንግስት መሰረት በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፤ ዘንድሮ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስታወቀው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ ነበር። ቦርዱ በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ “በጣም ተለዋዋጭ በመሆኑ”፤ ሀገራዊ ምርጫው የሚካሄደው “ፈቃጅ” እና “አስቻይ” ሁኔታዎች ባሉቸው አካባቢዎች እንደሆነ በወቅቱ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ፕሬዝዳንት ታዬ በዛሬው ንግግራቸው “በያዝነው ዓመት በሀገራችን የሚካሄደው ሰባተኛ ሀገራዊ ምርጫ፤ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተዓማኒ ይሆን ዘንድ መንግስት በኃላፊነት ይሰራል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)