በቤርሳቤህ ገብረ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ መጪው ሀገራዊ ምርጫ “ፈቃጅ” እና “አስቻይ” ሁኔታዎች ባሉባቸው የምርጫ ክልሎች እንደሚደረግ ገለጸ። በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ “በጣም ተለዋዋጭ በመሆኑ”፤ ምርጫው በሚቃረብበት ወቅት ሁኔታው “በዝርዝር” እና “በጥልቀት” የሚታይ መሆኑንም አስታውቋል።
ቦርዱ ይህንን ያስታወቀው፤ የሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 25፤ 2017 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ነው። የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ምርጫን ለማድረግ በየአካባቢዎቹ “አስቻይ ሁኔታ” መኖር “የግድ” አስፈላጊ እንደሆነ በዚሁ መግለጫ ላይ አመልክተዋል።
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቦርዱ “በሁሉም አካባቢ ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ ነው ያቀደው። አሁንም በሁሉም አካባቢ ምርጫ እናደርጋለን ብለን ነው የምናቅደው” ሲሉ ሜላትወርቅ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች ውስጥ 102 በሚሆኑት ላይ ምርጫ አልተካሄደም።

ከእነዚህ መቀመጫዎች ውስጥ 38ቱን ሊይዙ የሚገባው የትግራይ ክልል ተመራጮች የነበሩ ቢሆንም፤ በወቅቱ በክልሉ ጦርነት እየተካሄደ ስለነበር ምርጫው ሳይካሄድ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት የትግራይ ክልል ባለፉት አራት ዓመታት በፓርላማ ውስጥ ተወካዮች የሉትም።
የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እንደዚሁ በጦርነት እና በግጭት ውስጥ በመቆየታቸው፤ የፓርላማ ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ በአካባቢያቸው ምርጫ ማድረግ አልተቻለም። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘጠኝ የተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮችን ጨምሮ አዲስ መንግስት ለመመስረት የሚያስችሉ የቀሪ የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ምርጫ የተካሄደው ሁለት ዓመት ዘግይቶ ነበር።
ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሲያካሄድ፤ የየአካባቢውን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተመሳሳዩ አካሄድ ሊከተል እንደሚችል የቦርዱ ሰብሳቢ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ጥቆማ ሰጥተዋል። ቦርዱ ምርጫ ለማካሄድ “መሬት ላይ ያለውን ነገር” የሚመለከተው፤ በምርጫ ክልሎች ደረጃ መሆኑን ሜላትወርቅ አስረድተዋል።

“የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመሰረተው ምርጫ ክልሎችን መሰረት ባደረገ ነው። ስለዚህ ከዚህ ጋራ የሚያያዝ ስለሆነ፤ በጥቅሉ ሳይሆን ፈቃጅ እና አስቻይ በፈጠሩበት ሁኔታዎች የምርጫ ክልሎች ሁሉ ላይ ምርጫውን እናደርጋለን። ለዚህም ነው ዝግጅታችን። ማንንም ልዮነት ሳያደርግ፤ በሁሉም ቦታ ለማድረግ እንችላለን በሚል የተነሳነው” ሲሉ የቦርድ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
ምርጫ ቦርድ እያከናወናቸው ካላቸው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መካከል፤ ከ50ሺህ በላይ የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች አደረጃጀትን እንደገና መመልከት አንዱ መሆኑን ሜላትወርቅ ገልጸዋል። ቦርዱ ከታዛቢዎች በቀረበለት ሪፖርት፤ የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ምቹ እንዳልነበሩ መረዳቱን ጠቅሰዋል። ታዛቢዎች አሊያም ሌሎች ወደ ቦታው መሄድ የሚፈልጉ ሰዎች፤ ጣቢያዎችን “ለማግኘት ይቸገሩ” እንደነበርም አስታውሰዋል።
የምርጫ ጣቢያዎች “ምቹ” እና “ተደራሽ” መሆናቸውን በተመለከተ፤ ቦርዱ በዚህ ዓመት ግምገማዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ሰብሳቢዋ በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል። የምርጫ ጣቢያዎቹ የሚገኙባቸው “ኮርድኔቶች” በመለየት፣ መረጃውን ለታዛቢዎች እና ለባለድርሻ አካላት በማጋራት፣ የጣቢያዎቹን የመገኛ ቦታ እና ርቀት ለማግኘት በሚያስችል መንገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። እስካሁን ባለው ሂደትም በ12 ሺህ ያህል የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ስራው መከናወኑንም አክለዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ ለሎጅስቲክስ ስራ የሚያግዝ፤ “የመንገድ tracking ስራ” በመካሄድ ላይ መሆኑን ሜላትወርቅ ጠቁመዋል። የምርጫ ኦፕሬሽናል ማንዋል ማዘጋጀት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች በኦንላይን የሚመዘገቡትን ሲስተም ማሻሻል እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ አሰራር የምርጫ ዕጩዎቻቸውን የሚያስመዘግቡበት ሲስተም ማልማት፤ ቦርዱ በቅደመ ዝግጅት ስራዎች ያከናወናቸው ሌሎች ተግባራት መሆናቸውን የቦርድ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]