ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የስልጤ ዞን ተወካዮች 800 ቤት ለአካባቢው ካልገነቡ ህዝብ እንዳይመርጣቸው አሳሰቡ  

በስልጤ ዞን ከወረዳ እስከ ፓርላማ ገዢውን ፓርቲ ወክለው የተመረጡ ተወካዮች፤ በጥቂት ወራት ውስጥ እያንዳንዳቸው 10 ቤት ለህዝብ ካልገነቡ በመጪው ምርጫ የአካባቢው ሰው ድምጽ እንዳይሰጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሳሰቡ። የፌደራል መንግስት 1.5 ሚሊዮን ቤቶች የግንባታ ዕቅድ፤ እንደ ስልጤ ዞን ባሉ አካባቢዎች በገጠር ኮሪደር ልማት የሚሰሩ ቤቶችን እንደሚያካትትም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ እና የቤት ግንባታ ያስተሳሰሩበትን አስተያየት የሰጡት፤ የዞኑን አመራሮች ጨምሮ ከከፍተኛ የክልል እና የፌደራል ባለስልጣናት ጋር “የገጠር ኮሪደር ስራዎችን” በተመለከተ ትላንት አርብ መስከረም 30፤ 2018 ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በከተሞች ከሚያከናውነው የኮሪደር ልማት በተጨማሪ በገጠርም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት ልክ የዛሬ ዓመት ነበር።

አብይ በገጠር ኮሪደር የመኖሪያ ቤት እና ተያያዥ መሰረተ-ልማት የሚገነቡባቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ አራት ዞኖች ባለፈው ረቡዕ እና ትላንት አርብ ተዘዋውረው ጎብኘተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ፤ ሀላባ፣ ከምባታ፣ ሀዲያ እና ስልጤ ዞኖችን ያዳረሰ ነበር።

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅድሚያ በጎበኟቸው ሀላባ እና ከምባታ ዞኖች የተሰሩ ቤቶች ከመረቁ በኋላ፤ ሁለቱ ዞኖች እያንዳንዳቸው 100 ቤቶች እንዲሰሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ይህ ትዕዛዝ “በየዋህነት” እና “በስህተት” የተላለፈ እንደነበር በትላንቱ ውይይታቸው የጠቀሱት አብይ፤ “ካለማወቅ ነው ይቅርታ ይደረግልኝ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ሁለቱ ዞኖች እንዲገነቡ የታዘዙት የቤት ብዛት፤ ለስልጤ እና ሀዲያ “አይሰራም” ያሉት አብይ፤ “እያንዳንዱ ዞን በትንሹ 1,000 ቤት ካልሰራ እኔ ወደዚህ ተመልሼ አልመጣም” ሲሉ ለአካባቢው ባለስልጣናት የቤት ስራ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ “አንድ ሺህ ቤት በአንድ ወር ከጨረስክ፤ በአንድ ወር እንመጣለን። በሁለት ወር ከጨረስክ፤ በሁለት ወር እንመጣለን። በስድስት ወር ከጨረስክ፤ በስድስት ወር እንመጣለን” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

አብይ ከዞኑ አስተዳዳሪ ጋር በነበራቸው ንግግር፤ በስልጤ ዞን ብቻ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል እና በፌደራል ምክር ቤቶች “80 የሚጠጉ ተመራጮች” መኖራቸውን እንደተገነዘቡ ጠቅሰው፤ እነዚህ ተወካዮች እያንዳንዳቸው አስር ቤት ቢገነቡ በድምሩ 800 ቤቶች በአካባቢው እንደሚኖሩ አስገንዝበዋል። ተወካዮቹ ቤቶቹን ከመጪው ምርጫ በፊት ገንብተው ማጠናቀቅ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።  

“እኔ ለስልጤ እህት እና ወንድሞቼ ማስተላለፍ የምፈልገው፤ እነዚህ 80 ሰዎች ቢያንስ አስር፣ አስር ቤት ካልገነቡ በሚቀጥለው ምርጫ አትምረጧቸው። ያልሰራ ሰው መመረጥ የለበትም። ዝም ብሎ እያወራ ምርጫ የሚባል ነገር የለም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እነማንን መምረጥ እንደሚገባቸው ጥቆማ ሰጥተዋል።

ቤቶቹ ከተገነቡ በኋላ “ደረታችንን ነፍተን ‘ሰራንልህ ብለን ነው’ እኛ ወደ ምርጫ የምንቀርበው እንጂ፤ ገና ተስፋ እየሰጠን ‘ከመረጠክኝ በኋላ እናደርግልሃለን’ እያልን ከሆነ መቼም አንለወጥም” ሲሉም አብይ ለባለስልጣናቱ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንቱ ውይይቱ ላይ የሰጡት ትዕዛዝ፤ “በስልጤ አካባቢ የተወለዱ በየትኛውም ደረጃ ያሉ አመራሮችን” የሚመለከት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሆኖም የዞኑ ተመራጮችም ይሁኑ በተለያየ እርከን የሚሰሩ የመንግስት ባለስልጣናት ቤቶቹን ለመገንባት የሚያስፈልጋቸውን ወጪ እንዴት መሸፈን እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አላብራሩም። በትላንትናው ውይይት የተገኙት እና የስልጤ ዞን ተወላጆች የሆኑት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሬድዋን ሁሴን እና የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ትዕዛዙን አዳምጠዋል።

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

አብይ በገጠር ኮሪደር ልማት የመኖሪያ ቤት ግንባታ፤ በዞኖች መካከል “ውድድር ያስፈልጋል” የሚል እምነታቸውንም በትላንቱ ውይይት ላይ አንጸባርቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንዴት ስልጤ ከሃዲያ ያንሳል? እንዴት ሃዲያ ከከምባታ ያንሳል? እንዴት ከምባታ ከሃላባ ያንሳል?” በማለትም አንዳቸው ከሌላቸው መፎካከር እንዳለባቸው ነግረዋቸዋል።

መንግስታቸው “ከ1.5 ሚሊዮን ያላነሱ ቤቶች” ለመገንባት ማቀዱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ይህ ማለት አዲስ አበባ ላይ ብቻ የሚገነባ አይደለም። የእናንተን ስራ ጨምሮ ነው። በየቀበሌው፣ በየሰፈሩ የምንሰራቸው ቤቶች ናቸው ተደምረው በሀገር ደረጃ ያንን ውጤት የሚያመጡት” ሲሉም አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)