በሙሉጌታ በላይ
በከተማ የሚሰራው የኮሪደር ልማት “በቂ ስላልሆነ” መንግስት በገጠር የኮሪደር ልማት በቅርቡ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በገጠር ልማትን መፍጠር የሚቻለው፤ መንግስት “በቤተሰብ ደረጃ ጣልቃ ሲገባ” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፤ ትላንት ሐሙስ መስከረም 30፤ 2017 “ታማኝ” ለተባሉ ግብር ከፋዮች በብሔራዊ ቤተ መንግስት በተዘጋጀ የእውቅና እና ሽልማት መርኃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት የህዳሴን ግድብ “ከሞላ ጎደል ማጠናቀቅ የቻለው” በእርዳታ ሳይሆን ከግብር ከፋዮች በተሰበሰብ ገንዘብ መሆኑን አስረድተዋል።
የሚመሩት መንግስት እየተገበረው የሚገኘው “በራስ አቅም ሀገርን የመቀየር” አካሄድ፤ ከህዳሴ ግድብ አልፎ በአዲስ አበባ ከተማ መታየት መጀመሩን አብይ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ የመጡ ለውጦች እና በሌሎች ከተሞች የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችንም ለእዚህ አባባላቸው በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር የተጀመረው የኮሪደር ልማት የመጀመሪያው ምዕራፍ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምዕራፍ በዘንድሮው በጀት ዓመት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል። የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፈው ማክሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 2,817 ሄክታር መሬት የሚሸፍን መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ በዚሁ መግለጫቸው፤ የኮሪደር ልማቱ የሚከናውንባቸው ስምንት የአዲስ አበባ አካባቢዎችን ይፋ አድርገዋል። ከእነዚህ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ካዛንቺስ አካባቢ ብቻ ፤ ወደ 4,600 ሰዎች እንደሚነሱ የከንቲባዋ አማካሪ የሆኑት አቶ ሞላ ንጉስ ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
በዚሁ አካባቢ 494 የግል መኖሪያ ቤት ያላቸው ነዋሪዎች መኖራቸውን የጠቆሙት የከንቲባዋ አማካሪ፤ ከእነዚህ መካከል 476ቱ ቦታ በእጣ እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል። ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል 91 የሚሆኑት ደግሞ የካሳ ክፍያ ማግኘታቸውን አማካሪው አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንቱ ንግግራቸው፤ መንግስታቸው ከከተማ ኮሪደር ልማት ወደ ገጠር ኮሪደር ልማት መሸጋገሩን በመርሃ ግብሩ ለታደሙ ግብር ከፋዮች ይፋ አድርገዋል። የገጠር ኮሪደር ልማት ዋና አላማ፤ አርሶ አደሩ “በቤተሰብ ደረጃ ህይወቱን እና የአኗኗር ዘዬውን እንዲቀየር ማድረግ” መሆኑንም አስረድተዋል።
በሰለጠነው ዓለም “በሰው ቤት የአኗኗር ዘዬ” የመንግስታት ጣልቃ መግባት “ነውር” እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ባላደጉ ሀገራት ግን መንግስታት “ድርብ ኃላፊነት ስላለባቸው” በቤተሰብ ደረጃ ጣልቃ መግባት እንደሚኖርባቸው አብራርተዋል። መንግስታት “በቤተሰብ ደረጃ ጣልቃ እየገቡ ‘የህንጻዎቻችሁ ቀለም መመሳሰል አለበት’፣ ‘በረንዳችሁ መጽዳት አለበት’ ብለው ጣልቃ ካልገቡ ያማረ የተዋበ ሀገር መስራትም ማስረከብ አንችልም” ሲሉም አብይ ተደምጠዋል።
“የማይለምን ሀገር፣ የማይለምን ቤተሰብ ለመፍጠር የሚቻለው፤ በቤተሰብ ደረጃ ምን አይነት ቀለም መቀባት እንዳለበት፣ በጓሮ ምን አይነት አትክልት መትከል እንዳለበት፣ ስንት ዶሮ፣ ስንት የሚታለብ ላም እንዳለው ሁሉ ጣልቃ መግባት ያስፈልጋል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
“የማይለምን ሀገር፣ የማይለምን ቤተሰብ ለመፍጠር፤ በቤተሰብ ደረጃ ምን አይነት ቀለም መቀባት እንዳለበት፣ በጓሮ ምን አይነት አትክልት መትከል እንዳለበት፣ ስንት ዶሮ፣ ስንት የሚታለብ ላም እንዳለው ሁሉ ጣልቃ መግባት ያስፈልጋል”
– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
አብይ በትላንትናው ዕለት በተካሄደ ሌላ መርሃ ግብር ላይ ተመሳሳይ ሃሳቦችን አንጸባርቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእርሳቸው ጽህፈት ቤት አቅራቢያ በሚገኘው በሳይንስ ሙዚየም በተከፈተው “ሀገራዊ የቡና ኤግዚቢሽን“ ላይ ባሰሙት ንግግር ስለ ገጠር ኮሪደር ልማት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዘንድሮ አመት መጀመሩን የገለጹት የገጠር ኮሪደር “የእያንዳንዱን አርሶ አደር ቤት” “የአኗኗር ዘዬ” የመቀየር አላማ እንዳለው አስረድተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በተጀመረው የኮሪደር ልማት፤ ከተማይቱን “ከአፈር፣ ከጭቃ ከነበረ የኑሮ ዘዬ ለማሻሻል ሙከራ” እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)