በጎንደር ከተማ አቅራቢያ ሁለት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ታፍነው መወሰዳቸውን አንድ ሪፖርት አመለከተ

በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ አቅራቢያ ባለፈው መስከረም ወር ሁለት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂ ቡድኖች ታፍነው መወሰዳቸውን አንድ ሪፖርት አመለከተ። በክልሉ ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው የመካነ ሰላም የተፈናቃዮች መጠለያ፤ በአካባቢው ባለው አስቸጋሪ የጸጥታ ሁኔታ እና ግጭት ምክንያት ለሰብአዊ እርዳታ አሁንም ተደራሽ አለመሆኑን ሪፖርቱ ገልጿል። 

ሪፖርቱን ትላንት ማክሰኞ ጥቅምት 4፤ 2018 ያወጣው፤ በኢትዮጵያ ለተለያዩ ጉዳቶች ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚከታተለው ስብስብ (cluster) ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን፣ ለጋሾችን እና የመንግስት ተቋማትን ያካተተው ስብስብ በዚሁ ሪፖርቱ፤ በመስከረም ወር በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ሁኔታዎችን ዳስሷል።

ወርሃዊው ሪፖርት በዳሰሳው ከሸፈናቸው አምስት ክልሎች መካከል፤ በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ እየተካሄደበት የሚገኘው የአማራ ክልል ይገኝበታል። በክልሉ ያለው ግጭት በትራንስፖርት መዋቅሩ ላይ ከባድ ተጽዕኖ ማሳደሩን ሪፖርቱ አመልክቷል። የጭነት መኪናዎችን እና የአገር አቋራጭ አውቶብሶችን የሚያሽከረክሩ ሹፌሮችን ኢላማ ያደረጉ እገታዎች እንደሚፈጸሙም ሪፖርቱ ጠቅሷል። 

በመስከረም ወር በጎንደር ከተማ አቅራቢያ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂ ቡድኖች ታፍነው የተወሰዱ ሁለት የእርዳታ ሰራተኞች፤ በደባርቅ እና ጎንደር መካከል ባለው መንገድ በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን የደህንነት ችግር አጎልቶ ያሳየ መሆኑን ሪፖርቱ ገልጿል። የደባርቅ ጎንደር መንገድ ለሰብአዊ እርዳታ እንቅስቃሴዎች እና ለሰላማዊ ሰዎች አሁንም “ከፍተኛ አደጋ” የደቀነ መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ታፈነው የተወሰዱት እርዳታ ሰራተኞች አሁን ያሉበት ሁኔታ ሳይገልጽ ቀርቷል።

በአማራ ክልል በአሽከርካሪዎች ላይ ያነጣጠረው እገታ፤ በክልሉ ያለውን የንግድ ሁኔታ፣ የአቅርቦት ሰንሰለት እንዲሁም የሸቀጦች እና የሰዎች ዝውውር ማወኩን ሪፖርቱ አትቷል። በክልሉ ባለው ግጭት፣ በተደጋጋሚ በሚያጋጥሙ የመንገድ መዘጋቶች እና የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት ምክንያት፤ በግልጽ የሚታይ የዋጋ ንረት እንዳለም አክሏል።

በግጭት እና በአስቸጋሪ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት፤ በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው የመካነ ሰላም የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ እንደ ነሐሴ ሁሉ ባለፈው ወርም ተደራሽ አለመሆኑ ተመልክቷል። በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኘው የጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ያለው የጸጥታ ስጋት ከፍተኛ እንደሆነ ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በዚህ ምክንያት የአካባቢው ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ለመገኘት፣ ነዋሪዎች ወደ ገበያ ለመሄድ እና ማገዶ ለማምጣት መቸገራቸውን ሪፖርቱ አስረድቷል። በዚሁ የተፈናቃዮች መጠለያ አቅራቢያ ባሉት በዛ ያሉ ወታደሮች ምክንያት በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ “ኢላማ እንሆናለን” የሚለው ፍርሃት አሁንም እንዳለም ተገልጿል። 

በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ 75 በመቶ የሚሆኑት የተፈናቃይ መጠለያዎች በመስከረም ወር በንፋስ እና በዝናብ መጎዳታቸውም በሪፖርቱ ተካትቷል። በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙት የጃሪ ቁጥር 1 እና የኩታበር 41 የተፈናቃይ መጠለያዎች “አፋጣኝ ጥገና” እንደሚያስፈልጋቸውም ሪፖርቱ አሳስቧል።

በጃሪ ቁጥር 1 መጠለያ ጣቢያ የሚገኘው የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር በመበከሉ የጤና አደጋ መደቀኑን እና በዚህ ላይ አፋጣኝ እገዛዎች እንደሚያስፈልጉ ሪፖርቱ ጠቁሟል። በጃሪ ቁጥር 2 መጠለያ ጣቢያ ውሃ ባለመኖሩ፤ ተፈናቃዮች ውሃ ለማግኘት ለአንድ ሰዓት ያህል በእግራቸው ለመጓዝ እንደሚገደዱ እና ይህም ለተለያዩ አደጋዎች እያጋለጣቸው እንደሆነ ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)