የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎች መካከል ከ15 እስከ 20 በመቶ ያሉትን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲያልፉ ማድረግ የሚቻል ከሆነ “በጣም ትልቅ” ውጤት እንደሆነ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። አንድም ተማሪ ለዩኒቨርሲቲ ማሳለፍ ካልቻሉ እና ጉዳት ከደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል 700 ያህሉ ተለይተው፤ “የክትትል” እና “እገዛ” ስራ ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጀመርላቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፤ የመስሪያ ቤታቸው የሩብ አመት አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ አርብ ህዳር 5፤ 2018 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው። የመስሪያ ቤቱን ሪፖርት በንባብ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ እሸቱ ገላዬ ናቸው።
አቶ እሸቱ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡት 608,742 ተማሪዎች ውስጥ 96.2 በመቶ የሚሆኑት ፈተናውን መውሰዳቸውን በሪፖርታቸው አመልክተዋል። በተፈጥሮ ሳይንስ እና ማህበራዊ ሳይንስ ዘርፎች ለፈተና ከተቀመጡት ተማሪዎች ውስጥ፤ 50 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 8.9 በመቶዎቹ ብቻ እንደሆኑ ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ይህ ቁጥር ከ2016 የትምህርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር 3.3 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑንም ስራ አስፈጻሚው አክለዋል። በ2016 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 50 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 5.5 በመቶው ብቻ ነበሩ።
በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እየተመዘገበ ያለው ይህን መሰሉ ውጤት፤ ባለፉት ዓመታት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄዱ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ነበር። የዘንድሮው የፈተና ውጤትም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ስራዎች በሚከታተለው በፓርላማው የሰው ሃብት ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ ተነስቶበታል።
በቋሚ ኮሚቴው የትምህርት ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ታደሰ ጌጡ፤ በ2017 የትምህርት ዘመን ለዩኒቨርሲቲ የማለፊያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ካለፈው ዓመት አንጻር መሻሻል የታየበት ቢሆንም አፈጻጸሙ “አሁንም ዝቅተኛ” መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ታደሰ ባለፈው ዓመት ተማሪዎቻቸውን ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ አንድም ተማሪ ማሳለፍ አለመቻላቸውንም በተጨማሪነት ጠቅሰዋል።

“የትምህርት ስራ በቀጥታ ኃላፊነት ያሉባቸው አካላት ባሉበት፤ ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ የማይችሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ የቋሚ ኮሚቴ አባሉ የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮችን ጠይቀዋል። “በተከታታይ አንድም ተማሪ በማያሳልፉ እና አነስተኛ ቁጥር በሚያሳልፉ ትምህርት ቤቶች ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለምን ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አልቻለም?” ሲሉም ተያያዥ ጥያቄ አቅርበዋል።
ችግሩ በቀጣይነትም እንዳይቀጥል “ምን ተጨባጭ መፍትሄ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል?” ሲሉም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ጥያቄዎቹን ለመመለስ አስቀድመው እድል ያገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ለውጤቱ ዝቅተኛነት እርሳቸው ወደ ኃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት የነበረውን ሂደት ተችተዋል።
ባለፉት ዓመታት የነበረው የፈተና አሰጣጥ እና አጠቃላይ የትምህርት ዘርፉ “የሞራል መሰረት”፤ “ክፉኛ የተናጋበት ጊዜ ነበር” ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነቅፈዋል። በእነዚህ ዓመታት ከትምህርት ምዘና ጋር የተያያዘው ሂደት በሙሉ “በመሰረታዊ መልኩ ፈርሶ ነበር ማለት ይቻላል” ሲሉም ተደምጠዋል።
“ፈርሶ ነበር የምለው ለምንድን ነው? የትምህርት ምዘና የሚሰጠው ተማሪዎች ያሉበትን የእውቀት ደረጃ ለመለካት ከሆነ፤ ያ በመጀመሪያ ደረጃ በርግጥም የተማሪዎችን እውቀት የሚለካ የአሰጣጥ ዘዴ ነበር ወይ? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል” ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ጉዳዩ ጥልቅ ፍተሻ እንደሚያስፈልገው በቀደሙ ስብሰባዎች ያንጸባረቁትን ሀሳብ ደግመውታል።
“ያለንበት ሁኔታ ምን እንደሆነ እንኳን በደንብ ማወቅ አለመቻላችን ትምህርትን የትምህርት ሂደቱን ለማሻሻል ፍጹም የማያስችል [ነበር]” ሲሉም አክለዋል። ተማሪዎች የነበሩበትን ይህንን ሁኔታ በማየት፤ የፈተናው አካሄድ መቀየሩን ሚኒስትሩ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል።
“[ፈተና] ማንነታችንን በግልጽ ያሳየናል። በእውነተኛ መሰረት ላይ የተመሰረተ የተማሪዎቻችንን ውጤት ያሳየናል። የሞራል መሰረታችንን መደላደሉን ይፈጥርልናል” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ሆኖም “ፈተና ብቻውን የትምህርትን ጥራት” እንደማያሻሽል አስገንዘበዋል። የትምህርት ስርዓቱን ማሻሻል በትውልድ ደረጃ የሚመጣ የረጅም ጊዜ ለውጥ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ይህንን እውን ለማድረግም “በስፋት የተለዩ ጉዳዮች” ላይ “አንድ በአንድ መስራት” እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
“[ፈተና] ማንነታችንን በግልጽ ያሳየናል። በእውነተኛ መሰረት ላይ የተመሰረተ የተማሪዎቻችንን ውጤት ያሳየናል። የሞራል መሰረታችንን መደላደሉን ይፈጥርልናል”
– ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ የትምህርት ሚኒስትር
አንዳንዶቹ ጉዳዮች “በአጭር ጊዜ” በትንሹም ቢሆን “ውጤት እያመጡ” ሊሄዱ የሚችሉ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። የትምህርት ሁኔታውን ለማሻሻል የሚረዱ ነገሮች “ገና እየተሰሩ” መሆናቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በአጭር ጊዜ “የሚለወጡ” ጉዳዮች እንዳሉ አመልክተዋል።
“ለምሳሌ ተማሪው ‘ሰርቆ፣ አጭበርብሮ ማለፍ አይቻልም’ የሚል እምነት ሲይዝ ማጥናት ይጀምራል። በማጥናቱ ምክንያት ለማለፍ ያለው እድል ከፍ ይላል። ትምህርት ቤቶች፤ ተማሪዎች አሁን በትክክለኛው መንገድ እየተመዘኑ እንደሆነ ሲያዩ፤ ያ ምዘና ደግሞ ያ ትምህርት ቤት በትክክል ትምህርት እያስተማረ እንዳልሆነ የሚያሳይ [ስለሚሆን] በመምህራን በትምህርት ቤት አስተዳደሮች ላይ ጫና ይፈጥራል። ከዛም እነሱ ይበልጥ ማስጠናት ይጀምራሉ” ሲሉ ሚኒስትሩ ጉዳዩን አብራርተዋል።
በቀጣይ ዓመታት ከ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በጣም ብዙዎቹ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናዎችን አልፈው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይገባሉ የሚል “ግምት” (assumption) እንዳለ አንስተዋል። ይሁንና ሚኒስትሩ “በጣም ጥሩ ትምህርት ያስተምራሉ” የሚባሉ እንደ ፊንላንድ ያሉ ሀገራትን በምሳሌነት በማንሳት፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ምጣኔ በእነዚህ ሀገራት ጭምር ትንሽ መሆኑን አመልክተዋል።

በፊንላንድ ለአራት አመት የዲግሪ ትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ተማሪዎች ብዛት “22 በመቶ” መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ የተቀረሩት “በስፋት እና በጥራት የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት” የሚማሩ መሆናቸውን ለፓርላማ አባላቱ አስገንዝበዋል። በኢትዮጵያ ባለፉት ባለፉት 20 ዓመት የተለመደው በገፍ የማሳለፍ ሁኔታ “normal” ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት እና ይህ አስተሳሰብ መስተካከል የሚገባው እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ተነስተን ካየነው፤ ምናልባት 20 በመቶ ከደረሰ በጣም ትልቅ ነው። በእኛ አይነት ሀገሮች ከ15 እስከ 20 በመቶ ባለው range ውስጥ ማሳለፍ ከቻልን ከዚያ ኢኮኖሚው የሚፈልገው የskill level መድረስ እንችላለን” ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ “እኛ ምኞታችን ሄደን ሄደን እዚያ 15፣ 20 በመቶ አካባቢ ለመድረስ ነው። ስለዚህ ከዚያ አንጻር ባለፉት ሶስት አመታት ያሳየነውን እድገት ስናይ፤ ለራሳችንም የገረመን በጣም ከፍተኛ እመርታ ነው የመጣው” ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ የውጤት መሻሻሉን አሞካሽተዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት በዚህ ዓመት ወደ ዩኒቨርስቲ ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ማደጉን ነው። ቁጥሩን “ትንሽም”፣ “በቂም” ያልሆነ ሲሉ የጠሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ እድገቱ በዚሁ አካሄድ ከቀጠለ በሁለት እና ሶስት ዓመት “የምናስበው ጣሪያ ላይ እንደርሳለን” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ፕሮፌሰሩ ብርሃኑ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው፤ በበይነ መረብ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ጉዳይን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴ ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል። የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄ በንባብ ያሰሙት አቶ ታደሰ ጌጡ፤ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያን በበይነ መረብ ከተፈተኑት ተማሪዎች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
በወረቀት ፈተናውን ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል ወደ ዩኒቨርሲቲ የማለፊያ ውጤት ያመጡት 4.4 በመቶዎች ብቻ መሆናቸውን የገለጹት የፓርላማ አባሉ፤ “የውጤት ልዩነት መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል። ባለፈው ዓመት ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች መካከል በበይነመረብ የተፈተኑት 134,570 እንደሆኑ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ባለፈው ዓመት በበይነ መረብ ፈተናውን የወሰዱት ተማሪዎች፤ በወረቀት ቢፈተኑም “ትልቅ ውጤት” ያመጡ የነበሩ ተማሪዎች እንደሆኑ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በምላሻቸው አስገንዝበዋል። በበይነ መረብ ፈተናውን የወሰዱ ተማሪዎች “የተሻለ ዝግጅት ያላቸው” መሆናቸውን የገለጹት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ ከእነዚህ ውስጥ በክልሎች በሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ እንዳሉበት አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሁሉም ተማሪዎች በበይነ መረብ ፈተናውን መውሰዳቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ከሌሎች አካባቢዎች ሁሉ ለዩኒቨርስቲ ያለፉ ተማሪዎች “ትልቅ” ቁጥር የተመዘገበውም በመዲናይቱ መሆኑን አብራርተዋል። በከተማይቱ በ2017 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ500 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ብዛት 1,321 ነው።
በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቻቸውን ወደ ዩኒቨርስቲ ካሳለፉ 50 ትምህርት ቤቶች መካከል አስራ ሰባቱ የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ ከሁለት ሳምንት በፊት አስታውቆ ነበር። በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው ዓመት ለዩኒቨርሲቲ ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች ብዛት 1,225 መሆኑ በዛሬው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተነስቷል።
እነዚህን ትምህርት ቤቶች በሚመለከት ከፓርላማው ቋሚ ኮሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በሰጡት ምላሽ፤ “ስር የሰደደ ችግር ያለባቸው” እና “የተጎዱ” 700 ትምህርት ቤቶች መለየታቸውን አመልክተዋል። ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች “ክትትል” እና “እገዛ” እንዲደረግ ስምምነት ላይ መደረሱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ስራው በአንድ ወር በኋላ እንደሚጀምር ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































