በሚዛን አማን ማረሚያ ቤት ታስረው የነበሩ 27 ደቡብ ሱዳናውያን ተፈትተው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በሚዛን አማን ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የነበሩ 27 ደቡብ ሱዳናውያን ወጣቶች ተፈትተው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ገለጸ። አርብቶ አደሮቹ ወጣቶች በኢትዮጵያ መቼ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ባይገለጽም፤ የደቡብ ሱዳን መገናኛ ብዙኃን አንድ ዓመት ገደማ በእስር ሳይቆዩ እንዳልቀረ ዘግበዋል። 

ወጣቶቹን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሂደት በስኬት መጠናቀቁ የተገለጸው፤ የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መንደይ ሰማያ ከኢትዮጵያ አቻቸው ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጋር በጉዳዩ ላይ ያደረጉትን የስልክ ውይይት በማስመልከት በዛሬው ዕለት በተሰራጨ መግለጫ ነው። የደቡብ ሱዳን መንግስት 27 የታጠቁ አርብቶ አደሮች፤ በኢትዮጵያ በእስር ላይ እንደሚገኙ ያረጋገጠው ባለፈው መስከረም ወር አጋማሽ ነበር።

የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ አፑክ አዩኤል ማየን በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ከምስራቅ ኢኳቶሪያ ግዛት 27 ወጣቶች “በድንገት” ሁለቱ ሀገራት የሚዋሰኑትን ዓለም አቀፍ ድንበር እንዳቋረጡ ተናግረው ነበር። የምስራቅ ኢኳቶሪያ ግዛት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር የሚዋሰን ነው።

አፑክ አዩኤል ማየን በዚህ መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ የታሰሩ ዜጎቻቸው “ከብት አርቢዎች ናቸው። እንደተለመደው ታጥቀዋል” ሲሉ ወጣቶቹ አርብቶ አደር መሆናቸውን ጠቁመው ነበር። ወጣቶቹን ለማስፈታት ሀገራቸው አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል  ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተደራደረች እንደምትገኝም ቃል አቃባይዋ በወቅቱ አስታውቀዋል። 

አርብቶ አደር ወጣቶቹን ለማስለቀቅ፤ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት የልዩ ፕሮግራሞች ልዩ ልዑክ ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ ከሚገኘው የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ጋር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከትላንት በስቲያ አርብ ባወጣው መግለጫ አመልክቶ ነበር። በዚሁ ዕለት የሃያ ሰባቱ ወጣቶች የመፈቺያ ሰነድን የኢትዮጵያ መንግስትን በመወከል የሚዛን አማን ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጌትነት ፈቃዱ መፈረማቸው ተገልጿል።

በዚሁ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ምክትል አምባሳደር ዴንግ ኦቤድ፤ ወጣቶቹን ይዘው በዛሬው ዕለት ወደ ጁባ እንደሚጓዙም የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በአርብ መግለጫው ጠቁሞ ነበር። መስሪያ ቤቱ ዛሬ ባወጣው መረጃ፤ ሃያ ሰባቱ ወጣቶች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አረጋግጧል። 

ከ1,100 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝመውን የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ድንበር እየተሻገሩ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች ጭምር በየጊዜው ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል። ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በተጨማሪ በጋምቤላ በኩል ድንበር የሚሻገሩ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች፤ ግድያ፣ የህጻናት አፈና እና የቀንድ ከብቶች ዝርፊያ እንደሚፈጽሙ ክልሉ በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)