የማርበርግ ሻይረስ በሽታን መመርመር የሚያስችል ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ ዛሬ ወደ ጂንካ መላኩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ የተከሰተውን የማርበርግ ቫይረስ በሽታን፤ በቦታው ሆኖ መመርመር የሚያስችል ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ በዛሬው ዕለት ወደ አካባቢው መላኩን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናገሩ። በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ “በሙከራ ደረጃ ላይ” ያሉ ክትባቶች እና መድኃኒቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ስራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ይህን የገለጹት በወቅታዊ የጤና ጉዳይ ላይ ዛሬ ሰኞ ህዳር 8፤ 2018 በሰጡት መግለጫ ነው። ዶ/ር መቅደስ በዚሁ መግለጫቸው መስሪያ ቤታቸው ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ 17 ናሙናዎች ወስዶ ባደረገው ምርምራ፤ ሶስቱ በበሽታው መያዛቸው ማረጋገጡን አስታውቀዋል። 

በማርበርግ ቫይረስ መያዛቸው የተጠረጠሩ ስድስት ሰዎች የበሽታውን ምልክቶች አሳይተው ህይወታቸው እንዳለፈ የገለጹት የጤና ሚኒስትሯ፤ ነገር ግን በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሟቾች ሶስት ብቻ መሆናቸውን አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት የበሽታው ምልክቶችን ካሳዩ ሰዎች ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን “የመለየት” እና “ክትትል” የማድረግ ስራዎች “በሰፊው እየተሰራ” መሆኑንም ዶ/ር መቅደስ አመልክተዋል።

በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት በጤና ተቋማት እና ከዚያ ውጭ ያሉ ንክኪ የነበራቸው 129 ሰዎች “ራሳቸውን ለይተው እንዲያስቀመጡ” መደረጉን እና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ የተያዘ ሰው በህክምና ቦታ ውስጥ እንደሌለ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ በላብራቶሪ ምርመራ የተገኙ ምልክቶች ያለባቸው ናሙናዎች “እያሰባሰቡ” መሆኑን አክለዋል። 

ናሙናዎችን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከማከናወን ይልቅ በዚያው በሽታው በተከሰተበት አካባቢ ለማካሄድ እንዲቻል፤ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ በዛሬው ዕለት ወደ ጂንካ ከተማ መላኩንም ዶ/ር መቅደስ ተናግረዋል። የተንቀሳቃሽ ላብራቶሪው ወደ ስፍራው እንዲጓዝ   መደረጉ፤ ውጤቶችን “ቶሎ ቶሎ ማወቅ የሚያስችል” መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በ12 ሀገራት የተከሰተው የማርበርግ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ “እንዴት መጣ?” የሚለውን ምላሽ የሚሰጥ ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ከትላንት በስቲያ ወደ ስፍራው መጓዙንም የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ቡድኑ ወደ ስፍራው ያቀናው፤ የቅድመ ዝግጅት እና የመከላከያ ቁሳቁሶችን ይዞ እንደሆነም ገልጸዋል። 

የተለያዩ የሙያ ስብጥሮችን የያዘው ቡድኑ፤ “በሽታው ከየት ተገኘ? እነማን ናቸው የታመሙት? የት ነው በሽታውን ያገኙት?” በሚለው ላይ ጥልቅ ትንተና እና የምርመራ ስራ እንደሚያከናውንም አስታውቀዋል። ይኸው የከፍተኛ ተመራማሪዎች ቡድን፤ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ቅኝት እና የምርምር ስራዎች የሚሰሩ ባለሙያዎችን የያዘ እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል። 

በለሊት ወፎች አማካኝነት ወደ ሰዎች የሚተላለፈው የማርበርግ በሽታ፤ እንዴት ከሰው ወደ ሰው ተላለፈ የሚለውንም ቡድኑ ጥናት እንደሚያደርግም በዛሬው መግለጫ ላይ ተመልክቷል። “እንዳስፈላጊነቱ ሁሉም ባለሙያዎች በሚሰጡት እና በሚኒስቴራችንም በሚሰጠው ሳይንሳዊ recommendation መሰረት፤ እዚያ አካባቢ ያሉትንም የለሊት ወፎችንም በማጥመድ የሚሰሩ፤ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ እና የላብራቶሪ፣ የባዮሴፍቲ እና የሴኪዩሪቲ ጥንቃቄ ተወስደው የሚሰሩ ስራዎችን ለመስራት አቅም ያላቸውን ባለሙያዎችን ልከናል” ሲሉ ዶ/ር መሳይ ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ የተከሰተው የማርበርግ ቫይረሰ በሽታ ከአጎራባች ሀገራት መምጣት አለመምጣቱን በተመለከተም የቅኝት፣ የክትትል እና የመረጃ ልውውጥ ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1967 በጀርመን ማርበርግ እና ፍራንክፈርት ከተሞች የተከሰተው ይህ በሽታ፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ኬንያን ጨምሮ  እስካሁን በ12 ሀገራት ላይ እንደታየ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። 

በሽታው ባለፉት ዓመታት የተከሰተባቸው ሀገራት ታንዛንያ እና ሩዋንዳ ናቸው። ተመሳሳይ ተላላፊ በሽታዎች በድንበር በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ፤ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት “የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራ” ሲያከናውን መቆየቱን ዋና ዳይሬክተሩ በዛሬው መግለጫቸው ላይ አስገንዝበዋል።

“ሀገራችን በተለይ ከኮቪድ ወዲህ የህብረተሰብ ጤና አደጋ የቁጥጥር ስርዓትን ለማጠናከር ሰፊ መዋዕለ ንዋይ በማፈሰስ ሰፊ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት 18 በሚሆኑ የየብስ መግቢያ እና መውጪያ ኬላዎች ላይ እንዲሁም በአራት ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች ላይ “ጠንካራ የሆነ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ስራዎች” እያካሄዱ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለኬንያ እና ለደቡብ ሱዳን አካባቢዎች ቅርብ በሆነው በደቡብ ኦሞ ዞን የቅኝት ስራዎችን “በተደራጀ” እና “በልዩ ሁኔታ” እንደሚሰራ ዶ/ር መሳይ ለዚህ በማሳየነት ጠቅሰዋል። “ለምሳሌ ኝያንጋቶም አካባቢ ህብረተሰቡ ለተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚሄደበት እና እንቅስቃሴዎችም ያሉባቸው ቦታዎች ስለሆኑ፤ ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር በተላላፊ በሽታዎች ቀጥታ ስርዓት ውስጥ የተጋላጭነት እና የስጋት ሁኔታን በየጊዜው እንሰራለን” ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ድንበር ተሻጋሪ ተላላፊ በሽታዎችን በተመለከተ ከጎረቤት ሀገራት ጋር “በየቀኑ” መረጃዎችን እንደሚለዋወጡ የገለጹት ዶ/ር መሳይ፤ ከሀገር ውጭ ህክምና የሚከታተሉ ሰዎች የሚመጡባቸው ቦታዎች ላይ ስርዓት ዘርግተው እየሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል። የስጋት ደረጃቸው ከፍ ባሉባቸው እና ብዙ ህዝብ በሚገለገልባቸው ቦታዎች ላይ “መረጃዎች በየቀኑ የምናገኝበት እና ምላሽ የምንሰጥበት ስርዓት አለ” ሲሉም ማስተማመኛ ሰጥተዋል። 

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ በበኩላቸው ወረረሽኞችን መቆጣጠርን በተመለከተ ከሀገር አቀፍ፣ ከአህጉር አቀፍ እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አስታውሰዋል። “ዋናው ዓላማችን ወረረሽኙን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከዚህ አንጻር የመጀመሪያ ስራቸው ያደረጉት በውጭ ሀገራት በመሞከር ላይ የማርበርግ በሽታ መድኃኒቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣት መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

በአሁኑ ወቅት የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለማከም የሚውል ዕውቅና ያገኘ መድኃኒትም ሆነ ክትባት እንደሌለ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ይህንኑ በዛሬው መግለጫ ላይ ያነሱት የጤና ሚኒስትሯ፤ ሆኖም በሌሎች ሀገራት በሙከራ ላይ ያሉ መድኃኒቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ጥረቶች እየተደረጉ ገልጸዋል። 

“ከዚህ በፊት የተሞከሩትን የክትባት፣ የመድኃኒት የሌሎች መከላከያ ነገሮችም እንዴት አድርገን ህብረተሰባችን ጋር ማድረስ እንችላለን የሚለውን በተዋረድ ስራዎቻችንን ጀምረናል”

– ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ የጤና ሚኒስትር

“ከዚህ በፊት የተሞከሩትን የክትባት፣ የመድኃኒት የሌሎች መከላከያ ነገሮችም እንዴት አድርገን ህብረተሰባችን ጋር ማድረስ እንችላለን የሚለውን በተዋረድ ስራዎቻችንን ጀምረናል” ሲሉ ዶ/ር መቅደስ አስታውቀዋል። “በዚህ ሰዓት እጃችን ላይ ያለ፣ ዓለም የሚያውቀው የእዚህ በሽታ መድኃኒት የሚባል የለም። መከላከሉ ላይ አተኩረን እና ምልክቶች ሲኖሩ ቶሎ ህክምና በመውሰድ ነው የምናክመው” ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ጨምረው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)